የክልል መንግስታትን ግንኙነት የሚያጠናከር የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው

ኢዜአ Mar 31 2014

የክልል መንግሥታት የሕዝቦቻቸውን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍ እያዘጋጀ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ፤ ለረቂቅ ሕጉ ግብዓት ለማሰባሰብ ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በተዘጋጀ ዓውደ ጥናት ላይ እንደተናገሩት ፥ ድህነትና ኋላቀርነትን በማስወገድ በሚፈጠረው ልማት የሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጠናከረ የመንግሥታት ግንኙነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

የክልል መንግሥታት ከፌዴራል መንግሥት እንዲሁም የክልል መንግሥታት እርስ በርሳቸው የሚፈጥሯቸው ግንኙነቶች የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጥቅሞችን የሚያስጠብቁ ሊሆኑ ይገባልም ነው ያሉት።

ግንኙነቶቹ ሕገ-መንግሥቱን በመጠበቅና በማስጠበቅ ፥ የፌዴራል ስርዓቱ ቀጣይነት እንዲኖረውና ከትውልድ ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ለማስቻል የተጠናከረ የሕግ ማዕቀፍና ስርዓት መፍጠር እንደሚገባም ነው አፈ ጉባዔው የተናገሩት።

በተጨማሪም መንግሥታዊ ተቋማት በኢኮኖሚያዊ ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በተዋረድ ካሉ እርከኖች እንዲሁም ከአቻ ተቋማት ጋር የሚደረጉት ጎናዊ የመንግሥታት ግንኙነቶች በሕግ ማዕቀፍ የማጠናከሩ ስራ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የተደረጉ የመንግሥታት ግንኙነቶች የሕግ ማዕቀፍና ፖሊሲ ባይኖራቸውም ፥ በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ሁኔታዎች ሲካሄዱ እንደቆዩ ጠቅሰው ፥ ይህ አካሄድ የራሱ የሆነ ውስንነት ያለው በመሆኑ ሊሻሻል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

በመሆኑም ምክር ቤቱ የክልል መንግሥታት የሚያደርጓቸውን ግንኙነቶች የሚያጠናክር የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፍ አዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ ከፀደቀ በኋላ  ተግባራዊ እንደሚደረግም ነው የገለፁት።

ምክር ቤቱ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከፎረም ኦፍ ፌዴሬሽንስ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው በዚሁ ዓውደ ጥናት የክልል ምክር ቤቶች ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮዎች ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና የፌዴራል ተቋማት ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

በዚሁ ወቅት ''የመንግስታት ግንኙነት ጽንሰ ሀሳብና የአገራት ተሞክሮ'' በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ በተሳተፊዎች ውይይት መካሄዱን ኢዜአ ዘግቧል።

Read 33658 times