Print this page

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (የኢሕባሴማ) ጠቅላላ ጉባኤ ተካሄደ

EWLA Apr 01 2015

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (ኢሕባሴማ) ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት በቀረበው ሪፖርት 2014 .. ሰባት ሺህ ለሚደርሱ ሴቶች ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት አበረከተ፡፡

ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 19 ቀን 2007 . በኢትዮጵያ ሆቴል በተካሄደው ጉባኤ የማኅበሩ ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ወይዘሮ ዜናዬ ታደሠ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት ማኅበሩ ባለፈው አንድ ዓመት 6,997 ለሚሆኑ ሴቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አበርክቷል፡፡

ማኅበሩ በዚሁ ጠቅላላ ጉባኤው የሥራ አፈፃፀምና የኦዲት ሪፖርት እንዲሁም 2015 .. የዕቅድ ክለሳ ከማዳመጡ በላይ የቦርድ አባላት ምርጫ አድርጓል፤ በቦርድ የፀደቀው የአዳዲስ አባላት ዝርዝርም ቀርቦለታል፡፡

ነፃ የሕግ ምክር አገልግሎት ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል የፍቺ፣ የልጆች ቀለብና አስተዳደግ፤ የንብረት ክፍፍል፣ የሠራተኛና አሠሪ ጉዳይ፣ የውርስ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ድብደባ፣ የኣካል ጉዳት ማድረስ፤ ግድያና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡

ማኅበሩ ፈቃደኛ የሆኑ ጠበቆችን አግኝቶ እጅግ ዉስብስብ እና ባለጉዳዮቹም /ቤት ቆመዉ ለማስረዳት የአቅምም ሆነ የገንዘብ ችግር ላለባቸው 22 ሴቶች ነፃ የጥብቅና አገልግሎት መስጠቱን የገለፁት የሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተሯ 1,600 (አንድ ሺህ ስድስት መቶ) የሚበልጡ የባል እና የሚስት፤ የሰራተኛ እና አሰሪ፤ የዉርስ፤ የቀለብ፣ የልጅ አስተዳደግ እና ሌሎችም ጉዳዮች በዕርቅ እንዲያልቁ መደረጉን አመልክተዋል፡፡እንዲሁም 52 ለሚሆኑ ሴቶች የዳኝነት፣ የቴምብርና የትራንስፖርት ወጪዎች መሸፈኑንም አስታውቀዋል፡፡

የሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተሯ እንዳሉት በአዲስ አበባ በሚገኘው የማህበሩ ዋና /ቤት አሥራ አንድ በጎ ፈቃደኛ የህግ አማካሪዎች ደግሞ 2,020 (ሁለት ሺህ ሃያ) ሰዓት ነፃ የሕግ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡

ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕፃናት ፍትህ ፕሮጀክት /ቤት ጋር በመተባበር 65 በጎፈቃደኞች ከአውሮፓ ኅብረት ሲቪል ሶሳይቲ ፈንድ 2 በተገኘ ገንዘብ ድጋፍ ደግሞ 72 በጎፈቃደኞች የሚሠጡትን የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት የሚያጎለብት የፓራ ሌጋል (የመሠረታዊ ሕግ ሥልጠና) መሰጠቱን አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም በሴቶች መብት አከባበር አንጻር የፍትህ አካላትን አቅም የሚገነባ ሥልጠና 90 ዳኞችና ዓቃብያነ ሕግ ሠጥቷል፡፡

ማህበሩ ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ጋር ያለዉን ግንኙነት አጠናክሮ በመቀጠሉ በማህበሩ ባለሙያዎች ስልጠና እንዲሰጥላቸዉ በርካታ መስሪያ ቤቶች ጠይቀዉ በተለያየ ጊዜ ስለሴቶች መብትና ስለጾታዊ ጥቃት በአጠቃላይ 900 ለሚሆኑ የመንግስት /ቤት ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥቶአል፡፡ የማኅበሩ በጎ ፈቃደኞች የሠጡት ይኸው ሥልጠና በአጠቃላይ 32 ሰዓት ያህል የፈጀ ነው፡፡ 
ሴቶች ራሳቸውን ወክለው በፍርድ ቤት መከራከር የሚችሉበትን ትምህርት ለመሥጠት በተደረገው ጥረት 222 ሴቶች ሠልጥነዋል፡፡

በአሶሳ 80 ለሚሆኑ ሴት ተማሪዎችና መምህራን በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ዙሪያ ሥልጠና በመሠጠቱ ከአካባቢው ጾታዊ ጥቃትን የሚመለከቱ ሪፖርቶች መምጣት መጀመራቸውንም ተናግረዋል፡፡

ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ ለማስጨበጥ በመገናኛ ብዙሃን ልዩ ልዩ ፕሮግራሞችንና ድራማዎችን የማስተላለፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ዜናዬ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር በመተባበር በአዲስ ዘመንና በሪፖርተር ጋዜጦች ላይ ፅሑፎችን ለማውጣት ማኅበሩ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ማህበሩ በሴቶች መብት አከባበር እና በጾታዊ ጥቃት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ እንደሆነም ተገልጾአል፡፡

ከሕግ ትምህርት ቤቶች ጋር ባለ ግንኙነት 18 በመመረቂያ ዓመት ላይ ያሉና 10 የተመረቁ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል፡፡

በአጠቃላይ ማህበሩ በሪፖርት ዓመቱ የሰው ኃይሉ አድጎ 31 ሠራተኞች መድረሳቸው እና የገንዘብ አቅሙ ያደገ በመሆኑ የሥራ አፈፃፀሙ እየተሻሻለ መምጣቱን በያዝነው ዓመት ደግሞ የማህበሩን አባላት ተሳታፊነት ለመጨመር እና የገጽታ ግንባታ ላይ ጠንክሮ የሚሠራ መሆኑን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

ስለሪፖርቶቹ አንዳንድ ማብራሪያዎች ከተሰጡ በኋላ የሥራና የሂሳብ ሪፖርቶቹ በጠቅላላ ጉባኤው ጸድቀዋል፡፡

ቀጥሎም 2015 ዕቅድ እና በጀት ወይዘሮ ዜናዬ ያቀረቡ ሲሆን ዕቅዱ በጠቅላላ ጉባኤው ፀድቆአል፡፡

እንዲሁም አስመራጭ ኮሚቴ ከተሰየመ በኋላ ጊዜአቸውን ከነሐሴ ወር 2007 ጀምሮ በሚጨርሱ ሁለት የቦርድ አባላት እና ወደውጪ በሄዱ አንድ አባል ምትክ ስድስት መደበኛ አባል ሴቶች ተጠቁመው ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ ሦስቱ ለቦርድ አባልነት ተመርጠዋል፡፡

 

የማኀበሩ ቦርድ ያፀደቃቸው አዳዲስ አባላት ዝርዝርም ለጉባኤው ቀርቧል፡፡

Read 36129 times