በግለሰብ ነጋዴዎች ላይ የሚጣል ግብርና ታክስ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ አስነሳ

EthiopianReporter Nov 17 2014

በግለሰብ ነጋዴዎች ላይ የሚጣል ግብርና ታክስ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ አስነሳ

- ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ልኮታል

የአዲስ አበባ ከተማ ግለሰብ ነጋዴዎች የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94ን ተላልፈዋል በሚል፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚመሠርትባቸው ክስ የሕገ መንግሥት ጥያቄ አስነሳ፡፡

ባለሥልጣኑ በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 መሠረት በአዲስ አበባ ግለሰብ ነጋዴዎች ላይ ክስ የሚመሠርት ከሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 49 (2) ሥር የተደነገገውን ማለትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ከተሰጠው ሕገ መንግሥታዊ ሙሉ ሥልጣን ጋር የሚጣረስ መሆኑን በመጠቆም የሕግ ባለሙያዎች ተቃውሟቸውን አቅርበዋል፡፡

የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ሰለሞን እምሩ፣ አቶ ሐይረዲን ሁሴን መሐመድ የተባሉ ደንበኛቸውን፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 286/94 አንቀጽ 96ን ተላልፈዋል በሚል በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 9ኛ ወንጀል ችሎት ክስ መመሥረቱን ተቃውመው ተከራክረዋል፡፡

ጠበቃው ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት መከራከሪያ ነጥብ እንደገለጹት፣ የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 አንቀጽ 52 (4) እንደተደነገገው፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ግለሰብ ነጋዴዎች ላይ፣ የንግድ ትርፍ ግብር፣ የኤክሳይዝና የተርንኦቨር ታክስ በሕግ መሠረት የመወሰንና የመሰብሰብ ሥልጣን አለው፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ የመክሰስም ሆነ የመጠየቅ መብት እንደሌለው በማስረዳት የሞገቱ ሲሆን፣ ክሱም የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌን (አንቀጽ 49 (2)ን) እንደሚጥስም አክለዋል፡፡

ጉዳዩን እየመረመረ የሚገኘው የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 9ኛ ወንጀል ችሎትም የሁለቱን ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ብይን፣ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደሚያስፈልገው ገልጿል፡፡ በመሆኑም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ትርጉም እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቶ መዝገቡን ለታኅሳስ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 34740 times