አቢሲኒያ ሎው የሰበር ውሳኔዎችን ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ በመተርጎም (Case Summary) ውሳኔዎቹን ለተጠቃሚዎቹ ለማድረስ የመጨረሻ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 80 ሥር የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን ማናቸውንም የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ስልጣን እንደሚኖረው በግልጽ ይደነግጋል፡፡ የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሠረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ያለበትን በክልል ጉዳዮች የተሰጠ የመጨረሻ ውሳኔ ለማረም በሰበር ችሎት የማየት ስልጣን ይኖረዋል የሚል ተመሳሳይ ድንጋጌ በዚህ አንቀጽ ሥር ይገኛል፡፡
አዋጅ ቁጥር 454/1997
- ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌዴራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳኝነት ይኖረዋል፤
- የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም የተሰጠባቸውን ውሳኔዎች በየደረጃው ላሉ ፍ/ቤቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካል አሳትሞ ያሰራጫል፡፡
የሚሉ ድንጋጌዎችን ይዟል፡፡
በእነዚህ ድንጋጌዎች መሠረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት የተለያየ አስገዳጅ ውሳኔዎችን ሲሰጥና ውሳኔዎችን ሲያሰራጭ ቆይቷል፡፡ ዋና ዓለማውም በፌዴራልና በክልል የሚገኙ ፍርድ ቤቶች በተመሳሳይ ጉዳይ የተለያየ ውሳኔ እንዳይሰጡ እና ወጥ የሆነ የሕግ አተረጓጎም ሥርዓት እንዲኖር ለማስቻል እንደሆነ ከተለያዩ ጽሑፎች ለመረዳት ይቻላል፡፡
ይህንን ጽሑፍ እስከምንጽፍበት ጊዜ ድረስ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተለያዩ የሕግ ክፍሎች አስገዳጅ ውሳኔዎችን የያዙ 19 ቅጾችን በአማርኛ በማሳተም በድረገጽ እና በመጽሐፍ መልኩ ለተጠቃሚዎች አሰራጭቷል፡፡
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ላደረገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና ይገባዋል፡፡ እኛም ለዚህ ሥርዓት መጠናከር የሰበር ሰሚው የሰጣቸውን አስገዳጅ ውሳኔዎች ወደእንግሊዘኛ ቋንቋ በመተርጎም (Case Summary) ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ የመጨረሻ ዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡
ይህንን ማድረግ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት፡-
01የሰበር ውሳኔዎችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን እና ተማሪዎች በቀላሉ እንዲያገኟቸውና የመማር ማስተማር ሂደቱን ለመደገፍ፤
02በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ አማርኛ ቋንቋን ለመረዳት የሚቸገሩ የሕግ ባለሙያዎች የሰበር ውሳኔውን በቀላሉ እንዲረዱ ለማስቻል፤
03የኢትዮጵያ ሕጎችን ከሰበር ውሳኔዎች ጋር አቀናጅተው መረዳት ለሚፈልጉ የውጪ ሀገር ዜጎች ሕጉን ከውሳኔው ጋር በቀላሉ እንዲረዱ ለማስቻል፤ እና
04የተለያዩ ጥናቶች የሚያደርጉ አጥኚዎችና የሕግ ተመራማሪዎች የሰበር ውሳኔዎችን ለመተርጎምና ለማስተርጎም የሚያወጡትን ጊዜና ወጪ ለመቀነስ በማሰብ ነው፡፡
ይህ ሥራ የሰበር ውሳኔዎች ተደራሽነትን ከመጨመሩም በተጨማሪ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የበኩሉን ድርሻ ይጫዋታል ብለን እናምናለን፡፡
በቅርብ ይጠብቁን!
ስለዚህ ሥራ ያለዎትን አስተያየት ቢነግሩን እጅግ ደስ ይለናል!