- Details
- Category: Property Law
የንብረት አመዳደብ ወይም ክፍፍል
ተንቀሳቃሽ ወይም የማይንቃሳቀስ በሚል የተደረገ የንብረት ክፍፍል
ይህ ክፍፍል መሰረት የሚያደርገው ግዙፋዊ/ቁሳዊ ህልውና ያላቸውንና በስሜት ህዋሶቻችን ሊታወቁ የሚችሉትን ነገሮች ናቸው።
ተንቀሳቃሽ ንብረቶች፦
ተንቀሳቃሽ ንብረቶች የምንላቸው በራሳቸው ወይም በሰው ጉልበት ጉዳት ሳይደርስባቸው ወይም ተፈጥሮኣዊ ባህሪያቸውን ሳይቀይሩ ሊጓዙ ወይም ሊጓጓዙ የሚችሉ ግዙፋዊ ህልውና ያላቸው ናቸው። ስለዚ አንድ ንብረት ተንቀሳቃሽ ነው ለማለት፦
ሀ/ ንብረቱ ግዙፋዊ ህልውና ሊኖሮው ይገባል ወይም በስሜት ህዋሶቻችን ልንገነዘበው
የሚችል መሆን አለበት። ምሳሌ፦ ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ መፅሓፍ፣
ለ/ በራሱ ሊንቀሳቀስ /ሊጓዝ/ የሚችል መሆን አለበት። ምሳሌ ፦ ተሽከርካሪ ወይም ሰው ተሸክሞ የሚያንቀሳቅሰው መሆን አለበት።
ሐ/ ንብረቱ በራሱ ወይም በሰው ጉልበት ሲንቀሳቀስ ጊዜ ተፈጥሮኣዊ ባህሪው የማያጣ ወይም የማይለውጥ መሆን አለበት።
በ “ለ” እና “ሐ” የተቀመጡትን መመዘኛዎች ግልባጭ ትርጉም (a contrari0 interpretation) ሲታይ አንድ ነገር ሊንቀሳቀስ የማይችል የሆነ እንደሆነ ወይም ተፈጥሮኣዊ ባህሪው ሳይቀይር የማይንቀሳቀስ እንደሆነ ተንቀሳቃሽ ንብረት ሊባል እንደማይችል ነው። ይህ ማለት ግን የማይንቀሳቀስ ንብረት ነው ማለት አይደለም። በተፈጥሮው ተንቀሳቃሽ ንብረት ኖሮ በኃላ የማይንቀሳቀስ ንብረት አካል እንዲሆን በመደረጉ ምክንያት ተንቀሳቃሽ ንብረት መሆኑን ስለሚያቋርጥ ነው።ምክንያቱም የማይንቀሳቀስ ንብረት የሚባሉ መሬትና ህንፃ በመሆናቸው ነው።
የፍ/ሔር ሕጉ ከተጠቀሱት ውጭ በተፈጥሮ ሓይል /በነፋስ፣ ጎርፍ ወዘተ/ የሚንቀሳቀሱትን ነገሮች እውቅና የሰጠ አይመሰልም። ሆኖም ግን አንዳንድ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በሕግ እንደ ተንቀሳቃሽ ንብረት ተደርገው የሚወስዱበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። ለምሳሌ ፦ ዛፎች ወይም የእህል ሰብል ከመቆረጣቸው ወይም ከመታጨዳቸው በፊት ለሌላ ሰው የተላለፉ እንደሆነ እንደ ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚቆጠሩ ሲሆን ይህ ሁኔታ በሌለበት ጊዜ ግን እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ተደርገው ይወስዳሉ።
ተንቀሳቃሽ ንብረቶችም እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሚወሰዱበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ለምሳሌ ትራክተሮች አንድ እርሻ ለማልማት በቀዋሚነት የተመደቡ እንደሆነ ከመሬቱ ጋር እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ሊወሰዱ ይችላሉ።
የማይንቀሳቀስ ንብረት፦
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የምንላቸው በተለያየ ክፍል ተክፈለው ሊታዩ ይችላሉ። ከእነዚህ መካከል መሰረታዊ ናቸው የሚባሉት እንደሚከተለው ቀርበዋል።
- 1.በተፈጥሮአቸው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች (Immovables by their nature)
- 2.ተንቀሳቃሽ ንብረት ሆኖ ከማይንቀሳቀስ ንብረት ጋር ባለው ግንኙነትና ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር ሲታይ እንደማይንቀሳቀስ ንብረት የሚወስድ (Immovables by their distination)
- 3.መብቶችን ከማስከበርና ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር ሲታይ እንደማይንቀሳቀስ ንብረት የሚወስድ (Immovables by the object to which they apply)
የእነዚህ ዝርዝር ይዘት እንደሚከተለው ለማየት እንሞክራለን።
- 1.በተፈጥሮአቸው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች
በተፈጥርአቸው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሚባሉ እንደመሬት፣ ህንፃዎች፣ ዛፎች፣ ወዘተ የመሳሰሉት ናቸው።
ሀ/ዛፎች መሬት ላይ እስከበቀሉ ድረስ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ናቸው፦
ከመሬት ውጭ በሌላ ዕቃ ውስጥ የበቀሉ (እንደ አበባ የመሳሰሉ) ሲሆን ግን ተንቀሳቃሽ ንብረት ይሆናሉ። ዛፎች መሬት ላይ ገና በቁማቸው እያሉ ወይም ሳይቆረጡ በሽያጭ ወይም በሌላ መንገድ ወደ ሌላ ሰው የተላለፉ እንደሆነ ግን እንደተንቀሳቃሽ ንብረት ነው የሚወስዱት (movables by anticipation) ለምሳሌ፦ አቶ “ሀ” የበሰለ ግን ደግሞ ያልታጨደ ጤፍ ለአቶ “ለ” ቢሸጥለት ጤፉ ገና ያልታጨደ ቢሆንም እንደ ተንቀሳቃሽ ንብረት ይቆጠራል። ይህ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ሕግ የሰዎችን ግንኙነት ለመቆጣጠር ሲል ያስቀመጠው ፈጠራ መሆኑን ነው።
ለ/ ከመሬት ጋር ተያይዘው የተሰሩ ህንፃዎችና ቤቶች፦
እንደሚታወቀው ህንፃዎችን ለመገምባት የተለያዩ ነገሮች ያስፈልጋሉ። ህንፃውን ለመስራት የሚጠቅሙ ነገሮች በተናጠል ሲታዩ ለዚህ የህንፃ ስራ መስሪያ ከመዋላቸው በፊት ወይም የድሮ ባህሪያቸውን ሲታይ የሚንቀሳቀሱ ንብረቶች የነበሩ ቢሆንም በህንፃው ውስጥ ከተካተቱ በኃላ ግን የህንፃው ወይም የቤቱ ኣካል ስለሚሆኑ እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ተደርገው ይወስዳሉ።
- 2.ተንቀሳቃሽ ሆኖው ከማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ጋር ባላቸው ግንኙነትና ከሚሰጡት ጥቅም አንፃር ሲታይ እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሚወስዱ፦
እነዚህ ንብረቶች በተፈጥሮአቸው ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ሆኖው በሕግ ፈጠራ ወይም እውቅና ብቻ እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የሚቆጠሩ ናቸው። ለምሳሌ ፦ በሬዎች፣ ትራክተሮችና ሌሎች መሳሪያዎች በእርሻ ስራ ላይ ሲሰማሩ ወይም ለዚህ ስራ ተብለው ሲመደቡ፤ አንድ ፋብሪካ ስራውን ለማከናውን መኪና፣ ሌሎች ማሽኖች ወዘተ ስለሚያስፈልጉት እነዚህ ተሽከርካሪዎች እና ማሽኖች ከፋብሪካው ጋር አብረው እንደማይንቀሳቀስ ንብረት ይቆጠራሉ። እነዚህ የእርሻና የፋብሪካ ስራ ለማከናወን የሚጠቅሙ ንብረቶች ተጨማሪ ነገሮች (Accessories) ተብለው ይጠራሉ። ተጨማሪ ነገሮች (accessories) እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ተደርገው እንዲቆጠሩ ለማድረግ ሁለት ሁኔታዎች ሊሟሉ ይገባል።
ሀ/ በተፈጥሮው የማይንቀሳቀሰው ንብረትና ያ ተጨማሪ ነገር ከአንድ ፓትሪሞኒ የመጡ (የአንድ ሰው ንብረት) መሆን አለባቸው።
ለ/ ያ በተፈጥሮው ተንቀሳቃሽ የሆነ ንብረት ለማይንቀሳቀሰው ንብረት አገልግሎት የዋለ መሆን አለበት። ለምሳሌ ፦ አንድ የእግር መኪና በቀጥታ ለፋብሪካው የስራ ክንውን የሚያገለግል ስለማይሆን እንደማይንቀሳቀስ ንብረት ተደርጎ አይቆጠርም።
በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ የሚኖር ሕጋዊ ተፈፃሚነት በተጨማሪ ነገሮች ላይም ተፈፃሚ ይሆናል። ለምሳሌ፦ አንድ ፋብሪካ በፋብሪካ ውስጥ (ለፋብሪካው የስራ ተግባር) የምታገለግል መኪና ጋር በሞርጌጅ ሊያዙ ይችላሉ። ተጨማሪ ነገሮች በባለቤቱ አማካኝነት ከማይንቀሳቀሰው ንብረት የተለዩ እንደሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የመሆናቸው ጉዳይ ያቆማሉ።
3.መብቶች ከማስከበርና ከሚሰጠው ጥቅም አንፃር ሲታይ እንደማይንቀሳቀስ ንብረት የሚወስድ (Immovables by the object to which they apply)
እነዚህ እንደማይንቀሳቀሱ ተደርገው የተወሰዱ ንብረቶች በማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ላይ ተፈፃሚነት ያላቸው መብቶች ናቸው። እዚህ ላይ ስለ እነዚህ መብቶች ተንቀሳቃሽ መሆን ወይም አለመሆን መናገር አይቻልም። ሆኖም ግን እነዚህ መብቶች ተግባር ላየ ሊውሉ የሚችሉት የማይንቀሳቀሰውን ንብረት በመጠቀም አማካኝነት የሆነ እንደሆነ መብቶቹ እንደማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ተደርገው ይወስዳሉ። ለምሳሌ፦ የንብረት አገልግሎት መብት (servitude right) እና በአለባ የመጠቀም መብት (usufructuary right) መጥቀስ ይቻላል።
አንድ ንብረት ተንቀሳቃሽ እና የማይንቀሳቀስ በሚል መከፋፈል ያለው ፋይዳ
- 1.ንብረቱ ለማግኘት የምትጠቀምበት መንገድ በሁለቱ መካከል ልዩነት ያለ በመሆኑ፦
- ተንቀሳቃሽ የሆነ ንብረት ዕቃውን በቀጥታ በመያዝ (by occupation) ባለቤት መሆን ይቻላል። ለምሳሌ፦ ንብ የያዘ፣ በንብረቱ ውስጥ ተቀብሮ የቆየ ዕቃ ያገኘ፣ የወደቀ ዕቃ ያገኘ የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት /ባለሃብት/ ይሆናል /ፍ/ሕግ ቁጥር 1151…ወዘተ/
- የማይንቀሳቀስ ንብረት የሆነ እንደሆነ ግን በይርጋ ጊዜ ካልሆነ በስተቀር (usucaption) /ፍ/ሕግ ቁጥር 1168/ ፤ የማይንቀሳቀሰውን ንብረት በመያዝ ብቻ (by occupation) ባለሃብት መሆን አይቻልም።
- 2.በሁለቱ መካከል የባለሃብትነት መብት መተላለፍያ መንገድ ይለያያል፦ ይኸውንም የሚንቀሳቀስ ንብረትን ከአንድ ሰው ወደ ሌላ ሰው ሊተላለፍ የሚችለው ዕቃውን በመስጠት በቀላሉ ማስተለፍ ይቻላል። (ፍ/ሕግ ቁጥር 1185, 2274, 2395 እና 2444(1) መጥቀስ ይቻላል) ።
- የማይንቀሳቀስ ንብረት በተመለከተ ግን በሕግ የተደነገጉትን ፎርማሊቴዎች ካልተሟሉ በስተቀር ንብረቱን ከአንድ ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ አይቻልም። ንብረቱን ለማስተላለፍ መነሻ የሆነውን ውል በፅሑፍ መሆን አለበት፣ ውል የማዋዋል ስልጣን ባለው ኣካል ፊት መደረግ አለበት፤ እንዲሁም በሚመለከተው ኣካል ሊመዘገብ ይገባል (ፍ/ሕግ ቁጥር 1723, 2877 – 2879 በምሳሌነት ይጠቀሳል) ። እንዲሁም ፍ/ሕግ ቁጥር 2443 መጥቀስ ይቻላል።
- 3.የዳኝነት ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት የተኛው ነው የሚለውን ለማወቅ ይጠቅማል፦
- ተንቀሳቃሻ ንብረትን በሚመለከት ክስ የሚቀርበው ከሳሽ በሚኖርበት፣ ወይም ውል ካለ ውሉ በተደረገበት ወይም ውሉ በሚፈፀምበት ቦታ በሚገኝ ፍርድ ቤት ነው። (ፍ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 24) ።
- የማይንቀሳቀስ ንብረትን ክስ የሚቀርበው ግን ለክሱ ምክንያት የሆነው የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚገኝበት ቦታ በሚገኝ ፍርድ ቤት ነው። (ፍ/ስ/ስ/ሕግ ቁጥር 25) ።
- 4.በዕዳ መያዣ ከመሆን ረገድም በሁለቱ መካከል ልዩነት ይታያል፦
- ተንቀሳቃሽ ንብረት ለዕዳ በመያዥነት (pledge) መስጠት የሚቻል ሲሆን (ፍ/ሕግ ቁጥር 2825…ወዘተ) ፤ (ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረት የሚባሉት እንደ መርከብ፣ አውሮኘላን ወዘተ ሞርጌጅ ማድረግ እንደተጠበቀ ነው) ። የማይንቀሳቀስ ንብረት በሚመለከት ግን ለዕዳ በመያዥንተ መስጠት የሚቻለው በሞርጌጅ (mortgage) አማካኝነት ነው። (በፍ/ሕግ ቁጥር 3041…ወዘተ)
- 5.በሁለቱ መካከል የይርጋ ጊዜ ልዩነት አለ፦
- ለተንቀሳቃሽ ንብረት በሕግ የተቀመጠለት የይርጋ ጊዜ አጭር ሲሆን /ለምሳሌ ፍ/ሕግ ቁጥር 1165, 1192/፤ ለማይንቀሳቀስ ንብረት ሕግ ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ ረዘም ያለ መሆኑን ነው /ፍ/ሕግ ቁጥር 1168/
- 6.በቅን ልቦና የአንድ ንብረት ባለይዞታ በመሆን የባለሃብትነት መብት ማግኘት፦ ተንቀሳቃሽ ንብረትን በቅን ልቦና ይዞታ ያደረገ ሰው የንብረቱ ባለሃብት መሆን ሲችል /ፍ/ሕግ ቁጥር 1161/፤ የማይንቀሳቀስ ንብረት ግን በቅን ልቦና ባለይዞታ በመሆን የንብረት ባለሃብትነት መብት ማግኘት አይቻልም።
- 7.የንብረት ባለሃብትነት መብት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሁኔታዎች ያስፈልጋቸዋል፦ የተንቀሳቃሽ ንብረት ባለሃብትነት መብትን ለማረጋገጥ የንብረቱ ባለይዞታ መሆን በራሱ እንደ ባለሃብት እንደሚስያገምት ነው /ፍ/ሕግ ቁጥር 1193/። የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለሃብትነትን ለማስረዳት ግን የባለሃብትነት ምስክር ወረቀት ማቅረብ ይጠይቃል/ፍ/ሕግ ቁጥር 1194-1196/።
- 8.በውርስ ወይም በስጦታ የተገኘ ንብረት የመውረስ ሁኔታ፦
ለአውራሹ በውርስ ወይም በስጦታ ከአባቱ ወይም ከአያቱ መስመር ወገን የመጣለትን የማይንቀሳቀስ ንብረት የእናት መስመር ለሆኑ ወራሾች በውርስ ማስተላለፍ አይቻልም። እንዲሁም ከእናቱ ወይም አያቱ መስመር ወገን የመጣለትን የአባት መስመር ለሆኑ ወራሾች በውርስ ማስተላለፍ አይቻልም (849,1088) ። የሚንቀሳቀስ ንብረት ለመውረስ ግን ለማይንቀሳቀስ ንብረት ውርስ የተቀመጠ ስርዓት መከተል ሳይስፈልግ ያለ ምንም ልዩነት በሕግ ቅድሚያ ያለኑዛዜ ወራሾች ለሆኑ ሰዎች ይተላለፋል።
- 9.የአንድ አካለ መጠን ያልደረሰ ህፃን ሞግዚት የህፃኑ ሃብት የሆነው የሚንቀሳቀስ ንብረት የመሸጥ ስልጣን የተሰጠው ሲሆን የማይንቀሳቀስ ንብረት ግን የሚያጠቃልል አይደለም (ፍ/ሕግ ቁጥር 289)