ያንድ ነገር ሙሉ ክፍሎች (ፍ/ሕግ ቁ.1131-1134)

 

እንደሚታወቀው አንድ የማይንቀሳቀስ ንብረት የምንለው ከተለያዩ ነገሮች የተሰራ ወይም የተገነባ ነው። በሌላ ኣባባል የተለያዩ ነገሮች ቅልቅል ወይም ስሪት ወይም ውህደት ውጤት ነው ማለት ይቻላል። ነገሮቹ የተወሃዱ ወይም ተያይዘው የተገነቡ በመሆናቸው በዋናው ንብረት/ነገር/ ወይም በሙሉ ክፍሉ ነገር ላይ ጉዳት ሳይደርስበት ሊለያይ የማይችል ነው። አንድ ነገር የሌላ ነገር ሙሉ ክፍል (intrinsic element) ነው ለማለት በሁለት መንገድ ሊገለፅ የሚችል መሆኑ ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል (ቁ.1132)።

1)ያ ነገር በልምድ የዋናው ነገር /ንብረት/ ሙሉ ክፍል ነው ሲባል

ለምሳሌ (ሀ) አንድ ሰው መኪና ገዝቷል የተባለ እንደሆነ በልምድ ኣባባል ጐማውንም የሚያጠቃልል ነው።

     ለ) የአንድ ቤት ሰርቪስ ወይም ሽንት ቤት በልምድ ኣባባል የዋናው ቤት ሙሉ ክፍል እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። እዚህላይ ልምድ ስንል በተደጋጋሚ የተሰራበትና የታየ ነገር ማለትመሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።

 2)ከሌላ ንብረት ጋር የተወሃደ ወይም የተያያዘ ሆኖ ከተወሃደበት ንብረት ለመለያየት ሲያስፈልግ በዋናው ነገር /ንብረት/ ወይም በሙሉ ክፍሉ ላይ ጉዳት ካልደረሰ በቀር ሊለያይ የማይችል ሲሆን ነው። ይህ የደረሰው ጉዳት /ንብረቱ ሲለያይ/ ንብረቱ የሚሰጠው ጥቅምና አገልግሎት ስለመቀነስ ወይም ስላለ መቀነሰ ግምት ውስጥ የሚገባ አይደለም።

 

በተጨማሪ ዛፎችና ሰብሎች በልዩ ሁኔታ የመሬቱ ሙሉ ክፍሎች እንደሆኑ በፍ/ሄር ሕጉ ተካትተዋል (ፍ/ሕግ ቁ.1133) ። ይኸውም ከመሬት ሳይለያዩ በሚቆዩበት ጊዜ የመሬቱ ሙሉ ክፍሎች እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ። የመሬቱ ሙሉ ክፍሎች መሆናቸውን የሚያቋርጡ፤

 

ሀ/ ከመሬቱ ጋር ሲለያዩ ሆኖ ራሳቸውን የቻሉ ኣካላዊ /ግዙፋዊ/ ህልውና ያላቸው ተንቀሳቃሽ ንብረት ሲሆኑ፣

ለ/ ከመሬት ጋር ሳይለያዩ በውል በግልፅ ሁኔታ ወደ ሌላ ሰው የተላለፉ እንደሆነ ነው።

   አንድ ነገር የሌላ ነገር ሙሉ ክፍል ነው ማለት ምን ሕጋዊ ውጤት ያስከትላል? (ፍ/ሕግ ቁ.1134)

 

 1. 1)አንድ የተለየ ሃብት /ንብረት/ መሆኑን ያቋርጣል። ዋናው ነገር የተሸጠ ወይም በሌላ መንገድ ወደ ሌላ ሰው የተላለፈ እንደሆነ ያ ሙሉ ክፍል የተባለውን ነገርም ከዋናው ነገር አብሮ ይተላለፋል።
 2. 2)የአንድ ነገር ሙሉ ክፍል ከመሆናቸው በፊት ሶሰተኛ ወገን በእነሱ ላይ የነበረው መብት የአንድ ነገር ሙሉ ክፍል ከሆኑ በኃላ ግን ይቋረጣል።
 3. 3)ሶሰተኛው ወገን በሌላ መንገድ መብቱን ማስከበር እንደሚችል ነው።

ለምሳሌ ከውል ውጭ በሚኖር ሓላፊነት መጠየቅ ይችላል። እንዲሁም ያለ ኣግባብ በመበልፀግ ሓላፊነት መጠየቅ ይችላል።

 

አንድ መላምታዊ ጉዳይ በመውሰድ ነገሩን የበለጠ ግልፅ ማድረግ ይቻላል። አቶ “ሀ” በገንዘቡ አሸዋ ገዝቶ ግቢው አጠገብ አስቀሙጧል። አቶ “ለ” ደግሞ አቶ “ሀ”ን ሳያስፈቅድ የአሸዋው ግማሽ የሚያክል በመውሰድ ለቤቱ መስርያ ተጠቅሞበታል። አቶ “መ” በበኩሉ የተሰራው ቤት ከአቶ “ለ” ገዝቶታል። በዚህ ሁኔታ አቶ “ሀ” አቶ “መ”ን በመክሰስ የገዛኸው ቤት የእኔ አሸዋ ተጠቅመው የሰሩት ስለሆነ አሸዋዬን መልስልኝ ሊለው አይችልም። ማድረግ ያለበት ነገር ቢኖር ሌላ ሕግ ተጠቅሞ አቶ “ለ”ን በመክሰስ አሸዋየን መልስልኝ ወይም የጉዳት ካሳ ክፈለኝ ነው ማለት ያለበት።

 

ደባሎች (ተጨማሪ) ነገሮች (Accessories) (ፍ/ሕግ ቁ.1135-1139)

 

ተጨማሪ ነገር ማለት ለዋናው ንብረት በቀዋሚነተ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል የንብረት ዓይነት ነው። ከፍ/ሕግ ቁ.1136 መረዳት እንደሚቻለው የተጨማሪ ነገር ትርጉም ሁለት መመዘኛዎች ይዞ ይገኛል፤

 

 1. 1)የንብረቱ ባለቤት ወይም የአላባ ተጠቃሚ የሆነ ሰው አንድ ነገር የዋናው ነገር /ንብረት/ተጨማሪና አገልጋይ ብሎ የመደበው መሆን አለበት፣
 2. 2)ያ ተጨማሪ ነገር ለዋናው ነገር ለማገልገል በቀዋሚነት የመደበው መሆን አለበት።

ለምሳሌ፦ አንድ የመኪና ባለቤት ክሪክ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ክሪኩ በተጨማሪነት በመመደብ መኪናዋ እንድትጠቀምበትና እንድትገለገልበት በሚል ሃሳብ መሆኑን ለመገመት አያዳግትም።

 

ስለዚህ በሬዎች ለእርሻ መሬት፣ ማሽነሪ ለኢንዱስትሪ፣ ቁልፍ ለቤት በር፣ የመኪና መለዋወጫ ለተሽከርካሪዎች ተጨማሪዎች ናቸው። ተጨማሪ ነገር ለተወሰነ ጊዜ ከዋናው ንብረት ቢለይም የተጨማሪነት ባህሪው አይለቅም /ፍ/ሕግ ቁ.1137/።

 

አንድ ነገር የሌላ ነገር ተጨማሪ ነገር ነው ማለት የሚኖረው ሕጋዊ ውጤት ምንድነው? /ፍ/ሕግ ቁ. 1138/

 

 1. 1)አንድ ነገር ተጨማሪ ነገር ከመሆኑ በፊት ሶሰተኛ ወገኖች በዚህ ነገር ላይ መብት የነበራቸው እንደሆነ የሌላ ንብረት ተጨማሪ ከሆነ በኃላም መብቱ እንደተጠበቀ ይቆያል። ዋናው ነገር /ንብረት/ ቢሸጥም እንኳ ከዋናው ንብረት ጋር ያለ ተጨማሪ ነገር እንደተሸጠ አይቆጠርም። ይህ የሆነበት ምክንያትም ዋናው ንብረትና ተጨማሪው ነገር የየራሳቸው ህልውና ያላቸው በመሆኑ ነው።

 

 1. 2)ነገሩ የሌላ ንብረት ተጨማሪ ከመሆኑ በፊት በፅሑፍ በተደረገ ውል የዋናው ነገር ተጨማሪ አለመሆናቸው የሚገልፅ በማይኖርበት ጊዜ ግን በቅን ልቦና ንብረቱን ያገኘ ሶሰተኛው ወገን መብት የተጠበቀ ነው።

ለምሳሌ፦      አቶ “ሀ” የፋብሪካ ባለቤት ነው

        አቶ “ለ” የጭነት መኪና ባለቤት ነው

አቶ “ለ” መኪናውን አቶ “ሀ” እንዲጠቀምበት ሰጠው

አቶ “መ” ከአቶ “ሀ” ፋብሪካ እና መኪና (የአቶ “ለ” የነበረ መኪና ማለት ነው) ገዛ በዚህ ሁኔታ አቶ “ሀ” እና አቶ “ለ” መኪናውን ወደ ሌላ እንዳይተላለፍ የሚል ውል ካልነበራቸው በስተቀር አቶ “ሐ” የመኪናው ባለሃብት ይሆናል።

 

 1. 3)የሚያጠራጥር ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ ለዋናው ነገር /ንብረት/የሚመለከቱ መብቶች ወይም ተግባሮች ከእሱ /ከዋናው ነገር/ ጋር ተጨማሪ /ደባል/ሆኖው ለሚገኙ ነገሮችም የሚመለከት ወይም የሚሰራ ይሆናል/ፍ/ሕግ ቁ.1135/።

 

ለምሳሌየመኪና መለዋወጫ /አስኳርታ/ጐማ ወይም ክሪክ ከመኪናው ጋር በግልፅ ውል የተሸጠ እንደሆነ አብረው እንደተሸጡ ይቆጠራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ጐማው በመኪናው ውስጥ የተገኘ እንደሆነ አጠራጣሪ ስለሚሆን ከመኪናው ጋር እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ ነገር ፍትሓዊ መሆኑ ወይም ስላልመሆኑ ግን አነጋጋሪ ሊሆን ይችላል።

 

 

 1. 4)ተጨማሪው /ደባሉ/ ነገር ለቀድሞው ባለሃብት የሚመለስለት እንደሆነ ከዋናው ንብረት መለያየት የለበትም የሚሉ በቅን ልቦና የገዙ ሶሰተኛ ወገኖች በሸጡላቸው ሰዎች ላይ የጉዳት ካሳ ጥያቄ የማቅረብ መብታቸውን የተጠበቀ ነው።

 

ከዚህ ጋር በተያያዘ በፍ/ሕግ ቁጥር 1138(1) እና (2) ላይ ስለሶሰተኛ ወገን የተቀመጠ ነገር አለ። ቢሆንም በሁለቱ (ንኡስ ቁ.1 እና 2) መካከል ያለ ልዩነት ግልፅነት የጐደለው ይመስላል። በፀሓፊው እምነት በሁለቱ ንኡስ አንቀፆች አንድ ተጨማሪ ነገር ከዋናው ነገር ተደርቦ በሚሸጥበት ጊዜ ስለሚኖረው ውጤት የሚያወሱ ናቸው።

 

ይኸውም፦

በቁ.1138 (1) ላይ ሶሰተኛ ወገን የሚለውን የሚያመለክተው የተጨማሪ ነገር ባለሃብትን ሆኖ ተጨማሪው ነገር ከዋናው ነገር/ንብረት/ጋር ከመያያዙ በፊት የነበረው መብት እንደተጠበቀ መሆኑን የሚያስረዳ ነው። በሌላ አገላለፅ የዋናው ነገር ለሌላ ሰው መተላለፍ የደባሎች /ተጨማሪ/ ነገሮች አብሮ መተላለፍ አያመለክትም። ምክንያቱም የየራሳቸው ህልውና ስላላቸው ነው።

 

በቁ.1138 (2) ላይ ሶሰተኛ ወገን የሚለውን ነገር የሚያመለክተው ግን ዋናው ነገር የተላለፈለትን ሰው ነው። በንኡስ አንቀፅ 1 ላይ የተመለከተውን የሶሰተኛ ወገን

መብት /የተጨማሪ ነገር ባለሃብት መብት/የዋናው ነገር ባለሃብትና የተጨማሪ

ነገር ባለሃብት በፅሑፍ አድርገው በግልፅ ካልተዋዋሉ በስተቀር በቅን ልቦና የገዙ

ሰዎች ተቃውሞ ሊቀረብባቸው አንደማይችል ነው። ከዚህ መረዳት የሚቻለው

ንኡስ አንቀፅ 2-የንኡስ-አንቀፅ-ልዪ-ሁኔታ መሆኑን ነው።

 

አንድ ነገር በተጨማሪነት/በደባልነት/ ከሌላ ነገር /ከሚንቀሳቀስ ወይም ከማይንቀሳቀስ ንብረት/ ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ካየን ዘንድ እንዴትስ ተጨማሪ መሆኑን ይቀራል የሚል ነጥብ ደግሞ መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው። የፍ/ሕግ ቁጥር 1139 የተጨማሪነት ሁኔታ የሚቀርበት ጊዜ መቼ አንደሆነ ለማመልከት ሁለት ሁኔታዎች ደንግጎ ይገኛል

 1. ተጨማሪው ነገር ከዋናው ነገር/ንብረት/ ጋር የተወሃደ ወይም የተደባለቀ እንደሆነና ለማለያየትም ጉዳት ወይም ብልሽት ሳይደርስበት የማይቻል ሲሆን፤
 2. የተጨማሪው ነገር ባለሃብት ከአሁን ጀምሮ ተጨማሪ ነገር ሊባል አይገባውም ወይም የዋናው ነገር አካል ሆኖዋል ሲል ሓሳቡን የገለፀ እንደሆነ ነው።