በሐሰተኛ ሰነድ የሰበር ውሳኔ አግኝቶቷል የተባለ ይዞታ በድጋሚ ፍርድ ቤት ቀረበ

Ethiopian Reporter Mar 26 2014

ለሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበውና ሐሰተኛ መሆኑ የተገለጸው ሰነድ በፌደራል ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ ዳይሬክቶሬት ተመርምሮ ‹‹ተፈርሟል ወይም አልተፈረመም ለማለት አልተቻለም›› የሚል አሻሚ ምላሽ የተሰጠበት ቢሆንም፣ በሞግዚትነት ተሹመው ያስተዳድሩት የነበረን ያደራ ይዞታ ‹‹ከባለቤቴ የገዛሁት ነው›› በማለት እስከ ሰበር ችሎት ድረስ ክርክር ተደርጎበት ውሳኔ አግኝቶ የነበረው የውርስ ይዞታ ጉዳይ፣ በሥር ፍርድ ቤት ክርክር ሊደረግበት ለግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. ተቀጥሯል፡፡

የታላቅ ወንድማቸውን ልጆች በሞግዚትነት እንዲያስተዳድሩ በቤተሰብ ጉባዔ ከተሾሙ በኋላ፣ ስፋቱ 780 ካሬ ሜትር የሆነውን የመኖሪያ ቤትና ቦታ በሐሰተኛ ሰነድ የግላቸው ለማድረግ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሰው ነበር የተባሉት ግለሰብ ወ/ሮ እታበዛሁ ንጉሴ ይባላሉ፡፡ የወራሾች አባትና የግለሰቧ ታላቅ ወንድም መሆናቸው የተገለጸው ግለሰብ ደግሞ አቶ አወቀ ንጉሴ እንደሚባሉ የፍርድ ቤት ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

በሐሰተኛ ሰነድ ሊወሰድ ነበር የተባለው የግል ይዞታ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ቀበሌ 17/18 በአሁኑ ወረዳ 8 ካዛንቺስ አሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ ፊት ለፊት የሚገኝ ሲሆን፣ የይዞታው ባቤት በ1973 ዓ.ም. መሞታቸውም በሰነዶች ላይ ተጠቅሷል፡፡

አባታቸው አቶ አወቀ ንጉሴ በሞቱበት ወቅት ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት ያነሰ እንደነበር የተጠቀሰው ወራሾች አቶ ዮሴፍ አወቀ፣ ያዕቆብ አወቀ፣ ዮሐንስ አወቀና እሌኒ አወቀን በሚመለከት፣ ዘጠኝ አባላት ያሉት የቤተ ዘመድ ጉባዔ ግንቦት 10 ቀን 1978 ዓ.ም. ተሰብስቦ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ የቤተሰቡ ጉባዔ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ለአቅመ አዳምና ሔዋን ያልደረሱትን የሟች አቶ አወቀ ንጉሴ ልጆች፣ የታናሽ እህታቸው ወ/ሮ እታበዛሁ ንጉሴ ባለቤት ባላምባራስ ጤና ፈለቀ በሞግዚትነት እንዲያስተዳድሩ መመረጣቸውን ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡

ለ13 ዓመታት እንደ አባት በመሆን የሟችን ንብረት በመጠበቅና ልጆቹን በማስተዳደር የቆዩት ባላምባራስ ጤና ፈለቀ በ1986 ዓ.ም. በመሞታቸው፣ ባለቤታቸውና የአቶ አወቀ ንጉሴ ታናሽ እህት ወ/ሮ እታበዛሁ ንጉሴ፣ የባለቤታቸውን ኃላፊነት በመረከብ የወንድማቸውን ልጆች ንብረት ማስተዳደር እንደጀመሩ በሰነድ ሰፍሯል፡፡ አክስታቸው ወ/ሮ እታበዛሁ ንጉሴ የወንድማቸውን የአቶ አወቀን ንብረት የማስተዳደር ሥልጣን ከባለቤታቸው ባላምባራስ ጤና የወሰዱ ቢሆንም፣ በወቅቱ የአቶ አወቀ ልጅና ወራሽ ከሆኑት ውስጥ አቶ ዮሴፍ አወቀ ንብረት ለማስተዳደር ዕድሜው ደርሶ ስለነበር ለአክስቱ ሙሉ ውክልና መስጠቱም ተጠቅሷል፡፡ የአቶ አወቀ ወራሾች ለትምህርትና ለተለያዩ ሥራ ኑሮአቸውን በአሜሪካ በማድረጋቸው ውክልና የሰጧቸው አክስታቸው ወ/ሮ እታበዛሁ፣ በውክልና ከሚያስተዳድሩት ቤት የሚያገኙትን የኪራይ ገንዘብ እንዲጠቀሙበት ትተውላቸው እንደነበርም ለማስረዳት ያቀረቧቸው ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡

ወ/ሮ እታበዛሁ የራሳቸውም ልጆች አሜሪካ በመሆናቸው አብዛኛውን ጊዜያቸውን አሜሪካ በማሳለፍ እየተመላለሱ ንብረቶችን በመቆጣጠር ላይ እያሉ፣ መንግሥት አካባቢው መልማት እንዳለበት ያወጣውን መመርያ ተከትሎ የአቶ አወቀ ወራሾች እነ ዮሴፍ አወቀ ከአባታቸው በውርስ ባገኙት ቦታ ላይ፣ ለአባታቸው ማስታወሻ የሚሆን ሕንፃ ለመገንባት እንደፈለጉ በወቅቱ አሜሪካ ለነበሩት አክስታቸው ይነግሯቸዋል፡፡ በመቀጠልም እሳቸው (ወ/ሮ እታበዛሁ) አብዛኛውን ጊዜ አሜሪካ ስለሚሆኑ የሰጧቸውን ውክልና እንደሚሽሩት ሲያሳውቋቸው፣ እሺም እንቢም የሚል መልስ ሳይሰጡ ውክልና ለሰጧቸው ለእነ ዮሴፍ ሳያሳውቁ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

የአክስታቸው በድንገት ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ያሳሰባቸው ወራሾች፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የአክስታቸውን ውክልና በማንሳት ሌላ ተወካይ መሾማቸውንና የወ/ሮ እታበዛሁ ውክልና መሻሩን ለሚመለከታቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች አዲሱን ተወካይ ማሳወቃቸውን፣ የውክልና ሰነድ ማያያዛቸውን ለፍርድ ቤት ያቀረቧቸው ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለወንድማቸው ልጆች ሳያሳውቁ ወደ ኢትዮጵያ መጡ የተባሉት ወ/ሮ እታበዛሁ፣ ንብረት እንዲያስተዳድሩ የተሰጣቸውን ሙሉ ውክልና ይዘው ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በማምራት የስም ለውጥ እንዲደረግላቸውና በአቶ አወቀ ንጉሴ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ የቤት ካርታ በስማቸው እንዲዞር ይጠይቃሉ፡፡

የሚመለከታቸው የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ መሥሪያ ቤቶች የአቶ አወቀን ዶሴ ሲያወጡት፣ የወ/ሮ እታበዛሁ ንጉሴ ውክልና መውረዱንና በሌላ ግሰለብ መወከሉን የመሥሪያ ቤቶቹ ሠራተኞች ያስረዱዋቸዋል፡፡ በድርጊቱ የተበሳጩት ወ/ሮ እታበዛሁ ወንድማቸው ሲሞቱ የልጆቻቸው ሞግዚት በመሆን በቤተሰብ ጉባዔ ከተመረጡት ባለቤታቸው ባላምባራስ ጤና ፈለቀ፣ የወራሾችን ቤት ሚያዚያ 5 ቀን 1980 ዓ.ም. በተደረገ ውል በ80 ሺሕ ብር መግዛታቸውን በመግለጽ ንብረታቸው እንዲመለስላቸው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 8ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ክስ መመሥረታቸውን የክስ ቻርጁ ይገልጻል፡፡

የወራሾች ወኪልም ‹‹በውርስ የተላለፈ ቤት እንዴት ይሸጣል? በወቅቱ የነበረው የደርግ አገዛዝ ደግሞ ቤት መሸጥም ሆነ መለወጥ እንደማይቻል ክልከላ ነበረው፡፡ ሌላው ደግሞ  በወቅቱ ቤቱን ስለመግዛታቸው ሊያስረዱ የሚችሉበት በወረዳ፣ በውልና ማስረጃ እንዲሁም በክፍለ ከተማ የተረጋገጠና የገባ ማስረጃ በሌለበት፣ ክሱ ሊሰማና ሊከራከሩ እንደማይገባ በመግለጽ አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤት ማስገባታቸውን ሰነዶች ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ማስረጃ እንዲያቀርብ ተጠይቆ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው የሰነድ ማስረጃ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የስልክ ክፍያ እየተፈጸመ የሚገኘው በወራሾች አባት ስም መሆኑን ከማረጋገጥ ውጪ ወ/ሮ እታበዛሁ የሚባሉ ግለሰብ በቅፁም ውስጥ ሆነ በሌላ ነገር ላይ ስማቸው አለመኖሩን የገለጸ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ታኅሳስ 12 ቀን 2005 ዓ.ም. በሰጠው ብይን የቤቱን ሽያጭ ውል በመቀበልና ክሱ በይርጋ መታገዱን በማሳወቅ የወራሾች ምላሽ ውድቅ መደረጉን የውሳኔ ሰነዱ ያብራራል፡፡

ከሳሽ ወ/ሮ እታበዛሁ ንጉሴ ባለቤታቸው ባላምባራስ ጤና ፈለቀ በሞግዚትነት የያዙትን ቤት በ80 ሺሕ ብር ሚያዚያ 5 ቀን 1980 ዓ.ም. እንደሸጡላቸው የሚያሳየውን ሰነድ በተፈራረሙበት ዕለት፣ ተቃራኒ የሆነ ውሳኔ በኢሕድሪ የአዲስ አበባ አውራጃ ፍርድ ቤት ተሰጥቷል፡፡ የወ/ሮ እታበዛሁ ባለቤት ባላምባራስ ጤና ፈለቀ ለአውራጃው ፍርድ ቤት ባቀረቡት ማመልከቻ፣ በሞግዚትነት የሚያስተዳድሯቸው የሟች የአቶ አወቀ ንጉሴ ወራሾች በተጠቀሰው ፍርድ ቤት በመ/ቁ 313/73 የተረጋገጠ መሆኑን በመጠቆም፣ ንብረትን በሚመለከት የቤተ ዘመድ ጉባዔ ተሰብስቦ ስለወሰነ፣ ፍርድ ቤቱ የቤተሰቡን ውሳኔ አፅድቆ እንዲያስተላልፍላቸው መጠየቃቸውም በውሳኔ ተጠቁሟል፡፡

የአውራጃው ፍርድ ቤት ሚያዚያ 5 ቀን 1980 ዓ.ም. (ወ/ሮ እታበዛሁ ከባለቤታቸው ባላምባራስ ጤና ቤቱን ገዛሁ ባሉበት ቀን) በሰጠው ውሳኔ፣ በቤተሰብ ጉባዔ የሟች አቶ አወቀ ንጉሴ ንብረት የወራሽ ልጆቻቸው አቶ ዮሴፍ፣ አቶ ዮሐንስ፣ አቶ ያዕቆብና እሌኒ አወቀ መሆኑን በዳኛ ቀጸላ መንግሥቱ ፊርማ አረጋግጧል፡፡

የአቶ አወቀ ወራሾች በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 8ኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት የተጣለባቸውን ውሳኔ ‹‹ለምን?›› በማለት ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰዱት ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 13 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ አፅንቶታል፡፡ ተስፋ ያልቆረጡት ወራሾች ከፍተኛ የሆነ የሕግ ስህተት መፈጸሙን በመግለጽ ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ኅዳር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ ‹‹መሠረታዊ የሕግ ስህተት ተሠርቷል ለማለት አልተቻለም›› ብሎ የመጨረሻውን ውሳኔ ሰጥቶ  ነገሩን ቋጭቶት ነበር፡፡

ተስፋ ያልቆረጡት የአቶ አወቀ ንጉሴ ወራሾች ጉዳዩን በድጋሚ ወደ ፖሊስ በመውሰድ ለወ/ሮ እታበዛሁ የተሰጠው ውክልና መሻሩን፣ የአቶ አወቀ ይዞታ ለማንም ያልተዘዋወረ መሆኑንና ሌሎች ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይላቸው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በማቅረባቸው፣ ማመልከቻቸው ይሁንታ አግኝቶ እንደገና ሊታይ ለግንቦት ወር 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ይዞታውም ለማንም እንዳይተላለፍ፣ እንዳይሸጥና እንዳይለወጥ እግድ መጣሉ ታውቋል፡፡

Read 34646 times