የአካል ጉዳት መጠን ደረጃዎችና አወሳሰናቸው

Ahmed Jemal Nov 15 2012

የአካል ጉዳት መጠን ደረጃዎች

የአካል ጉዳት መጠን ደረጃዎች በአራት ይከፈላሉ፡፡ ይኸውም

  • ጊዜያዊ የአካል ጉዳት
  • ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት
  • ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት እና
  • ሞት ናቸው፡፡ እንደየቅደም ተከተላቸው በሚከተለው ሁኔታ እናያቸዋለን፡፡

 

ሀ. ጊዜያዊ የአካል ጉዳት፡-

 

የዚህ ጉዳት ሰለባ የሆነ ሠራተኛ የተመደበበትን ሥራ ለተወሰነ ጊዜ በሙሉ ወይም በከፊል ለማከናወን እንዳይችል ይሆናል አንቀጽ (100)፡፡ የመሥራት ችሎታው መቀነስ ወይ መጥፋት ጉዳቱን ለመጠገን በሚወስደው ጊዜ ይገደባል፡፡ ከዚያ በኋላ የመሥራት ችሎታው ይመለሳል፡፡ በአብዛኛው የጊዜው ርዝማኔ ከአንድ ዓመት የሚዘል አይሆንም፡፡ ለዚህ መነሻ የሚሆነው በአንቀጽ 107(1) cum 108(1) እና 108(3)(ሐ) ላይ የተገለፀው ነው፡፡ ጊዜያዊ የአካል ጉዳት እስከሚወገድበት ጊዜ ድረስ ተገቢው ክፍያ ሲፈፀም ቢቆይም ይህ በየጊዜው የሚሰጠው ክፍያ ከአንድ ዓመት የሚዘል አይሆንም [አንቀጽ 108(1)]፡፡ ይህ ማለት ጊዜያዊ የአካል ጉዳት ከአንድ ዓመት ያለፈ የመሥራት ችሎታን የሚያሳጣ አይደለም የሚለውን ሐሳብ የሚያመጣ ነው፡፡  

 

ለ. ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት ፡-

 

ይህ ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ የማይድን እና የመሥራት ችሎታውን የሚጐዳ ችግር ይገጥመዋል [አንቀጽ 101(1)] ፡፡ የመሥራት ችሎታው መቀነስ ለተመደበበት ሥራ ብቻ ሳይሆን በተመሣሣይ ሥራ ላይ ያለውን የመሠራት ችሎታ ጭምር የሚመለከት ነው፡፡ በያዘው የሥራ መደብ ላይ መሥራቱን ቢቀጥልም ባይቀጥልም የመሥራት ችሎታው አንድ ጊዜ የቀነሰ እና አብሮት የሚዘልቅ በመሆኑ መለኪያው ይሠራ የነበረው ሥራ ብቻ አይሆንም፡፡ በሌላ ቦታ በሌላ ጊዜና ሁኔታ ሊሠራ ይችል ለነበረው ለዚያው ሥራ ያለውን አቅም የሚያዳክም በመሆኑ ይኸው ግምት ውስጥ የሚገባ ይሆናል፡፡

 

 

ሐ. ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት

 

ይህ ጉዳት ደግሞ ማናቸውንም ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ ለመሥራት የሚከለክል የማይድን ጉዳት ነው [አንቀጽ 101 (2)] :: ከፍ ብሎ ከተገለፀው ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት ይህ በሁለት ዐቢይ ነጥቦች የሚለይበትን ሀሳብ ይዞ ቀርቧል፡፡ የመጀመሪያው የጉዳቱ መጠን መለኪያ ሆኖ የቀረበው ገቢ የማግኘት እንጂ የመሥራት ችሎታው አቅም አለመሆኑ ነው፡፡ በከፊል ዘላቂ የአካል ጉዳት የመሥራት ችሎታ መቀነስ የገቢ መቀነስን የሚያስከትል ቢሆንም ሁል ጊዜ ይህ ይሆናል ማለት አይቻልም፡፡ የመሥራት ችሎታው ቀንሶ እያለ በዚያው ደመወዝ ወይም ሻል ባለ ደመወዝ ሊሠራ የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ ግን ሁኔታውን አይለውጠውም፡፡ ዋናው መለኪያ የገቢው አለመነካት ወይም ከፍ ማለት ሳይሆን የመሥራት አቅሙ (Potential) መቀነስ ነው በዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ግን መሠረታዊው ጉዳይ ገቢ የማግኘ አቅምን ማሳጣት ነው::

 

ሌላው ደግሞ በዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት የመሥራት ችሎታው መቀነስ በመደበኛ ሁኔታ የገቢ ሁኔታን የሚቀንስ ሲሆን ይህ የገቢ መቀነስ የሚታየው ሠራተኛው ይሠራ ከነበረው ወይም በተመሣሣዩ ሁኔታ ሊሠራ ይችል ከነበረው ሥራ አንፃር ነው፡፡ ለዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት መሠረት የሚሆነው ግን ሠራተኛው ማናቸውንም ገቢ የሚያስገኝ  ሥራ ለማግኘት የሚከለክለው መሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ “ማናቸውንም ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ” የሚለው ምን ማለት ነው? የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ “ማናቸውንም” የሚለው ቃል ሰፋ ባለ መንገድ ታይቶ ሠራተኛው ከጉዳቱ በፊት ከነበረው ሙያ ውጪ ያሉ ሥራዎችንም እንደሚሸፍን ለምሳሌ አንድ ማሽኒስት የነበረ ሰው “በተሸካሚነት” ወይም “በሊስትሮነት” ሥራ ላይ ተሠማርቶ መሥራት ከቻለ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳተኛ ሊባል አይችልም የሚል ትርጉም እንደሚሰጥ ማንበብ አለብን ወይስ ጉዳቱ በደረሰ ጊዜ ተጐጂው በቀጥታ ወይም በተለዋዋጭ ሊሠራ ይችል ከነበረው የሠለጠነበት ወይ የተማረበት አማራጭ የሥራ መስኮች አንፃር መታየት አለበት? የፊተኛው ትርጓሜ እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሣ ተጐጂዎች ሁሉ ከፍ ሲል ከተጠቀሱት ዓይነት ሙያዎች በአንዱ ሊሠማሩ የሚችሉ መሆናቸው ብቻ ከዘላቂ ሙሉ የአካል ተጐጂነት ሽፋን በርካታዎችን የሚያወጣ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳተኛ አይኖርም ወይም ቁጥራቸው ያንሳል፡፡ ይህ ግን በጉዳቱ ከፍተኛነት የተነሣ በዘላቂ ሙሉ የአካል ተጐጂነት መደብ ሊያገኙ የሚገባውን ክፍያ እንዳያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ይልቁንም የሠራተውኛው ጉልበት ለዕድገት መሠረት መሆኑን ከግምት የሚያስገባወና ተገቢውን ክብር የሚሰጠው፣ ተመዛዛኝ (efficient) እና ተግባራዊ (Pragmatic) የሆነው አተረጓጎም ጉዳቱ በደረሰ ጊዜ ሠራተኛው በቀጥታ ወይም በተለዋዋጭ ሊሠራ  ይችል ከነበረው የሠለጠነበት ወይም የተማረበት አማራጭ የሥራ መስኮች አንፃር ማየቱ ሳይሆን አይቀርም፡፡ 

 

መ. ሞት፡-

 

ይህ ጉዳት ደግሞ በአንድ ሠራተኛ ላይ ሊደርስ የሚችለው አስከፊው እና የመጨረሻው ደረጃ ነው፡፡ ጉዳቱ ራሱን የሚገልጽ በመሆኑ ማብራራያ የሚያስፈልገው አይደለም፡፡

 

የጉዳት መጠን አወሳሰን

 

በአንድ ሠራተኛ ላይ የሚደርሱት የጉዳት መጠን ደረጃዎች ከፍ ብለው የተገለፁት ናቸው፡፡ ይህን ደረጃ በመመሪያ በጉዳት መወሰኛ ሠንጠረዥ የሚያወጣው የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ነው ፡፡ ደረጃ የሚያወጣው ለዘላቂ ከፊል እና ሙሉ የአካል ጉዳት ብቻ ነውአንቀፅ 102 1፡፡ በጊዜያዊ የአካል ጉዳት ሠራተኛው ቀድሞ የነበረውን የመሥራት ችሎታ መልሶ ስለሚያገኝ፤ ሞትም ቢሆን የጉዳቱ መጠን በራሱ የተገለጠ በመሆኑ ሚኒስትሩ ለነዚህ ጉዳቶች ደረጃን አይወስንም፡፡

 

ደረጃቸውን ለሚወስንላቸው ዘላቂ ሙሉ ወይም ከፊል ጉዳቶች ግን የጉዳቶቹ መጠን ደረጃ ከመወሰኑ በፊት ጉዳቱ በደረሰ በአስራ ሁለት ወራት ውስጥ በተቻለ መጠን የጉዳቱን መጠን መወሰን ከሚኖርበት የህክምና ቦርድ ማስረጃ ማግኘት ይጠይቃል [አንቀጽ 102 (2)] ፡፡

 

በዚህ መንገድ የጉዳቱ መጠን እና ደረጃ ከተወሰነ በኋላ ውሳኔው ቋሚ ሆኖ የሚቀጥል ላይሆን ይችላል፡፡ የጉዳቱ መጠን ከውሳኔው በኋላ ከፍ ሊል ወይም ሊሻሻል ይችላል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያበቃ ምክንያት አለ ወይም ቀድሞ የተደረገው ምርመራ ሥህተት አለበት የሚል ወገን ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን ሲጠይቅ በዚሁ መነሻነት በድጋሚ ምርመራ ሊደረግ ይችላል፡፡ አንቀጽ 102 (3) በድጋሚ ምርመራው የጉዳቱ መጠን ከተለወጠ ደረጃው በዚያው መጠን ታርሞ በጉዳቱ ምክንያት የሚገኘው ክፍያ እንዲቀጥል፣ እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ይደረጋል [አንቀጽ 102 (4)(5)] ፡፡ ለምሳሌ ያህል ጊዜያዊ የአካል ጉዳት የደረሰበት ሠራተኛ ከአንድ ዓመት የሚዘልቅ የመሥራት ችሎታን የሚቀንስ ጉዳት ያገኘው እንደሁ ተጐጂው በሚያቀርበው ጥያቄ መነሻነት በድጋሚ ተመርምሮ ወደሚቀጥለው ደረጃ ሊሻገር ይችላል፡፡ የሚፈፀመው ክፍያም በዚሁ መጠን የሚስተካከልለት ይሆናል፡፡

Read 12388 times Last modified on Jun 03 2015