Print this page

ከእነአቶ መላኩ ፈንታ ጋር በሙስና ተጠርጥረው የነበሩት ነጋዴ ነፃ ወጡ

EthiopianReporter Dec 03 2014

በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረውና ክስ ተመሥርቶባቸው በክርክር ላይ ከሚገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፈንታና ከምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ገብረዋሀድ ወልደጊዮርጊስ ጋር በመመሳጠር የሙስናውን ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት ነጋዴ በነፃ ተሰናበቱ፡፡

በነፃ የተሰናበቱት ነጋዴ አቶ ማሞ ኪሮስ ይባላሉ፡፡ አቶ መላኩ ፈንታና አቶ ገብረዋሀድ በተጠረጠሩበት ወንጀል በቁጥጥር ሥር በዋሉ በሳምንቱ ግንቦት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. አቶ ማሞም በቁጥጥር ሥር ውለው ታስረው ከርመዋል፡፡ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ ኃላፊዎች ከአቶ መላኩና አቶ ገብረዋሀድ ጋር በመመሳጠር የተለያዩ አክሲዮን ማኅበራት ማቋቋማቸውንና ከቀረጥ ነፃ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን ማስገባታቸውን፣ በወቅቱ ጊዜ ቀጠሮው ይቀርብ በነበረበት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን ሲገልጽ ከርሟል፡፡

የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክሱን ጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበበት ወቅት፣ አቶ ማሞ ኪሮስን ከእነ አቶ መላኩ ጋር በአንድ ላይ አልከሰሳቸውም፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ፣ አቶ ማሞ ኪሮስን የከሰሳቸው ተጠርጥረው በእስር ላይ በነበሩበት ጊዜ ያቀርብባቸው በነበረው ከፍተኛ የሙስና ወንጀል ሳይሆን፣ መንግሥታዊ ሰነዶችን በሐሰተኛ መንገድ ማዘጋጀትና ወደ ሐሰተኛ ሰነድ ለውጦ መገልገል የሙስና ወንጀል ነው፡፡

አቶ ማሞ የሌላውን ሰው መብትና ጥቅም ለመጉዳት እንዲሁም ለሌላ ሰው ተገቢ ያልሆነ መብትና ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ የከተማ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሲሠሩ፣ ከቀረጥና ታክስ ነፃ በቅድሚያ መገዛት ያለባቸውን ተሽከርካሪዎች፣ የኮንክሪት ሚክሰርና ቫይቭሬተር በድርጅቱ ስም በሐሰተኛ ሰነድ መግዛታቸውን የተመሠረተባቸው ክስ ይገልጻል፡፡ ነጋዴው ኤልያስ እሸቴ ወልደማርያም አጠቃላይ አስመጪ ድርጅት የገዙ ማስመሰላቸውንና ሐሰተኛ የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ እንዲዘጋጅላቸው ማድረጋቸውን፣ ደረሰኙን ተጠቅመው፣ በከተማ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም ገልባጭ መኪናና ሐይሉክስ ፒካፕ መኪና ከቀረጥ ነፃ ማስገባታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሦስት ምስክሮችንና አራት የሰነድ ማስረጃዎችን በአቶ ማሞ ላይ አቅርቦ ነበር፡፡ ክሱ ከእነአቶ መላኩ ፈንታ ተለይቶ ለብቻቸው ሲከሰሱ፣ ክርክሩን ሲያዳምጥ የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 18ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የቀረበውን ክስ ተመልክቶ፣ ተጠርጣሪ አቶ ማሞ ጥቅምት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ችሎት ቀርበው ማንነታቸውን ካረጋገጠ በኋላ ክሱን አንብቦላቸው፣ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግም የመልስ መልስ ሰጥቶ ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የአቶ ማሞን የክስ መቃወሚያ ውድቅ በማድረግ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተው፣ የዓቃቤ ሕግ ሦስት ምስክሮች እንዲሰሙ አድርጓል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ፣ ተሽከርካሪዎቹ የተገዙበትን የገንዘብ መጠንና ክሱ በተመሠረተበት ወቅት ያላቸውን የዋጋ መጠን በንጽጽር የሚገልጹ ማስረጃዎች፣ የተሽከርካሪዎቹን የሻንሲ ቁጥርና ተያያዥ ሰነዶችን አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ የሰው ማስረጃንና የሰነድ ማስረጃዎችን መርምሮ በሰጠው ብይን፣ አቶ ማሞ ኪሮስ መከሰስ ያለባቸው በሙስና ወንጀል ሳይሆን፣ በወንጀል ሕግ ቁጥር 696 (ሐ) ማለትም በከባድ አታላይነት መሆኑን ገልጾ፣ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 142 (1) ማለትም፣ ‹‹ተከሳሹ በቀረበበት ማስረጃ መሠረት የተመሰከረበት ከሆነና የተበደለው ወገን ያቀረባቸው ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ መከላከያውን እንዲጀምር ቃሉን መስጠትና የመከላከያ ምስክሮቹን ማቅረብ ይችላል፤›› በሚለው የሕግ ድንጋጌ መሠረት እንዲከላከሉ የካቲት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ብይን ሰጥቷል፡፡ የተከሰሱበት የሕግ አንቀጽ በመለወጡ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆላቸው፣ ከአሥር ወራት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ አቶ ማሞ በዋስ ወጥተው መከላከያቸውን አቅርበዋል፡፡

ነጋዴው፣ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 142 (3) መሠረት ማለትም ‹‹ተከሳሹ ቃሉን መስጠት የፈቀደ እንደሆነ መከላከያ ምስክሮች ከማቅረቡ በፊት የተከሳሽነት ቃሉን ይሰጣል፤›› በሚለው የሕግ ድንጋጌ መሠረት ቃላቸውን አስመዝግበዋል፡፡ አቶ ማሞ በሰጡት የተከሳሽነት ቃል፣ የተጠረጠሩበትን የተሽከርካሪዎች ግዥን በሚመለከት መቼ፣ እንዴትና በምን ሁኔታ ከነዋጋቸውና የሰነድ ማስረጃዎቻቸው ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ስለከተማ ኮንስትራክሽን የሥራ ሁኔታና ከሚመለከተው አካል ስለተሰጠ የተቋራጭነት ፈቃድ፣ ሰርተፍኬትና ሌሎች ዝርዝር ማስረጃዎችን በመተንተን ተናግረው ማረጋገጫ ሰነዶችን ጭምር ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል፡፡ የሰው ምስክር አላቀረቡም፡፡

ፍርድ ቤቱ፣ አቶ ማሞ የዓቃቤ ሕግን ክስና ማስረጃ ‹‹ተከላክለዋል ወይስ አልተከላከሉም?›› የሚል ጭብጥ በመያዝ መርምሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ የቀረበውን ማስረጃ አቶ ማሞ አንድ በአንድ በጥሩ ሁኔታ ማስተባበል መቻላቸውን በዝርዝር አስረድቶ፣ ከቀረበባቸው ክስ ከኅዳር 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በነፃ  መሰናበታቸውን በመግለጽ በሦስት ዳኞች ፊርማ በሙሉ ድምፅ ፍርድ ሰጥቷል፡፡

Read 35269 times