ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ለፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በዕጩ ዳኝነት ከተወዳደሩት ውስጥ ለቀጣዩ የቃል ፈተና ያለፉ ተወዳዳሪዎች ይፋ ሆነ፡፡ የቃል ፈተናው ሕዳር 18 እና 19 ቀን 2008 ዓ.ም እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት እንደገለፀው ቀደም ሲል በተሰጠው የጽሑፍ ፈተና የተሻለ ውጤት ያመጡ ተወዳዳሪዎች ለቃል ፈተና እንዲቀርቡ በተሰጣቸው መለያ ቁጥር /ኮድ/ መሠረት ዝርዝራቸው ይፋ ተደርጓል፡፡
በዚሁ መሠረት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኝነት ከቀረቡት ሴት ተወዳዳሪዎች መካከል 60 እና ከ60 በላይ ያመጡ 15 ተወዳዳሪዎት ለቃል ፈተና ያለፉ ሲሆን በተመሳሳይ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኝነት ከቀረቡ ወንድ ተወዳዳሪዎች መካከል 70 እና ከ70 በላይ ውጤት ያመጡ 29 ወንድ ተወዳዳሪዎች ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸው ተረጋግጧል፡፡ በተመሳሳይ ለፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዕጩ ዳኝነት ከቀረቡት ሴት ተወዳዳሪዎች መካከል 70 እና ከዚያ በላይ ውጤት ያመጡ 51 ሴት ተወዳዳሪዎች ከወንድ ተወዳዳሪዎች መካከል ደግሞ 80 እና ከዚያ በላይ ያመጡ 76 ወንድ ተወዳዳሪዎች ለቃል ፈተና ማለፋቸው ይፋ ተደርጓል፡፡
ለቃል ፈተና ያለፉ ተወዳዳሪዎችን በተመለከተ መረጃ ፈላጊዎች በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ስልክ ቁጥር 0111 56 56 84 ወይም 011156 56 85 በመደወል መረጃ ማግኘት እንደሚችሉ ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡