በሀረር የደረሰውን የእሳት አደጋ አጋጣሚ በመጠቀም ዝርፊያ የፈፀሙ እስከ 4 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ

ኢዜአ Mar 19 2014

በሐረር ከተማ ሰሞኑን የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ አጋጣሚ በመጠቀም ስርቆት የፈጸሙ አራት ተከሳሾች ላይ አንድ ዓመት ከ10 ወር እስከ አራት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የክልሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

የመጀመሪያ ፍርድ ቤቱ ዳኛ ወይዘሪት ሁዳ አብዱረሓማን እንደገለጹት ተከሳሾቹ ቅጣቱ የተወሰነባቸው በከተማው ሲጋራ ተራ ተብሎ በሚጠራው የገበያ ስፍራ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ከመደብር እቃ ሰርቀው የተገኙ ናቸው።

በደረሰው የእሳት ቃጠሎ ጨለማን ተገን በማድረግ አልባሳትና የኤሌክትሮኒክስ እቃ ሰርቀው መውሰዳቸው በቀረበባቸው ማስረጃና ራሳቸውም በማመናቸው የእስር ቅጣቱ መወሰኑን ገልጸዋል።

የሐረሪ ክልል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መጋቢት 8 ቀን በዋለው ችሎት በሞገስ አለማየሁ ሺበሺ ላይ የአራት ዓመት፣ በቢሶ ኡመር አሊና ዮርዳኖስ ፋሲል ሙሉነህ ላይ እያንዳንዳቸው በሁለት ዓመት፣ በዘመድኩን አስፋው ላይ ደግሞ የአንድ ዓመት ከ10 ወር ፅኑ እስራት የወሰነባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

Read 34776 times