Print this page

ቤኒሻንጉል ጉሙዝን ለመገንጠል የሽብርተኝነት ድርጊት ፈጽመዋል በሚል የተጠረጠሩ ተከሰሱ

EthiopianReporter Dec 17 2014

-የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማስተጓጐል ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ተጠቁሟል በታምሩ ጽጌ

በኤርትራ መንግሥት ድጋፍ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሥልጠናዎችን በመውሰድ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድና በመዘጋጀት፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ለመገንጠል የሽብርተኝነት ድርጊት ፈጽመዋል በሚል በተጠረጠሩ አሥር የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ታኅሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተ፡፡

በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ተሰናድቶ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች አብዱልዋሀብ መኸዲ (በሌለበት)፣ አብዱራህማን ናስር (በሌለበት)፣ ኩርፊል ጅማ፣ ያሲር ጃባላ፣ ኢማም አብዱራዛቅ፣ ደፈአላ መሐመድ፣ አደም በደዊ፣ ሙድወኪል ከማል፣ አልፋዮድ በዳናና አዜን አህመድ ናቸው፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ በሰው ሕይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች ማድረሳቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት፣ የአገሪቱን መሠረታዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ ሕገ መንግሥታዊና ማኅበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ ራሱን የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጭ ንቅናቄ (ቤሕነን) ብሎ በሚጠራው በሽብር ተግባር ላይ በተሰማራ ድርጅት ውስጥ ሆነው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ 

አብዱልዋሀብ መሀዲ የተባለው ተጠርጣሪ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ቤሕነን የሚባለውን ሕገወጥ ድርጅት በማቋቋምና በሊቀመንበርነት ከመምራቱም በተጨማሪ፣ ኤርትራ ውስጥ ሆኖ የተለያዩ የፖለቲካ ሥልጠናዎችንና የሽብር ተልዕኮዎችን ሲሰጥ መቆየቱ በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ተጠርጣሪው ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ኤርትራ ውስጥ በሚገኘውና ‹‹ሀሆና›› በሚባለው ወታደራዊ ማሠልጠኛ በመግባት፣ ከሁለት እስከ ስድስት ወራት ሥልጠና መውሰዳቸው በክሱ ተገልጿል፡፡ የመሣሪያዎች አጠቃቀም፣ የወታደራዊ አካል ብቃትና የፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂ ማጥመድ ሥልጠናዎችን መውሰዳቸውንም ክሱ አክሏል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ሸርቆሌና አልቤሮ በተባሉ አካባቢዎች በሚገኘው፣ ዱምድ አቤ ተብሎ በሚጠራ መንገድ ላይ ፀረ ተሽከርካሪ ፈንጂዎችን በማጥመዳቸው፣ ጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም. 12 ሰዎችን ጭኖ ከሸርቆሌ ወደ አስቢሮ ይጓዝ የነበረ ሚኒባስ ላይ የፍንዳታ ጉዳት በማድረስ ሦስት ሰዎች ወዲያውኑ እንዲሞቱና በዘጠኝ ተሳፋሪዎች ላይ ከባድ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

የክልሉን መንገዶች በማጥናትና ፈንጂዎችን በማጥመድ ከፍተኛ አደጋ እንዲደርስና የንፁኃን ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ተጠርጣሪዎቹ ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎችን በማስቆም፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላትንና ሌሎች ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ ከሁለተኛው ተጠርጣሪ አብዱራህማን ናስር ከሚኖርበት ሰሜን ሱዳን በኩል በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ደማዚን አሻራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በመገናኘት፣ የተለያዩ የሽብር ተልዕኮ ማስፈጸሚያ የጦር መሣሪያዎችን፣ ለምግብና የተለያዩ ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ ይቀባበሉ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ በሚያዚያ ወር 2006 ዓ.ም. ወደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሚወሰደውን መንገድ በድንጋይ በመዝጋት፣ ከአሶሳ ከተማ ወደ ግድቡ 28 ሰዎችን ጭኖ ይጓዝ የነበረ የመከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪን በማስቆምና በማስወረድ፣ በአካባቢው በነበረ ጫካ ውስጥ በማስገባት፣ ሦስተኛው ተጠርጣሪ በጥይት ደብድቦ እንደገደላቸውና የያዙትን ገንዘብ እንደወሰዱ ክሱ ይገልጻል፡፡ ተሽከርካሪውንም ከራሱ ቤንዚን ስበው በማርከፍከፍ እንዳቃጠሉት ክሱ ያብራራል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹ የሽብር ተልዕኮ ለመፈጸም ቆርጠው በመነሳታቸው በተለያዩ ጊዜያት መንገድ በመዝጋትና ተሽከርካሪዎችን በማስቆም፣ ተሳፋሪዎችን በጥይት ደብድበው በመግደል፣ እንዲሁም የተወሰኑ ሰዎችን እጃቸውን ወደኋላ በማሰር፣ በድንጋይና በዱላ በመደብደብና አንገታቸውን በመቆልመም የግድያ ወንጀል መፈጸማቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 

የመከላከያ ሠራዊት በደረሰው ጥቆማ መሠረት ባደረገው ከበባ ለ30 ደቂቃ ያህል ተኩስ ከተለዋወጡ በኋላ ሁለት ተጠርጣሪዎች ተገድለው፣ ሌሎቹ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በተጠረጠሩበት የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡   

Read 35415 times