ለብሔር ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ጥናት ሊጀመር ነው

ኢዜአ Mar 25 2014

የብሔር ብሔረሰቦችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅና የልማቱ እኩል ተጠቃሚ ለማድረግ የብሄረሰቦች ፕሮፋይል ጥናት ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፌደሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

በምክር ቤቱ የዴሞክራሲያዊ  አንድነትና የመንግስታት እርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከሪያ ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በቀለ ጥናቱ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን በምክር ቤቱ ያልተወከሉና አዲስ የብሔር ጥያቄ  ያነሱ ህዝቦችን ህጋዊ እውቅና ለመስጠት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፥ ጥናቱ ሲጠናቀቅ አዳዲስ የብሔር ጥያቄዎችን ከመፍታት ባሻገር ብሔር ብሔረሰቦች መብትና ግዴታቸውን በትክከል እንዲወጡና ከመንግስት ማግኘት የሚገባቸውን ልማታዊ ተጠቃሚነት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቋንቋና ባህል አካዳሚ ጥናቱን በጋራ ያከናውናሉ።

የጥናቱን ስራ በቀጣዩ በጀት አመት ለማስጀመር አብይ ኮሚቴ ለማቋቋምና ፕሮጀክቱን የሚመራ አካል ለመመስረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለጥናቱ 80 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ ሲሆን፥ ገንዘቡን የማሰባሰቡ ስራ እየተካሄደ ነው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 75 ብሔር ብሔረሰቦች ህጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው በፌደሬሽን ምክር ቤት ተወክለው ይገኛሉ።

Read 34832 times