Print this page

በቡድን በመድፈር ተማሪዋን ለሞት ዳርገዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ድርጊቱን ክደው ተከራከሩ

EthiopianReporter Nov 24 2014

- ፖሊስ ለተጨማሪ ምርመራ የጠየቀው ጊዜ ተፈቀደለት

ከትምህርት ቤት ወደ ቤቷ ለመሄድ በተሳፈረችበት ሚኒባስ ታክሲ ተገዳ ከተወሰደች በኋላ፣ በደረሰባት በቡድን የመደፈር ጥቃት ምክንያት ሕይወቷ ያለፈው ተማሪ ሃና ላላንጐ ጉዳይ እያነጋገረ ነው፡፡

ድርጊቱን ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ አምስት ተጠርጣሪዎች፣ ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ በመካድ ኅዳር 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ተከራክረዋል፡፡

አንደኛ ተጠርጣሪና የድርጊቱ አቀነባባሪ መሆኑ የተገመተው ግለሰብ፣ ሟች ተማሪ ሃና ቀደም ሲል ጉዳት ደርሶባት እንደነበር ለፍርድ ቤት የተናገረ ቢሆንም፣ የት፣ በማንና እንዴት ጉዳቱ እንደደረሰባት አላስረዳም፡፡ ድርጊቱን መፈጸማቸውን ለጓደኞቻቸው ሲያወሩ መስማቱን በመግለጽ ለፖሊስ መጠቆም ቢችልም፣ ፖሊስ ሊቀበለው አለመቻሉን በማስረዳት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡ 

የታክሲ ሾፌር መሆኑን የገለጸውና ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ያዋሉት ‹‹ሰው ገጭተኸል›› በማለት መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ያስረዳው ሁለተኛው ተጠርጣሪ፣ ፖሊስ ጣቢያ ከተወሰደ በኋላ በሟች ሃና ላይ ደርሷል የተባለውን የቡድን ድርጊት አብሮ መፈጸሙ እንደተነገረው እያነባ አስረድቷል፡፡ ባለቤቱ ዓረብ አገር መሆኗንና አንድ ልጅ እንዳለው የገለጸው ተጠርጣሪው፣ እናቱ ደካማና ሕመምተኛ በመሆናቸው ማንም የሚጠይቀው እንደሌለ በማስረዳት፣ በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉና ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች እንዲያዙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት አመልክቷል፡፡ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በጨለማ ቤት ውስጥ ታስሮ በጨለማ እንዲመገብና ቀዝቃዛ ሲሚንቶ ላይ እንዲተኛ በመደረጉ ከፍተኛ በደል እየደረሰበት መሆኑንም አሳውቋል፡፡ 

ጉዳት የደረሰባትና ሕይወቷ ያለፈው ሃና በሕይወት እያለች ተይዞ ቢሆን ምርጫው እንደነበር የተናገረው ሌላው ተጠርጣሪ፣ አይታው ‹‹አለበት ወይም የለበትም›› ብትል ጥሩ እንደነበር ተመኝቶ፣ በማያውቀውና በሌለበት ሁኔታ ምንም የሚያውቀው ነገር ሳይኖር ተይዞ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡

አራተኛው ተጠርጣሪ ‹‹የማውቀው ነገር የለም፤ ቀጠቀጡኝና አመንኩ›› በማለት በአጭሩ ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል፡፡ አላግባብ ድብደባ እየደረሰበት ቢሆንም፣ ምንም የሚሰጠው ማስረጃ እንደሌለው ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ የሁለተኛ ተጠርጣሪ ረዳት (ወያላ) መሆኑን የገለጸው ተጠርጣሪ፣ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለና ሊያዝ የቻለውም ሁለተኛ ተጠርጣሪን ፖሊሶች ይዘውት ሲሄዱ፣ ቀን ሙሉ የሠሩበትን ገቢ ለመስጠት ሲሄድ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ተሳታፊ አለመሆኑን ክዶ ተከራክሯል፡፡

ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ፍርድ ቤት የቀረበው መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ምርመራውን ሲያደርግ የከረመው የፖሊስ አባል ሌላ መሆኑን ገልጾ፣ ተጠርጣሪዎቹ ደረሰብን የሚሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ግን ተቋሙ እንደማይፈጽም ተናግሯል፡፡ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ቀሪ ምርመራ እንደሚቀረው ሲያስረዳ፣ ‹‹ሟች ከተመረመረችባቸው ሆስፒታሎች መረጃ ማሰባሰብ እንደሚቀረው፣ በአንደኛው ተጠርጣሪ ቤት ለአምስት ቀናት ታግታ መቆየቷንም ማጣራት እንዳለበትና ተጠርጣሪዎቹ ከቤት አውጥተው ከጣሉዋት በኋላ መጀመሪያ ቀድመው ያገኟትን ሰዎች አፈላልጐ ቃል መቀበል እንደሚቀረው አስረድቷል፡፡ በሟች ላይ የቡድን ድርጊት ከመፈጸሙ በፊት፣ አንደኛው ተጠርጣሪ በሚኒባስ ታክሲ ውስጥ ከሟች ጋር ግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽሙ አይቷል የተባለ ተጠርጣሪን ይዞ ቃል መቀበል እንደሚቀረው በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቅድለት አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ፖሊስ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ማድረግ ያለበት ቴክኒክና ታክቲክ ተጠቅሞ መሆን እንዳለበት አስረድቶ፣ ተጠርጣሪዎቹ ደርሶብናል ያሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአስቸኳይ እንዲቆም አዟል፡፡ ከቤተሰብ ጋር የመገናኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዳላቸው ጠቁሞ፣ እንዲገናኙ እንዲያደርግም አዟል፡፡ ድርጊቱና ወንጀሉ ውስብስብ መሆኑን ገልጾ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት አሥር ቀናትን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዶ ለኅዳር 22 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 34912 times