የአላባ መብት ከአንድ ግዙፍነት ያለው የሚንቀሳቀስ ወይም የማይንቀሳቀስ ንብረት ወይም ግዙፍነት ከሌለው የባለቤትነት መብት ተቀንሶ በንብረቱ ለመገልገል (usus) ወይም ፍሬውን የመሰብሰብና መውሰድ (fructus) መብት በመስጠት የሚቋቋም የንብረት ግንኙነት ነው፡፡ ይሄውም አንድ ሰው ካለው የባለቤትነት መብት ቀንሶ ለሌላ ሰው የሚያስተላልፈው መብት ነው፡፡  አንድን ንብረት በአላባ የማስተላለፍ መብት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 40/1/ ". . . ወይም በሌላ መንገድ የማስተላለፍ መብቶችን ያካትታል" በሚለው ስር የሚወድቅ ህገ-መንግስታዊ ሽፋን የተሰጠው መብት ነው፡፡ አላባ ከፍ/ብ/ህጉ አንፃር ሲታይም ከቁጥር 1309-1358 ባሉ ድንጋጌዎች ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት የምናገኘው በንብረት የመገልገል ወይም ፍሬው የመሰብሰብና የመውሰድ ወይም ሁለቱ መብቶች አንድ ላይ ተዳብለው ልናገኛቸው የምንችል የንብረት ማስተላለፍያ አገባብ ነው፡፡

 

የአላባ መብት መሰረቱ (subject matter) ግዙፍነት ያላቸው (corporeal things) የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው (incorporeal things) እንደ ቅጅ መብትና ፈጠራ ያሉ የንብረት መብቶች ናቸው፡፡ (በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1204/1/፣ 1126፣ 1309/1/ /2/ እና 1347 እና ቀጠቀዮቹ)  የአላባ መብት ምንጭ (source) ውል፣ ኑዛዜ ወይም ሕግ ሊሆን ይችላል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1184 እና 1185) የአላባ መብት መሰረት የሚንቀሳቀስ ንብረት በሆነ ግዜ ተጠቃሚው ንብረቱን በእጅ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1186/1/) የአላባ መብት መሰረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜ ግን የአላባ መብት ምንጭ የሆነው ውል ወይም ኑዛዜ መመዝገብ ስለሚኖርበት በይዞታው ስር በማድረግ ብቻ የአላባ ተጠቃሚነትን መብት ሊያገኝ አይችልም፡፡ (በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1184 እና 1185) በኢትዮጵያ ፍ/ብሄር የፍትህ ስርዓት የአላባ መብት ከህግ የሚመነጨው ከማይንቀሳቀስ የውርስ ሃብት ጋር በተያያዘ መንገድና፣ ለአካለ መጠን ባላደረሰ ልጅና ሞግዚቱ ወይም በባልና ሚስት መካከል ያለን ግንኙነት መሰረት በማድረግ ሲሆን የሚተላለፍበት ስርዓትም በማግኘት (acquisition, Possession etc.) በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1310 እና 1311 ላይ በተደነገገው መሰረት ነው፡፡

የንብረት ባለቤትነት መብት (ownership right) ሶስት መሰረታዊ መብቶችን ማለትም የሌሎችን መብት ሳያውኩ (ሳይነኩ) (without impairing any one’s right) እንደፈለጉ ማድረግ (abusus right) በንብረት የመገልገልን (usus) እና ፍሬውን የመሰብሰብና የመውሰድ (fructus) መብቶችን የሚያጐናፅፍ ሲሆን የአላባ መብት የንብረቱ ባለቤት (owner) የባለቤትነት መብቱን (ownership right or abusus right) ለራሱ በማስቀረት የተቀሩትን ሌሎች ሁለት መብቶች ማለትም በንብረቱ የመገልገልና (right of using) እና ፍሬውን ሰብስቦ የመውሰድ (enjoying the thing) ለአላባ ተጠቃሚው በማስተላለፍ የሚገኝ መብት ነው፡፡ የአላባ መብት ተጠቃሚው በሂወት አስካለ ድረስ ሊገለገልበት የሚችል መብት እንጂ እንደሌሎቹ የንብረት መብቶች ወደ ተወላጆቹ ወይ ወላጆቹ በውርስ ሊተላለፍ የሚችል መብት አይደለም፡፡ይህ ማለትም አንድ ሰው በንብረት ያላውን የባለቤትነት መብቱን ተጠቅሞ የአላባ መብት ለሌላ ሰው በኑዛዜ መስጠት የሚችል ቢሆንም ይህ የአላባ ተቀባይ በሚሞትበት ጊዜ ይህን የአላባ መብቱ ለወራሾቹ በኑዘዜ ማሰተላለፍ አይችልም ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322(1)) አንዱ የአላባ መብት ማስገኛ መንገድ ውል እንደምሆኑ መጠን  የአላባ መብት በአላባ ሰጪና ተቀባይ መካከል በሚደረግ ስምምነት የሚቋቋም የንብረት መብት በሚሆንበት ጊዜ በተዋዋዮቹ መካከል በርካታ መብቶችና ግዴታዎች (bundle of rights and duties) ያሉበት ነው፡፡

 

የአላባ ተጠቃሚ መብትና ግዴታ

 

Øበአላባ የተሰጠውን መብት ለመገልገል ንብረቱን በራሱ ወይም በወኪሉ አማካይነት በይዞታው ስር ማድረግና በዚህ መብቱ ለመስራት በባለቤቱ፣ በወራሾቹ ወይም ንብረቱን በእጃቸው ላይ ባደረጉ 3ኛ ወገኖች ላይ የባለይዞታነት ክስ (possessory action) የመመስረት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1311 እና 1341)

Øየማይንቀሳቀስው ንብረት ለህዝብ ጥቅም ሲባል በመንግስት በሚወሰድበት ግዜ የአላባ ተጠቃሚው በመልቀቅ ምክንያት የተሰጠውን ካሳ የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1319(2)) 

Øየአላባ ተቀባዩ ያለውን መብት መሰረት በማድረግ የመድን ሽፋን የመግዛትና ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1320 እና ን/ህ/ቁ 654)

Øፍ/ብ/ህ/ቁ.1311 የአላባ ተጠቃሚው የአላባ ንብረቱን በቁጥጥር ስር ማደረግ አለበት ሲል እንደሚደነግግ ሁሉ የአላባ ተጠቃሚው ይህን የአላባ መብት የሚያገኘው ከህግ ከሆነ መብቱን የሚያገኘው ወድያውኑ (automatic) ነው፡፡ መብቱ የመነጨው ከውል በሆነ ጊዜ ስመምነቱ እንደተፈፀመ፣ በውርስ ከሆነም ውርሱ ሲከፈት፤ በኑዛዜ ከሆነ ደግሞ የውርስ ንብረት የማጣራቱ ስራ እንዳለቀ የአላባ መብቱን ያገኛል፡፡

Øየአላባ መብቱ መሰረት የሆነው ነገር የፍጆታ እቃ (consumable good) ከሆነና ሳይጐዳ በመብቱን ሊሰራበት የማይችል በሆነ ግዜ የንብረቱ ባለቤት ይሆናል፡፡ ይህ ማለትም በአላባ የተሰጠውን ንብረት እንደፈለገ ያረገዋል(will have the right to dispose) ማለት ነው:: ለምሳሌ፡- የአላባ መብቱ የተሰጠው በወይን ላይ ከሆነ ወይኑን የመጠጣት፣ የድንጋይ ከሰል ከሆነ በድንጋይ ከሰሉ የመገልገልና የመጨረስ፣ ገንዘብ ከሆነም ገንዘቡን ወደ ሌላ የማስተላለፍ መብት ይኖረዋል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1327(1))

Øየአላባ መብቱ የተሰጠው ፍሬ ለመሰብሰብ ከሆነ የአላባ ተቀባዩ የተፈጥሮ ፍሬዎች (natural fruits) እንደ ጥጃዎች (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1171 እና 1328(1)) ፣ ሲቪል ፍሬዎች (civil fruits) እንደ ኪራይ፤ ወለድ ወይም የተጣራ ትርፍ (interests, arrears or dividends) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331 እና 1347) እና የኢንዱስትሪ ውጤቶች (periodical products) (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1170/2/ እና 1333) የመሰብሰብ መብት ይኖረዋል፡፡

Øየአላባ መብቱ በሚቋረጥበት ግዜ ባልበሰሉ ሃብቶች ወይም የአላባ መብቱ በሚቋረጥበት ግዜ ባልበሰሉ ነገሮች (pre-mature things) ሲበስሉ ወይም ውሉ ሲቋረጥ የበሰሉ ካሉ የአላባ ተጠቃሚው እንደሆኑ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ 1328(1))

Øየአላባ ንብረቱ ለምሳሌ እንደ ቤተ መፅሐፍ ፣ ፈረስና የቤት እቃ ያለ ሲሆን የአላባ ተጠቃሚው ይህንን ንብረት ለሌላ 3ኛ ወገን በኪራይ (lease) የመስጠት መብት ይኖረዋል፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331)

Øበአላባ የተሰጠን ንብረት መሬት ወይም ቤት ሲሆን ከተኸራየ በኋላ የገዛ ወይም በዋስትና የያዘ ሰው ቢኖሩም ለሚቀጥሉት 3 ዓመታት የአላባ ተጠቃሚው በአላባ መብቱ ይሰራበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1332(2))

Ø

Øአላባ ተቀባዩ የዋስትና (mortgage) ዋናው እዳ (principal debt) የመክፈል ግዴታ የለበትም፡፡ የከፈለ እንደሆነ ግን አላባ ሰጪውን ገንዘቡ እንዲመልስለት የመጠየቅ መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1340 (2))

Øየማይንቀሳቀስ ንብረት ማስለቀቅንና የመድህን ካሳ ክፍያን መሰረት በማድረግ በሚነሱ ክርክሮች መብት አለኝ ብሎ በክርክሩ ውስጥ ልግባ የማለት መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1311 ፤1341፣ ን/ህ/ቁ. 654 እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 33(2))

Øበአላባ በተሰጠው ንብረት ላይ ሌላ ተጨማሪ ነገር የሰራው ካለ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ነቅሎ የመውሰድ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1346(2))

Øበአላባ የተሰጠው ንብረት ከእጁ ወይም ከይዞታው ከወጣ እንዲመለስለት ወይም ሁከቱ እንዲወገድለት የባለ ይዞታ ክስ (possessry action) የመመስረት መብት አለው፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1149፡ 1311፡1341 እና ፍ/ብ/ስ/ስ/ህ/ቁ 33(2))

Øበአላባ የተሰጠው ንብረት ቢወድምም የአላባ ተጠቃሚው በትራፊው ወይም በቀሪው ዎና (ruins) መገልገል ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1344)

Øበአላባ የተሰጠውን ንብረት የመስጠትና የኪራዩን ገቢ የመስብሰብ መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1331) ስለዚህም የአላባ ግንኙነት እጅግ በርካታ መብቶችን ሊያስገኝ የሚችል የንብረት ግንኙነት እንደሆነ ከንብረት ህጉ ይዘት ለመገንዘብ ይቻላል፡፡ ከግዴታ አንፃር ሲታይም የሚከተሉት ግዴታዎች የሚስተዋሉበት ነው፡፡

vበአላባ የተሰጠውን ንብረት ደረጃውን ጠብቆ በቅን ልቦና የማስተዳደርና የተቋቋመበትን አላማ መሰረት በማድረግ በአላባ መብቱ የመገልገል ግዴታ አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1312 ፣ 1326 ፤ 1328 እና 1330)

vእንደ የጣራ ማፍሰስ፣ መለስተኛ የግንብ መሰንጠቅ፣ የቀለም ቅብ ያሉ ተራ የጥገና ስራዎች የመስራት ግዴታ አለው፡፡ የአላባ መብቱ የተገኘው በውርስ (inheritance) ሲሆን የአላባውን ንብረት ዕዳ ወይም ወለድ የመክፈል ግዴታና መደበኛ ወጪ እንደ ግብር ያሉ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ ይህ የግብር መክፈል ግዴታ በመፈፀም ላይ ያለ የአላባ ተጠቃሚ ለተከታታይ 15 ዓመታት ቢከፈልም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1168 በመያዝና መገልፈገል ብቻ (usucaption) የባለቤትነት መብት እንዲያገኝ አያደርገውም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1313 እና 1314)

vየአላባ ውሉ ሲቋረጥ የአላባው ንብረት በሂደት የሚመጣውን መጥፋትና መበላሸት (loss and deterioration) ሳይጨምር እንደነበረው ለባለቤቱ የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1317 ፣  1326፤ 1327(2) ፣1343 ፤ 1346 እና 2027)

vየአላባ ተጠቃሚ በአላባ የተሰጠውን ንብረት በሚንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (pledge)፣ በማይንቀሳቀስ ንብረት ዋስትና (mortgage)፣ በንብረት አገልግሎት (servitude) ወይም ለሌላ ሰው በአላባ የመሰጠት ወይም የማስተላለፍ መብት ቢኖረውም ይህን መብቱን በስራ ላይ በሚያውልበት ግዜ የባለቤቱን መብት መጉዳት (impair) የለበትም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1318 እና 1324)

vየአላባ መብት ቀሪ በሚሆንበት ግዜ የንብረቱን ዋጋ ሳይሆን ንበረቱን በዓይነት ማለትም በአላባ የተሰጠውን ንብረት የመመለስ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1321)

vበአላባ የተሰጠው ንብረት በሶስተኛ ወገኖች እጅ ሲገባወይም የጣለቃ መግባት (interference) ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ለባለቤቱ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1342)

vበአላባ የተሰጡት እንስሳት በሚሆንበት ግዜና ከእነዚህ የተወሰኑት በአደጋ ወይም በበሽታ ያለቁ እንደሆነ የነዚህን ምትክ ከሚወለዱት የመተካት ግዴታ አለበት፡፡ እነዚህ እንሰሳት በጠቅላላ በአደጋው ወይም በበሽታው ካለቁ ግን ቆዳቸውን የማስረከብ ወይም የቆዳውን ዋጋ ለባለቤቱ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1345)

vመሰረታዊ ለውጥ ያለማድረግ ግዴታ ይኖርበታል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1330)

vንብረቱን የማቀብ (preserve) ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1309)

vለንብረቱ ለማስተዳደር፡ ፍሬውን ለማግኘትና ለመጠቀም የሚያስፈልገውን ወጪና ወለድ የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡(ፍ/ብ/ህ/ቁ.1313) ስለዚህ አንድ የአላባ ተጠቃሚ በርካታ መብቶች እንዳሉት ሁሉ ግዴታዎችም ያሉበት ነው፡፡

የአላባ ሰጪ መብትና ግዴታ

ü  የአላባ ውል ግዜው ሲያልቅ ንብረቱን የመረከብ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322 እና 1327)

ü  በአላባ መብትነት በሰጠው ንብረትና በመብቱ ላይ ተፅእኖ (jeopardy) አለ ባለ ግዜ ፍርድ ቤት ጣልቃ ገብቶ መብቱ እንደነበረው እንዲደረግለት የመጠየቅ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1324) 

ü  ልዩ ወጪዎች እንዲከፍል በሚጠየቅበት ግዜና ይህን ወጪ የአላባ ተጠቃሚው በብድር መልክ የማይሰጠው ከሆነ በአላባ ሰጥቶት ከነበረው ንብረቱ ገሚሱን በመሸጥ እዳውን የመክፈል መብት፡፡

ü  በአላባ የሰጠውን ንብረት በዋስትና (mortgage) የመስጠት መብት፡፡

ü  በአላባ ተጠቃሚው ዋስትና (Securities) እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1324)

ü  የአላባ ተቀባዩን መብት ሳይጋፋ በንብረቱ የማዘዝ መብት አለው ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1323)

ü  የባለቤትነት መብቱን መሰረት በማድረግ የመድን ዋስትና የመግዛትና የመድን ሽፋን የተሰጠው አደጋ እውን ሲሆን (whenever the risk materialises) ካሳ የማግኘት መብት አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1320)

ü  በአላባ ከተሰጠው ንብረት ጋር ያለአግባብ የተላለፈ ንብረት ካለ የማስመለስ መብት፡፡

ü  ለአላባ ተቀባይ እንዲሆን ከተወሰነው በላይ ፍሬ ወይም ትርፍ ከተገኘ የመውሰድ መብት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1328(2) እና 1348)

ü   በአላባ በተሰጠው መሬት ውስጥ የተቀበረ ገንዘብ (treasure) ከተገኘ ባለቤት በመሆኑ የመውሰድ መብት፡፡( ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1329)

ü   የአላባ ተጠቃሚው በተሰጠው ንብረት ላይ ሌላ ተጨማሪ ስራ ሰርቶ ከሆነ የአላባ መብቱ ከተቋረጠ ግዜ ጀምሮ በአንድ ዓመት ግዜ ውስጥ ንብረቱን ለማንሳት ካልጠየቀ አላባ ሰጪው የዚህ ተጫማሪ ስራ ባለቤት ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1346/2/ )  ከግዴታ  አንፃር ሲታይም የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩታል፡፡

በአላባ የሰጠውን ንብረት ለአላባ ተጠቃሚው የማስረከብ ግዴታ አለው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1321)

የአላባ ውሉ በፅሑፍ እንዲሆንና እንዲመዘገብ የማድረግ ግዴታ አለው፡፡

በአላባ የተሰጠው ንብረት ጥገና ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ሲሆን ወጪውን የመሸፈን ግዴታ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1338)

የጦርነት መዋጮ፣ የሰራዊት ሰፈር፣ ቆሻሻ ማስወገጃ ወጪ ወይም ረግረጐች የማድረቅ የመሳሰሉ ልዩ ወጪዎች (extra ordinary charges) የመክፈል ግዴታ የአለባ ሰጪው ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.

በመደበኛ አገልግሎት ምክንያት ዋጋው ቢቀንስ (depreciation caused by ordinary wear and tear) የንብረትን ማሽቆልቆል መሰረት በማድረግ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚደረግ ወጪ ቢኖር የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1326 )

የአላባ ግንኙነት ቀሪ ስለመሆን

የአላባ ተጠቃሚው በውሉ ያሉትን ግዴታዎች የጣሰ አንደሆነ የአላባ መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1318 (3) እና 1324)

የአላባ ተጠቃሚው ሲሞት የአላባ መብት በውርስ የሚተላለፍ መብት ባለመሆኑ ምክንያት ቀሪ ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን የአላባ ተጠቃሚነት መብቱ የተሰጠው ለባልና ሚስት በጋራ በሆነ ጊዜ የአንደኛው መሞት የአላባ ተጠቃሚነቱን መብት ሙሉ ለሙሉ ቀሪ አያደርገውም፡፡ በሌላ አነጋገር በሂወት ካለው ስው ጋር የአላባ ግንኙነቱ ይቀጥላል ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322)

የአላባ ውሉ ግዜ ሲያልቅ በአላባ ተጠቃሚ የመሆን መብቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1322)

የአላባ መብት ተጠቃሚነት መብት የተሰጠበት ነገር እንደ ጥሬ ገንዘብ ባሉ አላቂ ነገሮች (consumable goods) ሲሆንና ሲያልቁ የአላባ መብት የተቋቋመበት ውል ቀሪ ይሆናል፡፡

የአላባ ተጠቃሚው በራሱ ፍላጐት በግልፅ የአላባ ተጠቃሚነት መብቱን ሲተው (express waiver) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1323(2))

በአላባ የተሰጠው ንብረት ሙሉ ለሙሉ ሲወድም የአላባ ጥቅም መሰረት (subject matter of the usufract) በሌለበት ሁኔታ መብቱ ሊኖር ስለማይችል የአላባ ግንኙነቱን እንዲቀር ያስገድዳል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1319፣ 1343) ስለዚህ የአላባ ግንኙነት እንደ ሁሉም በህግ ፊት ዋጋ ያለው ተግባር ወይም ከህግ የሚመነጭ መብት በአንድ ወቅት ሊቋረጥ የሚችል ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት በመቋረጡ የሚኖረው ውትም፡-

vከአላባ ተጠቃሚው ጋር የተደረጉ ውሎች ውጤት አልባ (extinguished contracts) ይሆናሉ፡፡

vበአላባ የተሰጠው ንብረት የማይንቀሳቀስ ንብረት በሆነበት ግዜና ተከራይቶ ወይም በዋስትና ተሰጥቶ ከቆየ የውሉ ግዜ በማለቁ ብቻ የአላባ መብቱ ቀሪ ሊሆን ስላማይቻል 3ኛ ወገኞች ለሶስት ዓመት የግድ መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የአላባ መብት ግዙፍነት ባላቸው የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ እንዲሁም ግዙፍነት በሌላቸው የንብረት መብቶች ላይ ሊመሰረት የሚችል ህገ-መንግስታዊ እውቅና የተሰጠው የዜጐች በንብረት የመገልገል፤ፍሬ የመሰብሰብንና መውሰድን መብት የሚያጎናፅፍ ከውል ፤ ከህግ ወይም ከኑዛዜ የሚመነጭ ግንኙነት  ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ከውል፤ ከህግና ከኑዛዜ የሚመነጩ በርካታ የአላባ ተጠቃሚና አላባ ሰጪ መብቶችና ግዴታዎች የሚስተዋሉበት ንበረትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ነው፡፡ ይህ ግንኙነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት (juridical acts) ወይም ከህግ የሚመነጩ መብቶች (legal rights) ተመስርቶ ቆይታው ይርዘም ይጠር ሰዎች በመብቱና ግዴታው ሲሰሩበት ከቆዩ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ቀሪ የሚሆን ንብረትን መሰረት ያደረገ ግንኙነትም ነው፡፡