Print this page

ፀረ ሙስና ኮሚሽንን የሚያገዝፉት አዋጆች በፓርላማው ፀደቁ

EthiopianReporter Jan 15 2015

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት ካለው ሙስናን የመከላከል አቅም በእጅጉ የገዘፈ ኃላፊነት የሚሰጡትን ሦስት ረቂቅ አዋጆች ፓርላማው ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. አፀደቀ፡፡

የፀደቁት አዋጆች የሙስና ወንጀልን ለመደንገግ፣ የፀረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና ማስረጃ ሕግ አዋጅን ለማሻሻል፣ እንዲሁም የፌዴራል ሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ሲሆኑ፣ እንደቅደም ተከተላቸው አዋጅ ቁጥር 881/2007፣ 882/2007 እና 883/2007 ሆነው ፀድቀዋል፡፡ 

የሙስና ወንጀሎችን የሚደነግገው አዋጅ በወንጀል ሕጉ በሙስና ወንጀልነት የተለዩትን በማጠቃለል በፀረ ሙስና ሕጉ ውስጥ እንዲካተቱ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አዳዲስ የሙስና ወንጀሎችንም ለይቶ አካቷል፡፡ 

ለአብነት ያህልም ወታደራዊ ሚስጥርን ስለመግለጽ በወንጀል ሕጉ በወንጀልነት ቢደነገግም፣ ሚስጥሩ የተገለጸው ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት በሚል እሳቤ ሊሆን ስለሚችል፣ ወታደራዊ ሚስጥር የሚለውን መግለጽ ሳያስፈልግ የሥራ ሚስጥር በሚል ሐረግ ሥር የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን እንዲካተቱ አድርጓል፡፡ 

በተጨማሪም የሕዝብ ጥቅም ያለባቸው የግል ድርጅቶች ውስጥ የሚፈጸሙ ሙስናዎችንም በሙስና ወንጀልነት አካቷል፡፡ በዚህም መሠረት ሕዝባዊ ድርጅት በሚል ስያሜ ከሃይማኖት፣ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም እንደ እድር ያሉ ሕዝባዊ ገንዘብና ንብረት የሚያስተዳድሩ ተቋማት ውጪ ያሉ ከሕዝብ የተሰበሰበ ወይም ለሕዝባዊ ጥቅም ታስቦ የተሰበሰበ አግባብነት ያለው ኩባንያ (በሕዝብ የአክሲዮን መዋጮ የተቋቋመ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያና እንደዚህ ዓይነቱ ኩባንያ በሽርክና የሚመሠርተው ሌላ ድርጅት) እንዲካተቱ አድርጓል፡፡

ይህም ማለት ለሕዝብ ጥቅም የተቋቋሙ ኢንዶውመንቶች ማለትም እንደ ኤፈርትና ጥረት ያሉ የትግራይና የአማራ ክልል ኢንዶውመንት ኩባንያዎች ውስጥ የሚፈጸም ሙስናን ኮሚሽኑ የማየት ሥልጣን አለው፡፡ 

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያን የሚያሻሻለው አዋጅ ደግሞ፣ ኮሚሽኑ ወንጀልን ከክስ በመለስ እንዲቋጭ ወይም ሙሰኞች በሙስና ያገኙትን ሀብት እንዲመልሱ በማድረግ ክስ እንዳይመሠረት ወይም እንዲቋጭ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡   

ይህንን ማድረግ ያስፈለገው ለምርመራ የሚወጣን ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ለማዳን እንዲሁም በክርክር ሊመለስ የማይችል በሙስና የተመዘበረ ሀብትን ለማስመለስ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

ይህንን ተግባር ለመፈጸምም የፀደቀው የማቋቋሚያ አዋጁ ማሻሻያ ከክስ በመለስ ሊታረሙ ይችላሉ የሚላቸውን የሙስና ወንጀሎች ዝርዝርና አፈጻጸም፣ እንዲሁም ይኼንን ለማድረግ ስለሚከተለው አካሄድ ራሱ ኮሚሽኑ በመመርያ እንዲወስን አዋጁ ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ 

Read 39146 times