በሽብር ወንጀል ከተመሰረተባቸው ክስ በነጻ መሰናበታቸውን ተከትሎ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ የአንድነት፣ ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ እና የአረና ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሽበሺ፣ አብርሃ ደስታ፣ አብርሃም ሰሎሞን እና የሺዋስ አሰፋ ላይ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በጠየቀባቸው ይግባኝ ክርክር ላይ ቆይተው የካቲት 3 2008 ዓ.ም ችሎቱ አምስቱም ተከሳሾች ጉዳያቸውን ከማረሚያ ውጭ ሆነው ይከታተሉ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ይህን ተከትሎ የማረሚያ አስተዳደሩ ከአምስቱ ግለሰቦች ሦስቱ "ዳንኤል ሽበሺ፣ አብርሃ ደስታና የሺዋስ አሰፋ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር የመጀመሪያ ሳምንት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት መዝገባቸውን እየተመለከት ሳለ ችሎት በመዳፈራቸው ከአንድ ዓመት ከሁለት ወር እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወር በሚደርስ እስራት ቀጥቷቸው ገና የእስራት ጊዜያቸውን ሳያጠናቅቁ እንዴት ይፈቱ የሚል ትዕዛዝ ይደርሰኛል፤ ትዕዛዙ ግልጽ አይደለም" በማለት ለችሎቱ የጻፈው ደብዳቤ ትናንት የካቲት 7 2008 ዓ.ም ደርሷል፡፡
ተከሳሾቹም የእስራት ቅጣቱ እጃችን ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ነው መቆጠር ያለበት፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ችሎት በመዳፈር የተላለፈብን ቅጣት ይጠናቀቃል፤ ከእስር ተለቀን ነው ጉዳያችንን መከታተል ያለብን በማለት ለችሎቱ ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡
ችሎቱም እጃችሁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ሳይሆን መቆጠር ያለበት ወንጀሉን ከፈጸማችሁበት ቀን ጀምሮ ነው የሚቆጠረው በማለት ጉዳያቸውን በእስር ሆነው መከታተል አለባቸው ብሏል፡፡
ነገር ግን የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በችሎት መድፈር ያልተቀጡትን የቀድሞ የአንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ አብርሃም ሰሎሞን በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መሰረት ለምን እንዳልለቀቃቸው ረቡዕ የካቲት 9 2008 የሚመለከተው ኃላፊ ችሎት ቀርቦ እንዲያስረዳ ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ሀብታሙ አያሌው እና አብርሃም ሰለሞን ዛሬ ከእስር ተለቀዋል፡፡ የካቲት 3 2008 ሁሉም ግለሰቦች ከሀገር እንዳይወጡ መታዘዙ አይዘነጋም፡፡