በሽብር የተከሰሱት ሙስሊሞች ያቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ አከራከረ

addisadmassnews Mar 31 2014

635 የመከላከያ ምስክሮች በተከሣሾች ተቆጥረዋል
በትናንትናው እለት ሙስሊሙ ህብረተሰብ ተቃውሞ አሰምቷል

በአወሊያ ት/ቤት መነሻነት “ድምፃችን ይሠማ” በሚል ከተፈጠረው መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተያያዘ በእነ አቡ በከር መሃመድ መዝገብ ስር፣ በሽብር ወንጀል የተከሰሱት 18 ግለሰቦች ያቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ ጭብጥ ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤቱን አከራክሯል፡፡ 
የተለያዩ የሽብር ተግባሮች ውስጥ ተሳትፈዋል ተብለው ክስ የቀረበባቸው 18 ተከሳሾች፣ ቀደም ሲል በአቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ማስረጃ ይከላከሉ ሲል ፍ/ቤት ብይን መስጠቱን ተከትሎ ይከላከሉልናል ያላቸውን 635 የሰው ምስክሮች ቆጥረዋል፡፡ 
በትናንት በስቲያው ችሎት ተከሳሾች በጠበቆች አማካይነት ከቀረቡት የመከላከያ ማስረጃ ጭብጥ ውስጥ አቃቤ ህግ የሚቃወማቸውን ነጥቦች በዝርዝር ጠቅሶ አቅርቧል፡፡ ከተጠቀሱት የመከላከያ ማስረጃ ጭብጦች መካከልም “ሃይማኖታዊ ቃላትን የሃይማኖት አባቶችን አቅርበን እናስተነትናለን” ማለታቸው  ፍ/ቤቱን በስፋት አከራክሯል፡፡ 
ቀደም ሲል በአቃቤ ህግ የማስረጃ አቀራረብ ወቅት ሲጠቀሱ ነበር ከተባሉት ሰደቃ፣ ጅሃድ፣ አዛን፣ አህባሽ እና ሌሎችም ሃይማኖታዊ ትርጉም አላቸው ለተባሉ ቃላት ሙያዊ ትንታኔ እናሰጥበታለን መባሉን የተቃወመው አቃቤ ህግ፤ “የእነዚህ ቃላት ትርጓሜና ትንታኔ የሚቀርብበት ምክንያት የለም፣ በዚህ ችሎት እየታየ ካለው ጉዳይ ጋርም አይገናኝም“ ሲል አመልክቷል፡፡ ፍ/ቤቱም በማጣሪያ ጥያቄው እነዚህን ቃላት ለማስተንተን ሙያዊ ማስረጃ ማቅረብ ለምን ያስፈልጋል ሲል የጠየቀ ሲሆን የተከሳሽ ጠበቆች በሰጡት ምላሽ፤ ቀደም ሲል አቃቤ ህግ ማስረጃውን ሲያቀርብ “አህባሽ የሚባል ሃይማኖት የለም” በማለቱ ሃይማኖቱ መኖሩን ለማስረዳት፣ ወሃቢያን በቀጥታ ከሽብርተኝነት ጋር አያይዞ በማስረዳቱ ስለወሃብያ ምንነት ለማስረዳት፣ አዛን በማይደረግበት ጊዜ አዛን አድርገው ህዝቡን ቀስቅሰዋል በማለቱ አዛን መቼ እና እንዴት ይደረጋል የሚለውንና ሌሎች ሃይማኖታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልጋቸውን ተንትኖ ለማስረዳት መሆኑን አመልክተዋል፡፡ እነዚህን ቃላት ሽፋን አድርገው ወንጀል ፈፅመዋል ስለተባለም ትክክለኛ ፍቺውን ለማስገንዘብ ነው ብለዋል፡፡ 
በተከሣሾች ማስረጃ ውስጥ ግልፅነት ይጎድላቸዋል ተብለው በአቃቤ ህግ ከተጠቀሱት መካከልም አቃቤ ህግ “የኡስታዞች (አስተማሪዎች) ቡድን ብሎ የጠራው የአድማ ቡድን አይደለም፤ ሃይማኖታዊ እውቀትን ለማስፋፋት የተደራጀ ነው” ያሉ ሲሆን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ “አድማ ለማድረግና ወንጀል ሊሰሩ የተደራጁ ናቸው አላልኩም” ሲል አቃቤ ህግ ተከላክሏል፡፡ በዚህ ጭብጥ ላይ ክርክር እንዳይደረግበትም አመልክቷል- አቃቤ ህግ፡፡
ሌላው “እኛ የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ለመሆን ተመርጠን ችግሩን ለመፍታት በመንግስትና በህዝቡ መካከል እንደ ድልድይ ስናገለግል ነበር፡፡” በማለት አግኝተናቸዋል ያሏቸውን ባለስልጣናት ስም ዝርዝር በመከላከያ ማስረጃቸው መዘርዘራቸውን በመጥቀስ፤ አቃቤ ህግ ግልፅ አይደለም ሲል ተከራክሯል፡፡ ጠበቆች በበኩላቸው፤ ከህዝበ ሙስሊሙ ተመርጠው የሙስሊሙን ጥያቄ ለመንግስት ለማቅረብ የተወከሉ መሆኑን ለማስረዳት ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 
የ1997 ዓ.ም የምርጫ ቀውስን ተከትሎ የቅንጅት መሪዎች ጉዳይ በታየበት በአቃቂ 08 ቀበሌ አዳራሽ በዋለው በዚህ ችሎት፤ ከአቃቤ ህግ እና ከጠበቆች ክርክር ባሻገር ፍ/ቤቱ በማስረጃ ጭብጥ ዝርዝሩ ላይ ቀኖች በሚገባ አልተገለፁም የሚሉና የተለያዩ የማጣሪያ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆችም የተለያዩ የቀን ማስተካከያዎችን አድርገዋል፡፡ 
በመቶዎች የሚቆጠሩ የተከሳሾች ቤተሰቦች እና ወዳጅ ዘመዶች የታደሙበት ችሎቱ፤ በዚህ የማስረጃ ጭብጥ ክርክር ላይ የጠዋቱ ጊዜ ባለመብቃቱ ፍ/ቤቱ ጉዳዩን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለከሰዓት በኋላ የቀጠረ ሲሆን ችሎቱ ከሰዓት በኋላ ቀጥሎ ዳኞች ጉዳዩን መርምረው ውሳኔ ለመስጠት ሰዓት እንዳልበቃቸው በመግለፅ፤ መዝገቡን ለፊታችን ማክሰኞ ቀጥረዋል፡፡ በእለቱ ዳኞች ተቀይረው ስለነበር  ቅያሬውን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት የቀኝ ዳኛው፤“መደበኛ ዳኞች እክል ስለገጠማቸው ሂደቱ እንዳይቋረጥ ነው እኛ የተገኘነው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በትናንትናው እለት መርካቶ በሚገኘው ታላቁ አንዋር መስጊድ በተከናወነው የጁማ ሶላት ስግደት ሥነሥርዓት ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ 
ለደቂቃዎች በቆየው በዚህ የተቃውሞ ድምጽ ነጭ ሪቫን በሁለት እጃቸው ወደ ላይ ዘርግተው በማውለብለብ አሜን! አሜን! አሜን! የሚለውን ቃል ሲያስተጋቡ እንደነበር ለመታዘብ ተችሏል፡፡ በቦታው ፖሊስ የነበረ ቢሆንም ተቃውሟቸውን ባሰሙ የእምነቱ ተከታዮችና በፖሊስ መካከል ምንም ግጭት አልተፈጠረም፡፡ 

Read 33627 times