እነ አቶ መላኩ ፈንታ ለብይን ተቀጠሩ

Ethiopian Reporter Mar 19 2014

-የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ላይ ምላሽ ሰጠ

በተጠረጠሩበት ከባድ የሙስና ወንጀል ላለፉት አሥር ወራት በእስር ላይ የሚገኙት፣ በሚኒስትር ማዕረግ የቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ

መላኩ ፈንታና ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስን ጨምሮ ታዋቂ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች፣ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞችና አርሶ አደሮች ለብይን ተቀጠሩ፡፡ 

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የመሠረተውን የሙስና ወንጀል ክስ በመመርመር ላይ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ መጋቢት 9 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው፣ ዓቃቤ ሕግ ላቀረበው የሙስና ክስ ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያና ከመቃወሚያው በኋላ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የመቃወሚያ ምላሽ መርምሮና ከተገቢው ሕግ ጋር አገናዝቦ ብይን ለመስጠት ነው፡፡ 

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የሁለቱንም ወገኖች መቃወሚያና የመቃወሚያ መቃወሚያ መርምሮና ከተገቢው ሕግ ጋር አገናዝቦ ብይን ለመስጠት 37 ቀናት እንደሚበቁት በመገመት፣ ለሚያዝያ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች ሰነዶቻቸውን ማለትም ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ክሱንና ማስረጃዎቹን፣ እንዲሁም ተጠርጣሪዎች መቃወሚያቸውን በ‹‹ሶፍት ኮፒ›› በትዕዛዝ ሳይሆን በፈቃደኝነት እንዲሰጡት ጠይቋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አካል ጉዳተኞች (ዓይነ ስውራን) ተጠርጣሪዎች በክሱ የተካተቱ በመሆናቸው፣ ክሱን በአግባቡ ለመከታተል እንዲያስችላቸው በብሬል ተገልብጦ እንዲሰጣቸው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ ‹‹ሶፍትዌር›› በማግኘቱ ወደ ብሬል ገልብጦ ለመስጠት መሆኑን አብራርቷል፡፡ 

Read 33841 times Last modified on Mar 19 2014