የጋራ ባለሃብትነት ምንድን ነው? የጋራ ባለሃብትነት መብት በመሰረቱ በሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች መካከል በሚደረግ ውል የሚቋቋምና የሚገዛ የጋራ ንብረት ባለሃብትነት መብት ወይም ከህግ በሚመነጭ የጋራ ባለሃብትነት የሚቋቋም የንብረት መብት ነው፡፡ የጋራ ባለሃብትነት መብት ከፍታብሄር ህግ አኳያ ሲታይ በሁለት ማለትም ተራ የጋራ ባለሃብትነት (Ordinary joint ownership) እና ልዩ የጋራ ባለሃብትነት (Special joint ownership) በሚል ሊከፈል ይችላል፡፡ ተራ የጋራ ባለሃብትነት መብት መሰረቱ (Subject matter) ግዙፍነት ያላቸው የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችና ግዙፍነት የሌላቸው የንብረት መብቶች እንደ የፈጠራ መብት (patent right) ፣ የቅጂ መብት (copy right) እና የኢንዱስትሪ ንድፍ (Industrial design) ያሉ የንብረት መብቶችን መሰረት በማድረግ ሊሚቋቋም የሚችል የንበረት መብት ነው፡፡ የጋራ ባለሃብቶቹ ይህን የንብረት መብታቸውን ንብረቱ የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚሆንበት ግዜ በዋስትና (mortgage) ፣ የንብረት አገልግሎት (Servitude) ፣ አላባ በመስጠት (usufruct) ወይም የቀደምትነት መብት (pre-emptive right) አለኝ በማለት በጋራ ሃብቱ ላይ ያላቸውን መብት ሊሰሩበት የሚያስችላቸው የንብረት መብት ነው፡፡ ንብረቱ የሚንቀሳቀስ በሚሆንበት ግዜም በዋስትና (pledge) በአላባ (usufract) ወ.ዘ.ተ. በመስጠት በጋራ ሃብቱ ላይ ያላቸውን መብት ሊሰሩበት ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን በሁለትና ከዚያም በላይ ባሉ ሰዎች መካከል የጋራ ባለሃብትነት ግንኙነት አለ ብሎ ለማለት የሚኖረው መስፈርት የጋራ ባለሃብቶች ነን በሚሉት ሰዎች መካከል የባለቤትነት ጥቅም (ownership interest) ያላቸው ሰዎች መሆንና የጋራ ባለሃብትነታቸው በተመሳሳይ ንብረት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል፡፡(the joint ownership must exist over the same thing) እነዚህን ሁለት መመዘኛዎች ካላሟሉ ግን የጋራ ባለሃብቶች ሊባሉ አይችሉም፡፡ ለምሳሌ አንድ የንብረት ባለቤት (owner) እና የአላባ ተጠቃሚ (usufractuary) የሆነ ሰው በአንድ ንብረት ላይ የጋራ ባለሃብቶች (joint owners) ሊሆኑ አይችሉም፡፡የዚህ ምክንያትም አንደኛው በንብረቱ ያለው የሰፋ የባለቤትነት መብት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በንብረት ላይ ያለው መብት ጠበብ ያለ የአላባ መብት ስለሆነ በንብረት ላይ ያላቸው መብት የተለያየ አስከሆነ ድረስ የጋራ ባለሀብትነት (joint ownership) ሊመሰርቱ አይችሉም፡፡ ስለሆነም የጋራ ባለሀብትነት ግንኙነት አለ ብሎ ለማለት የባለቤትነት መብትንና ይህ መብት በዚያ ተለይቶ በታወቀ ንብረት ላይ ያለ የጋራ መብት መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡
የጋራ ባለሃብቶች መብቶች (Rights of Joint Owners)
የጋራ ባለሃብትነት መብት ከውል ወይም ከህግ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ይሄውም ስምምነቱን መሰረት ከሚያደርገው ሰነድ ወይም በጋራ ባለሃብቶች መካከል የተደረገ ስምምነት ባይኖርም እንኳ ህግ በራሱ ግዜ ያንን ንብረት የጋራ ሃብት በሚያደርግበት ግዜ ሊመሰረት ይችላል፡፡ ለምሳሌ በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 አንቀጽ 62 መሰረት የሚታይ የባልና የሚስት የጋራ ሃብት በሚሆንበት ጊዜ፣ የውርስ ንብረት እስከ ሚከፋፈል ድረስ ያለው የጋራ ባለሃብትነት መብት (የፍ/ብ/ህ/ቁ.1060-1064) ወይም በማቀላቀል ወይም በማዋሃድ መሰረት የተገኘ በጋራ ባለሃብትነት መብት በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1183 ወይም ከፍ/ብ/ህ/ቁ. 1257-1277 ባሉ ድንጋጌዎች መሰረት የሚገዛ የጋራ ባለሃብትነት መብት በሚኖርበት ግዜ መብቱ የመነጨው ከህግ ይሆንና ሰዎቹ የጋራ ባለሃብቶች ይሆናሉ፡፡ ከዚህም በመነሳት የጋራ ባለሃብቶች ከንብረት ህጉ አኳያ ሊኖራቸው የሚችል የጋራ እና የተናጠል መብቶችንና ገዴታዎችን በዝርዝር ስናይ፡-
ብዙውን ግዜ ከዚህ መብት ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ የሚነሳው ጥያቄ ከአደጋ ለመከላከል ወጪውን የጠየቀው ስራ ውጤታማ ባይሆንና የጋራ ሃብቱ ቢወድም ሌሎቹ የጋራ ሃብት ባለድርሻዎች ይህን ወጪ የመተካት ግዴታ አላቸውን? የሚል ሲሆን ሌላውም የጋራ ሃብቱ በሙሉ ወይም በከፊል ከአደጋው ቢተርፍም ለዚህ ሲባል በአንደኛው ባለድርሻ የወጣው ወጪ ከጋራ ሃብቱ ዋጋ የበዛ በሚሆንበት ግዜስ የጋራ ባለሃብቶቹ ይህን ወጪ የመሸፈን ግዴታ አላቸውን? የሚሉ ናቸው፡፡ በመጀመርያው ጥያቄ ዙሪያ የሚንሸራሸሩት ሃሳቦች የጋራ ሃብቱን ለመከላከል የወጣው ወጪ መታየትና መመዘን ያለበት ከድል (success) አንፃር ሳይሆን ከአላማው (purpose) አንፃር መሆን ይኖርበታል:: ፍ/ብ/ህ/ቁ.1268 ቢሆንም የንብረቱ ከአደጋ ወይም ከጉዳት ስለመከላከልና ለዚህ ሲባል ስለሚወጣ ወጪ እንጂ ስለውጤቱ የሚለው ነገር ስለሌላ የመከላከሉ ግብ መምታት እና አለመምታት ወጪውን ከመሸፈንና ካለመሸፈን ጋር አያይዘን ማየት የለብንም የሚል ነው፡፡ ለዚህ የመራከሪያ ሃሳብ እንደማጠናከሪያ የሚነሱት ሌሎች ሓሳቦችም ንብረቱን ካላተረፈው ወጪውን አንሸፍንም የሚል አካሄድ መከተል የጋራ ሃብቱ እየጋየም ቢሆን በግሉ አውጥቶ የሚከላከል ሰው ስለማይኖር የጋራ ባለሃብቶች ችላ እንዲሉ ስለሚያደርግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዘን ይቸላል የሚል ነው፡፡ ሌላውም አንድን በአደጋ ግዜ ረጋ ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ በሆነበት ግዜ የጋራ ሃብቱን ለማዳን ሲል አስፈላጊ የሆነውን ወጪ ያወጣ ባለድርሻ ወጪውን አንተካም ብሎ ማለት ምክንያታዊ አይደለም (unreasonable) የሚል ነው፡፡ የሁለተኛውን ጥያቄ በማስመልከት የሚሰነዘረው አስተያየትም የጋራ ንብረቱን ከአደጋ ለመከላከል የወጣው ወጪ ከጋራ ሃብቱ ዋጋ በላይ ቢሆንም ለዚህ የወጣን ወጪ የጋራ ባለሃብቶቹ መተካት አለባቸው የሚል ሲሆን ለዚህም በምክንያትነት የሚሰነዘረው አስተያየት የጋራ ሃብቱን ለመከላከል የወጣው ወጪ በመብዛቱ ብቻ እንዳላስፈላጊ ወጪ (unnecessary expense) መታየት የለበትም፡፡ የፍታብሄር ህጉ ይህን የሚያስብ ቢሆን ኑሮ አሁን እያነሳን ያለውን የባለ ድርሻው መብት በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1268 ያላስፈላጊ ወጪ የሚላቸውን ነገሮች በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1269 ለብቻ ባላስተናገዳቸው ነበር የሚል አስተያየት ነው፡፡ ሌላው ከባለድርሻው መብት ጋር ተያያዥነት ባለው መልኩ አንድ ግልፅ መሆን ያለበት ጉዳይ ግን አንድ ባለድርሻ ይህንን ለማድረግ ስልጣን ሳይኖረውና አስፈላጊ ባልሆነ ጊዜ ወጪ አድርጎ የጋራ ሃብቱን ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ከፍ እንዲል፤ (increase the economic value) እይታው እንዲያምር፤ (increase the appearances) ወይም የሃብቱ ጠቃሚነት እንዲጨምር (increase the usefulness) ቢያደርግም ወጪውን ሌሎች ባለድርሻዎች እንዲተኩለት መጠየቅ የማይችል መሆኑ ነው ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1269(1)) አንደዚሀ ያለ ድርጊት የፈፀመ ባለድርሻ ያለው አማራጭም ንብረቱን ቀድሞ ወደ ነበረበት መመለስ (restoration) ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1269(2))
የጋራ ባለሃብቶች ግዴታዎች (Duties of Joint Owners)
የጋራ ባለሃብትነት እንደሁሉም ህግ ፊት ዋጋ ያላቸው ተግባራት (juridical acts) ከስምምነት የሚመነጩ መብቶች እንዳሉት ሁሉ ግዴታዎችም እንዲሚኖሩት ይታወቃል፡፡ የጋራ ባለሃብትነቱ የመነጨው ከህግ በሚሆንበት ግዜም እንደዚሁ ከህጉ የሚመነጭ የጋራ ባለሃብቶች መብትና ግዴታ ይኖራል፡፡ ከንብረት ህጋችን አንፃር የጋራ ባለሃብቶችን ግዴታዎች ስንመለከት፡-
በአንድ የጋራ ሃብት ላይ ድርሻ ያለው ተጋሪ የጋራ ሃብት በሆነው ንብረት የመገልገል መብት (physical enjoyment) ቢኖረውም በዚህ መብቱ በሚሰራበት ግዜ ንብረቱ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ ሊገለገልበትና (shall not convert the purpose for which it was destined) የሌሎቹን ባለድርሻዎች በጋራ ንብረቱ የመገልገል መብትን በሚፃረር መንገድ (shall not impair their use rights) ሊገልገልበት አይገባም፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1263)
የጋራ ባለሃብቶቹ ከውሳንያቸው ለሚመነጭ ያልተጠበቀ ውጤት (consequence) ሃላፊ የመሆን ግዴታ አላቸው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1267)
በባለድርሻው አማካይነት በጋራ ሃብቱ ላይ ለደረሰ ጉዳት ከባሰ ውድመት ለማዳን ሲባል በጥፋት የወጣው ወጪ አስፈላጊ ወጪ (necessary expense) ቢሆንም ጥፋቱን የፈፀመው ባለድርሻ ወጪውን የመሸፈን ግዴታ አለበት፡፡ እንዲሁም ወጪው አላማ የሌለው (purposeless) ከሆነም ወጪውን የመሸፈን ግዴታ የሚወድቀው የዚህ ዓይነት ወጪ ባደረገው ባለድርሻ ላይ ነው፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1268(2) )
የጋራ ባለሃብቶቹ በጋራ ሃብቱ አማካይነት በሶስተኛ ወገኖች ሂወትና ንብረት ለሚያደርሱት ጉዳት ሃላፊዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ ተራ የጋራ ባለሃብትነት ከውል ወይም ከህግ ሊመነጭ የሚችል የንብረት መብትና ግዴታ ያለበት በሰዎች መካከል የሚፈጠር ግንኙነት ነው፡፡
የጋራ ሃብትን ስለማስተዳደር (Acts of management)
የጋራ ሃብትን ማስተዳደር ማለት በፍ/ብ/ህ/ቁ.1265 ያለውን አባባል ከፍ/ብ/ህ/ቁ.2204 ጋር አስተሳስረን ስንመለከተው የጋራ ሃብቱን ማቀብ (to preserve or maintain) ማለት ነው ብለን ልንተረጉመው እንችላለን:: ይህን ዘርዘር ባለ መልኩ ስናየው ደግሞ የጋራ ሃብትን ማስተዳደር የጋራ ሃብቱን ከሶስት ዓመት ላልበለጠ ግዜ ማከራየት፣ የተገኘውን ገቢ በሌላ ስራ ላይ ማዋል (investing the income) ምርትንና፣ የሚበላሹ ነገሮችን መሸጥን እንዲሁም በፍ/ብ/ህ/ቁ. 1266 የተዘረዘሩትን የጋራ ባለሃብቶች ሙሉ ድምፅ በማግኘት ሲወሰን የጋራ ሃብቱን መሸጥ (to dispose of) ፣ በዋስትና (mortgage or pledge) በኣላባ (usufruct) መስጠትና የጋራ ሃብቱ የተቋቋመበትን አላማ መለወጥ እንደ አስተዳደራዊ ስራ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ እንዲሁም በፍ/ብ/ህ/ቁ.1266 ከተዘረዘሩት ነገሮች ውጭ በፍ/ብ/ህ/ቁ.1265 ስር በሚወድቁ ጉዳዮች ላይ የጋራ ባለሃብቶቹ በድምፅ ብልጫ ውሳኔ ያገኘን ጉዳይ እንዲተገበር ማድረግ እንደ አስተዳደራዊ ስራ (act of management) ሊወሰድ ይችላል፡፡ የጋራ ባለሃብትነቱ መብት መሰረት ውል በሚሆንት ጊዜ ውሉ በፅሑፍ ሆኖ ተዋዋይ ወገኖች ስለሚኖራቸው መብት፤ ግዴታና የንብረቱ አስተዳደር ምን መሆን እንዳለበት መግለፅ ይኖርበታል:: (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1277ን ከ1282 እና 1283) የጋራ ባለሃብትነት የሚመነጨው ከህግ በሚሆንበት ግዜም የጋራ ባለሃብቶቹ መብትና ግዴታ የሚመነጨው ይህን መብት ከሚያስገኘው ወይም ግዴታን ከሚጥለው ህግ ነው፡፡
የማይንቀሳቀስ ንብረት የጋራ ባለሃብቶች ከመጀርያው የጋራ ሃብቱን አስተዳደር መሰረት በማድረግ የሚፈጠሩትን ያለመግባባቶች በድርድር (arbitration) ለመፍታት ሊሰማሙ ይችላሉ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1275 እና 3307-3346) ባለድርሻዎቹ ሳይስማሙ ከቀሩ ፍ/ቤት አስተዳደሪ ሊሾምላቸው ይችላል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1273) ስለሆነም የጋራ ሃብት የማስተዳደር ስልጣን ከውል ወይም ከሕግ ሊመነጭ የሚችል ሆኖ በጋራ ባለሃብቶች መካከል ያለመስማማት ማለትም ሙሉ ድምፅ (unanimous vote) ወይም አብላጫ ድምፅ (majority vote) መሰጠት ባለባቸው ጉዳይ የሚፈለገውን ድምፅ ሳይሰጡ የቀሩ እንደሆነ ጉዳያቸውን በመመስረቻ ውላቸው ባስቀመጡት የችግር አፈታት መንገድ እልባት እንዲያገኝ ይደርጋል፡፡ ይህ በማይሆንበት ጊዜ ደግሞ ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ እልባት የሚያገኝ ይሆናል ፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1265፤1266 እና1277(2) )
የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ ስለመሆን
የጋራ ባለሃብትነት መብትና ግዴታ እንደ ሁሉም በህግ ፊት ዋጋ ያለው ተግባር ከውል ሊመነጭና ባለ መብቶቹ ሲሰሩበት ከቆዩ በኃላ ይህ መብትና ግዴታ ቀሪ የሚሆንበት ማለትም ህግ ፊት ዋጋ ሊያጣ የሚችልበት ጊዜ አለ፡፡ መሰረቱ ህግ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ህግ አውጪው ህጉን በሚለውጥበት ጊዜ መብቱ ህጋዊ መሰረት (legal standing) የሚያጣበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህም መሰረት የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ የሚሆኑባቸው መንገዶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ውስደን ያየን እንደሆነ፡-
ü የጋራ ባለሃብቱ ድርሻውን ለሌሎቹ ባለድርሻዎች በነፃ ፈቃዱ ሲተው (surrender) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1262)
ü የጋራ ሃብቱ ክፍፍል ሲደረግበት፡፡ (partition) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1264)
ü ድርሻየን ትቻለሁ ሲል፡፡ (renunciation) (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1268(3))
ü ተቃራኒ ስምምነት ቢኖርም የሚንቀሳቀስ ንብረት ሲሆንና የጋራ ባለሃብቱ በሚያቀርበው ጥያቄ ንብረቱ በግልፅ ሓራጅ ሲሸጥ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1271)
ü የጋራ ሃብቱ የማይንቀሳቀስ ሆኖ ተቃራኒ ስምምነት ከሌለና ለመከፋፈል የማይቻል ከሆነ ወይም ንብረቱን መሸጥ ተስማሚ አይደለም ተብሎ በፍርድ ቤት ካልተወሰነ በስተቀር የጋራ ሃብቱ ሲሸጥ ወይም ሲከፋፈል የጋራ ባለሃብትነቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 1272-1274)
ü የጋራ ባለሃብቶቹ በራሳቸው ስምምነት ውላቸው እንዲቀር ሲያደርጉ ወይም ህጉ በሚያዘው መሰረት የጋራ ሃብቱ ክፍፍል ሲጠናቀቅ፡፡ ለምሳሌ የጋራ ሃብቱ የውርስ ሃብት በሚሆንበት ጊዜ በፍ/ብ/ህ/ቁ1079(1) መሰረት የንብረቱ ክፍፍል ሲጠናቀቅ፡፡
ü የጋራ ባለሃብትነት ቀሪ በሚሆንባቸው ሌሎች ሁኔታዎች ቀሪ ሲሆን፡፡ (ፍ/ብ/ህ/ቁ.1188-1192)
ü ለጋራ ባለሃብትነት መብት መኖር መሰረት የሆነው የጋራ ንብረት ሲወድም ግንኙነቱ ቀሪ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ (ፍ/ብ/ህ/ቁ 1304)
ü
ስለዚህ ተራ የጋራ ባለሃብትነት (ordinary joint ownership) ከውል ወይም ከህግ የሚመጣ ንብረትን መሰረቱ በማድረግ የሚፈጠር መብትንና ግዴታን ያዘለ ግንኙነት ነው፡፡ በመሆኑም በህገ-መንግስቱና ከዚያ በታች ባሉ ሌሎች ህጐች ጥበቃ የተደረገለትና በአንድ ወቅት የጋራ ባለሃብቶቹ በመብታቸው ሲሰሩበት ከቆዩ በኃላ ቀሪ የሚሆን ወይም መብቱም ሆነ ግዴታው ተፈፃሚነት ሊያጣ የሚችል የኢኮኖሚ ትስስር ነው፡፡