ፈቃድ ሳይኖረው የነዳጅ ማደያ በመክፈትና ባዕድ ነገር በመቀላቀል ወንጀል የተከሰሰው ግለሰብ ተቀጣ

Fanabc Mar 28 2014

የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የንግድ ፈቃድ ሳይኖረው በራያ ቆቦ ከተማ የነዳጅ ማደያ በመክፈትና ነዳጅን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ ለገበያ በማቅረብ ፤ በሸማቾችና በተሽከርካሪ ንብረት ላይ ጉዳይ ባደረሰ ግለሰብ ላይ የ11 ዓመት ዕኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት አስተላለፈ።

አቶ ነጋ አስገዶም የተባለው ይሄው ፍርደኛ የተባበሩት ብሄራዊ ፔትሮሊየም አ.ማ በሚል በከፈተው የነዳጅ ማደያ ውስጥ በገንዘብ ተቀባይነት  ወሎ ቆቦ ነጋ አስገዶም ማደያ በሚል ህገወጥ የመሸጫ ቲኬት እየቆረጠ ንግዱን ሲያከናውን በነበረው አቶ ይመር አዳነንም ችሎቱ በእስራትና በገንዘብ ቀጥቷል። 

አንደኛ ተከሳሽ አቶ ነጋ አስገዶም ሁለተኛ ተከሳሽ ይመር አዳነ ይባላሉ።

1ኛ ተከሳሽ አቶ ነጋ አስገዶም አራት  ክስ  የቀረበበት ሲሆን ፥ የመጀመሪያው ክስ የፀና ፍቃድ ሳይኖረው በራያ ቆቦ ከተማ 02 ቀበሌ የተባበሩት ብሄራዊ ፔትሮሊየም አማ አገልግሎት መስጫ በሚል ማደያ መክፈት ፣ ሁለተኛው ወሎ ቆቦ ነጋ አስገዶም ማደያ የሚል የመሸጫ ቲኬት በማዘጋጀት ለሸማቾች ሲሸጥ መገኘቱ እንደሆነና የተቀሩት ክሶችም በማደያው በገንዘብ ተቀባይነት ከሚሰራው 2ኛ ተከሳሽ አቶ ይመር አዳነ ጋር በመሆን ውሃ የተቀላቀለበት ነዳጅ ለህብረተሰቡ በማቅረባቸው ነው።

በተጨማሪም አቶ ወንደሰን ካሳ የተባሉ ግለሰብ ተሽከርካሪ ነዳጅ ማስተላለፊያ ፓምፕ ላይ ጉዳት በማድረስ 12 ሺህ በር የሚደርስ የተሽከርካሪውን አካል ለብልሽት መዳረጋቸው ፣ አቶ ብርሃን ደበሳ ለአሽከርካሪያቸው ከማደያው የገዙት ናፍጣ ውሃ የተቀላቀለበት ሆኖ ማለዳ ላይ ተሽከርካሪው አልነሳ ማለቱ እንዲሁም 20 ሺህ በር የሚያወጣ ጉዳት ፓምፕና ሞተሩ ላይ ማጋጠሙን በተደረገው ምርመራ መጣራቱ ተመልክቷል።

በወሎ ዞን ፍትህ መምሪያ ፖሊስ አማካኝነት ለሰሜን ወሎ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የቀረበውን ክስ የተመለከተው ችሎቱም ፤ ክስና ማስረጃውን አረጋግጦ የጥፋተኛነት  በይን ሰጥቷል ።

ለዚህ የወንጀል ድርጊታቸውም አንደኛ ተከሳሽ አቶ ነጋ አስገዶም በ11 ዓመት ፅኑ አስራትና በ60 ሺህ ብር እንዲሁም፤ 2ኛ ተከሳሽ ይመር አዳነ በ6 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል።

Read 34100 times Last modified on Mar 28 2014