Print this page

በሽብር የተከሰሱ የተቃዋሚ አመራሮች፤ በማረሚያ ቤት ንብረት ተወስዶብናል አሉ

addisadmassnews Dec 29 2014

ማረሚያ ቤት ምላሽ እንዲሰጥ ፍ/ቤት አዝዟል

“የግንቦት 7 አባል በመሆን በሽብር ድርጊቶች ተሳትፈዋል” በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የአንድነት፣ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲ አመራሮች፤ ሌሊት በማረሚያ ቤት በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ገንዘብን ጨምሮ የተለያዩ ንብረቶች እንደተወሰደባቸው ባለፈው ረቡዕ ለፍ/ቤት አመልክተዋል፡፡ በእነ ዘላለም ወርቅ አገኘው መዝገብ የተከሰሱት የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሀብታሙ አያሌው፣ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ም/ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አቶ የሸዋስ አሰፋ እና የአረና ፓርቲ አመራር አባል አቶ አብርሃ ደስታና ሌሎች ተከሳሾች በጠበቃቸው በኩል ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፤ ታህሳስ 12 ለ 13 አጥቢያ ከሌሊቱ 8 ሰዓት እስከ ቀኑ 5 ሰዓት በማረሚያ ቤት ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎ፤ የማስታወሻ ደብተራቸው፣ ገንዘብና ሌሎች ሰነዶች እንደተወሰደባቸው ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡

 

ፈታሾቹ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ሳይሆኑ በፊት ይመረምሯቸው የነበሩ ፖሊሶችና የደህንነት አባላት እንደሆኑም ጠቁመዋል፡፡ በተለይ የማስታወሻ ደብተራቸው እንደተወሰደባቸው አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት ጠበቃው ተማም አባቡልጋ፤ ተከሳሾቹ ለቀጣይ ክርክር ያዘጋጇቸውን ነጥቦች ያሰፈሩባቸው በመሆኑ በቀረበባቸው ክስ ላይ ለመከራከር እንደሚቸገሩና የስነ ልቦና ጫና እንደሚያሳድርባቸው ለፍ/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ “ምርመራ የሚፈቀደው ከጠዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽት 2 ሰዓት ሆኖ ሳለ በሌሊት መደረጉ ህግ የጣሰ ተግባር ነው፤ ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀማቸው ህጋዊ እርምጃ ይወሰድልን” በማለት ለፍ/ቤቱ ያመለከቱት ጠበቃው፤ “ደንበኞቼ የማረሚያ ቤት ቆይታቸው አደጋ ላይ የወደቀ በመሆኑ የደህንነት ስጋት አለብኝ፤ በዋስትና ይለቀቁ አሊያም ከወህኒ ቤቱ በተለየ ቦታ እንዲቀመጡ ይደረግ” ሲሉ አጠይቀዋል፡፡ 

 

አቃቤ ህግ፤ ለተከሳሾቹ አቤቱታ በሰጠው ምላሽ፤ ጠበቃ ተማም አባቡልጋ የብዙ ታራሚዎችን ደህንነት በማስጠበቅ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለን ማረሚያ ቤት የታራሚዎችን ደህንነት የመጠበቅ ብቃት የለውም ማለታቸው አግባብነት እንደሌለው ጠቁሞ፣ ይህን መነሻ አድርጎ ዋስትና መጠየቁም ተቀባይነት የለውም ሲል ተቃውሟል፡፡ ፖሊስ የብርበራ ትዕዛዝ ይዞ በማረሚያ ቤት ፍተሻ ማካሄድ እንደሚችልም አቃቤ ህግ አስረድቷል፡፡ ፍ/ቤቱ የቀረበውን አቤቱታ መርምሮ ብይን ለመስጠት በአቤቱታው ላይ የማረሚያ ቤቱ ምላሽ እንደሚያስፈልግ ጠቅሶ፣ በቀጣይ ቀጠሮ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ጉዳዩ ተፈፅሟል አልተፈፀመም በሚለው ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ 

 

ፍ/ቤቱ በተጨማሪም ለጠበቃ ተማም አባቡልጋ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ “ተቋምን ብቃት የለውም ብሎ መግለፅ አግባብ አይደለም፣ በማስረጃ አረጋግጡ ቢባሉ ሊከብድት ይችላል” ያለው ፍ/ቤቱ፤ ጠበቃው ከዚህ አይነት አገላለፅ እንዲታረሙ ተግሳፅ ሰጥቷል፡፡ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ አቶ ሃብታሙ አያሌው “የምናገረው አለኝ” በማለት “በማረሚያ ቤቱ ደህንነት እየተሰማኝ አይደለም፤ ፍ/ቤቱ ደህንነቴን ያስከብር” ሲሉ አቤቱታቸውን በቃል ያቀረቡ ሲሆን ፍ/ቤቱም “ድርጊቱ ስለመፈጸሙ በማስረጃ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፤ ጉዳዩ በቀጣይ ቀጠሮ ብይን ይሰጥበታል” ሲል መልሷል፡፡ መዝገቡንም ለታህሳስ 24 ቀጥሯል፡፡ 

Read 35183 times