Print this page

በሽብር የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው

FanaBC Dec 25 2014

መቀመጫውን ኤርትራ ውስጥ ያደረገውና ራሱን የትግራይ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ በማለት የሚጠራው የሽብር ድርጅት አባል በመሆን በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የዝርፊያ፣ የእገታና የግድያ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ ሰባት ተከሳሾች ክስ ተመሰረተባቸው።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን ተመልክቶታል።

ተከሳሾቹ 1ኛ ግርማ ልዑል አረጋይ፣ 2ኛ ሙቀት ንጉስ፣ 3ኛ ሀይለ በላይ ባህታ፣ 4ኛ ተክሏት ሀጎስ፣ 5ኛ ካህሳይ ኪሮስ ካህሳይ፣ 6ኛ ሃይላይ ግርማ እና 7ኛ አልጋ ግርማይ ወልደየሱስ ናቸው።

የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል ድርጊት ተካፋይ በመሆን፣ የእያንዳንዳቸውን ድርጊት የጋራ ውጤት በማድረግ ፣ፖለቲካዊ አላማን ለማራመድ በማሰብ፣ በመንግስት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በቀበሌ ሚሊሻዎችና ሲቪል ዜጎች ላይ የግድያና የእገታ ወንጀል በሚፈፅመውና ራሱን የትግራይ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ት.ህ.ዲ.ን) ብሎ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን ውስጥ አባል ሆነው ሲንቀሳቀሱ ነበር።

በአሸባሪ ቡድኑ ውስጥ በአባልነት በተዋጊነት፣ በጋንታ መሪነት እና በስለላ ባለሙያነት ተመድበው፤ ስለ ጦር መሳሪያ አፈታት፣ አገጣጠምና አጠቃቀም፣ ስለመሬት አቀማመጥ ጥናት፣ የጠላትን የሰው ሃይል ብዛት ስለመገመትና ስለውጊያ ስልቶች በሻእቢያ የደህንነት ሃላፊዎችና የትህዲን አመራሮች አማካኝነት ተከታታይ  ስልጠናም አግኝተዋል።

በዚህም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት የሽብር ድርጊቶችን ፈፅመዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ።

1ኛ ተከሳሽ በ1996 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ በፃረና ግንባር በኩል ወደ ኤርትራ ሀዕና የሚባል የአሸባሪዎች ማሰልጠኛ ሄዶ የትግራይ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ አባል በመሆኑ፣ ከ70 በላይ የሚሆኑ ከሌሎች የምልምል አባላት ጋር በመሆን አሽገላ ተብሎ በሚታወቀው የቡድኑ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ወታደራዊ ስልጠና ወስዷል።

በ2006 ዓ.ም ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ጥዕላይ ዓዲያቦ ወረዳ የሚገኘውን የፖሊስ ጣቢያን በማጥቃት የፖሊስ አባላትን እንዲገድሉ፣ የጦር መሳሪያ እንዲዘርፉና የህግ እስረኛ እንዲያስለቅቁ ተልዕኮ የተቀበለ በመሆኑ፣ ነሃሴ 19፣ ቀን 2006 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የፖሊስ አባላትን ለመግደል፣ የጦር መሳሪያ ለመዝረፍና የህግ እስረኞችን ለማስለቀቅ ሲሞክር በአካባቢው የጸጥታ ሀይሎች በቁጥጥር ስር ውሏል፣ በዚህም ክስ ተመስርቶበታል።

2ኛ ተከሳሽ በ1998 ዓ.ም ወደ ኤርትራ በመሄድ ሃዕና በተባለ የአሸባሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም በመግባትና የሽብር ቡድኑ አባል በመሆን ወታደራዊ ስልጠና ወስዷል።

ታህሳስ 16፣ 2004 ዓ.ም ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ገደማ በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን ጥዕላይ ዓዶያቦ ወረዳ ቦታው ዓዲ ገርገስ በመባል በሚታወቅ አካባቢ በጠንካራ ሚሊሻነት ይታወቅ የነበረውን ሟች ክፍሌ ታደሰን ሶስት ማንነታቸው ያልታወቁ ተጠርጣሪ አሸባሪዎችን አስከትሎ በመግባት በተኛበት በአምስት ጥይት ደብድቦ ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጓል።

3ኛ ተከሳሽ በ2001 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ በኢትዮጵያ አዲጋሹ በተባለ ቦታ በመከላከያ ሰራዊት ላይ ተኩሶ ወደ ኤርትራ ተመልሶ ይገባል።

በ2004 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በስም ካልታወቁ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር በመሆን ትግራይ ክልል ዕቁብ ስላሴ በሚባል አካባቢ የጦር መሳሪያ ታጥቆ በስም ያልታወቁ ሁለት ሴቶችንና ስምንት ወንዶችን በድምሩ አስር ሲቪል ዜጎችን ወደ ኤርትራ በመውሰድ ለሽብር ቡድኑ አስረክቧል።

ከአራት እስከ ሰባት ያሉት ተከሳሾችም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ ያቀረበባቸው ክስ ተነቦላቸዋል።

ፍርድ ቤቱ ለተከሶቹ ተከላካይ ጠበቆች ይመደብላቸው ብሏል።

ተከሳሾቹ የክስ መቃወሚያ ካላቸው እንዲያቀርቡ ለጥር 5፣ 2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።

Read 35428 times