Print this page

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሱን የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት አዋጅ አፀደቀ

FanaBC Dec 31 2015

አዋጁ ቀደም ሲል በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ይፀድቃል ተብሎ ቢጠበቅም በውስጡ ውስብስብና አከራካሪ ጉዳዮችን በመያዙ ሊዘገይ እንደቻለ ተገልጻል።

በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ በሕዝባዊ ውይይቶች፣ ከተለያዩ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች እንዲሁም በሥራው ከሚሳተፉ አካላት ጋር በተካሄዱ መድረኮች ጠቃሚ ሀሳቦችና ረቂቁን የሚያዳብሩ ሀሳቦች ተገኝተዋል። ከዚህ በመነሳትም 28 የሚደርሱ አንቀጾች መሻሻላቸው ተገልጻል።

አዲሱ የውጭ ሀገራት ስምሪት አዋጅ ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል፣ የዜጎችን መብትም የሚያስከብርና የባለድርሻ አካላትን ሀላፊነት በግልጽ የደነገገ ነው ተብሏል።

አዋጁ ኤጀንሲዎችና አሰሪዎች ለሠራተኞች የሚሰጡት ህጋዊ ሽፋንና ከሠራተኞች የሚቀመጡ መስፈርቶች ተቀምጠውበታል።

1 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ሠራተኞችን ወደ ውጭ ሀገራት የሚልኩ ኤጀንሲዎች ለሠራተኞቹ አስፈላጊውን የደህንነት ሽፋን መግባት እንዳለባቸው በአዋጁ ተደንግጓል።

በአብዛኛው በውጭ ሀገራት በተለያዩ የሥራ መስኮች በተሰማሩ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ችግሮች ከእውቀት እና ክህሎት ክፍተት ጋር የሚገናኙ በመሆኑም በአዲሱ አዋጅ ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ የሚጓዙ ዜጎች ቢያንስ 8 ክፍልን ማጠናቀቅ ይኖርባቸዋል።

እነዚህ ዜጎች ለሦስት ወራት የሚሰለጥኑ ሲሆን፥ ሥልጠናውን ሲያጠናቅቁ የሚሰጣቸውን ፈተናም ማለፍ እንደሚጠበቅባቸው ያመለክታል።

ከዚህ ቀደም ወደ ተለያዩ ሀገራት ያመሩ እና በድጋሚ መሔድ የሚፈልጉ 8 ክፍል ካርድ የሌላቸው ዜጎችም የሚሰጣቸውን ፈተና ማለፍ ይኖርባቸዋል ይላል።

በአዲሱ አዋጅ መሠረት በላኪና ተቀባይ ሀገራት መካከል ባሉ ኤጀንሲዎች መካከል ስምምነት ቢደረግም በዋናነት የሥራ ስምሪቱ ተግባራዊ የሚሆነው ግን በኢትዮጵያና በሌላኛው ተቀባይ ሀገር መካከል የጋራ ስምምነት ሲከናወን ነው።

የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ አዋጁ ራሱ የሚያሠራ በመሆኑ መመሪያና ደንቡን የማውጣቱ ሥራ ጎን ለጎን እየተካሔደ አዋጁን በቀጥታ ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቋል።

በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚከወነው የግንዛቤ ማስፋትና ሕገወጥ ደላሎችን የማስቀጣቱ ሥራ በዚህ ዓመትም ትኩረት እንደሚሰጠውም ገልጿል።

መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያውያን በብዛት ለሥራ ከሚሔዱባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር የዜጎችን መብት ባስጠበቀ መልኩ የሥራ ስምሪት ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወሳል።

Read 39278 times Last modified on Dec 31 2015