ይህ ሀላፊነት በእንግሊዝኛው /vicarious liability/ የሚባለው ነው፡፡ የተደነገገውም ከ2124 እስክ 2136 ባሉት ቁጥሮች ስር ነው፡፡ ሀላፊነትን የሚያስከትለው ተግባር የተፈፀመው በአንዱ ሰው ሲሆን ተጠያቂ የሚሆነው ግን ሌላ ሰው ነው፡፡ ሀላፊነት የሚያስከትለውን ተግባር የሚያከናውኑት ሦስት ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ እነሱም አካለ መጠን ያላደረሰ ልጅ፣ ሠራተኛ እና ደራሲያን /ፀሐፊዎች/ /authors/ ናቸው፡፡ ሠራተኛ የሚለው የመንግስት ሹም ሠራተኛ ወይም  ሌሎች ሠራተኞች ሊመለከት ይችላል፡፡ ለአካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች ተፈፃሚነት ያላቸው  ከቁጥር 2124 እና 2125 ሲሆኑ ለሠራተኛ ደግሞ ከቁጥር 2126 እስከ 2134 ያሉት ናቸው ስለደራሲ ደግሞ ቁጥር 2135 ይደነግጋል፡፡ ለአካለመጠን ላልደረሰ ልጅ ሀላፊ የሚሆኑት ወላጆችና ሌሎች ሲሆኑ ለሠራተኛ ደግሞ መንግስት ወይም አሠሪ ይሆናሉ፡፡ ለደራሲ ሀላፊ የሚሆነው አሳታሚው ነው፡፡ በመጨረሻም አንድ ነጥብ ግልፅ እናድርግ፡፡  ሀላፊነት የሚያስከትለውን ተግባር የፈፀሙ ሰዎች አላፊ  ሳይሆኑ ሌሎች ሀላፊ ይሆናሉ ማለት ተግባሩን የፈፀሙት በጭራሽ ተጠያቂ አይሆኑም ማለት አይደለም፡፡ ይህን ያህል ለመግቢያ ካልን ቀጥለን ነጥቦችን ዘርዘር አድርገን ለመመልከት እንሞክር፡፡

 

አካለ መጠን ያልደረሰ ልጅ ቁጥር /2124 /

 

በቅድሚያ አንድ ነጥብ ግለፅ አናድርግ በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2124 መሠረት አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ሀላፈነትን የሚያስከትል ሥራ የሰራ እንደሆነ በፍትሐብሔር በኩል ለተሠራው ሥራ አላፊ የሚሆነው አባት ነው በማለት ቅድሚያ አባትን ያስቀምጠዋል፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያት አባት የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ግን የኢፌዳሪ ህግ መንግስትንም ሆነ አዲሱን የተሻሻሉ የቤተሰብ ህጐችን የሚፃረር ነው፡፡ ለምሳሌ በኢፌዳሪ ህግ መንግስት አንቀፅ 34 /1/ መሠረት ባል አና ሚስት በጋብቻ ዘመን እኩል መብት ሲኖራቸው በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ አንቀፅ 5ዐ  መሠረት በቤተሰብ አመራር ረገድ ባልና ሚስት እኩል መብት አላቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ባልና ሚስት ልጆቻቸው በመልካም ስነምግባር እንዲታነፁ ተገቢ ትምህርት እንዲቀስሙና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጐች ሆነው እንዲያድጐ ለማድረግ መጣር  አለባቸው፡፡

 

ስለሆነም አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ሀላፊ በሚሆንበት ጊዜ አባትና እናት እኩል ሀላፊ መሆን አለባቸው እንጂ በመጀመሪያ ደረጃ አባት በሁለተኛ ደረጃ እናት መሆን የለባቸውም፡፡ ስለዚህ ይህ የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር ከኢፌዲሪ ሕገ መንግስትና ከተሻሻሉት የቤተሰብ ሕጐች አንፃር መቃኘት አለበት፡፡

 

ለአካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ሀላፊ መሆንን በሚመለከት የኮመን ሎው አገሮችና የሲቪል ሎው አገሮች የተለያዩ አቋም አላቸው፡፡ በኮመን ሎው አገሮች ለአካለመጠን ላልደረሰ ልጅ አባትን ወይም እናትን ሀላፊ ለማድረግ በአባት ወይም በእናት በኩል ጥፋት መኖሩን ማረጋገጥን ይጠይቃል፡፡ በሲቪል ሎው አገሮች ግን አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ ድርጊት ጉዳት ካደረሰ በወላጆች ዘንድ ጥፋቱ እንዳለ ይገመታል፡፡ ይህ ግምት ግን በተቃራኒ ማስረጃ ሊፈርስ የሚችል ግምት /ribufuble/ ነው፡፡

 

 

በእኛ ህግ ግን ሁለቱም አቋም ያለ ይመስላል፡፡ በቁጥር 2124 ስር አባት ወይም በ2125 /1/ ስር እናትን ሀላፊ ለማድረግ ጥፋትን ማረጋገጥ አያሰፈልግም፡፡ በቁጥር 2ዐ52 መሠረት ግን ወላጅን ወይም ሌላ አካለመጠን ያልደረሰ ልጅ አሳዳሪነት ወይም ጠባቂነት የተሰጠውን ሰው ሀላፊ ለማድረግ ጥፋትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

 

ሌላው ግልፅ መሆን ያለበት ነጥብ ደግሞ ወላጆች ወይም ሌሎች በቁጥር 2125 የተጠቀሱት ሰዎችና አካላት ሀላፊነት የፍትሐብሔር ሀላፊነት ብቻ ነው፡፡ አካለመጠን ያልደረሰው ልጅ የወንጀል ድርጊት ቢፈፅምና ቢረጋገጥበት ከ9 ዓመት በላይ ከሆነ በወንጀል ድርጊት ተጠያቂነቱ ወደ ሌሎች ሰዎች አይተላለፍም፡፡ በመጨረሻም ቁጥር 2124 አስመልክቶ በፍትሐብሔር ህግ አማርኛውና እንግሊዝኛ መሃል ልዩነት አለ፡፡

 

አማርኛው ልጁ ሀላፊነትን የሚያስከትል ሥራ የሰራ እንደሆነ በማለት የልጁ ሀላፊነት ከሥራ የሚመነጭ መሆኑን ሲደነግግ እንግሊዝኛው ግን /Where his minor child incurs a liability/ ስለሚል የልጁ ሀላፊነት ወይ ልጁ ጥፋተኛ በመሆኑ ሊመነጭ ይችላል ወይም ጥፋት ሳይኖርበት ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮች ባለቤት በመሆኑ ሊመነጭ ይችላል፡፡ ሌሎች ለልጁ ሀላፊ ተብለው በህግ ይገለፁ እንጂ ልጁም ከሀላፊነት አያድንም፡፡

 

የመንግስት አላፊነት ቁጥር  /2126/

 

 

በቁጥር 2126 /1/ መሠረት የመንግስት ሹም ወይም ሠራተኛ በራሱ ጥፋት በሌላው ሰው ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ኪሣራውን ለመክፍል ይገደዳል፡፡ ይህ ጥፋት በሁለት አጋጣሚ ሊደረግ ይችላል፡፡ አንድ አጋጣሚ  የመንግስትን ሥራ ሲሠራ ሊሆን ይችላል፡፡ የግል ሥራውን ሲሠራም ሊሆን ይችላል፡፡ የመጀመሪያው ጥፋት የሥራ ጥፋት ሲሆን የተጐዳው ሰው ካሣ ከመንግስት ላይ ለመጠየቅ ይችላል፡፡ ሠራተኛው ያደረገው ጥፋት የግል ጥፋቱ የሆነ እንደሆነ ግን መንግስት ሀላፊነት አይኖርበትም //2126 /2/ እና /3// ፡፡

 

አንድ ጥፋት የሥራ ጥፋት ለመባል ምን ማሟላት እንዳለበት ቁጥር 2127 ስር ተዘርዝሯል፡፡

እነሱም፣

  1. ሥራው በስልጣኑ ልክ መሆን አለበት
  2. ቅን ልቦና መኖር አለበት
  3. ለሥራ ክፍል ይለዋል እንግሊዝኛው ግን /In the interest of the state/ ይለዋል፡፡

 

ከዚህ ውጭ በሆነው በማናቸውም ሌላ ጉዳይ ጥፋት ቢፊፅም ጥፋቱ እንደግል ጥፋት ሆኖ ይቆጠራል፡፡

 

ከላይ ያልናቸው ነጥቦችና ሀሳቦች በሙሉ ለክልል መንግስታት ሠራተኞችና ለህዝብ አገልግሎት በተቋቋሙ በህግ የሰውነት መብት በተሰጣቸው ድርጅቶች ሠራተኞችም ላይ ተፈፃሚ ይሆናሉ /2128/፡፡

 

የሰውነት  መብት  የተሰጣቸው  ድርጅቶች  አላፊነት ቁጥር  /2129/

 

እነዚህ ድርጅቶች  በእንግሊዝኛው  /Bodies corporate / የሚባሉ ናቸው  ምን  እንደሆኑ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 4ዐ4 ጀምሮ እስከ 482  ተደንግጓል፡፡ ቁጥር 457  ስር ለሠራተኞቻቸው  እነዚህ  የሰውነት መብት የተሰጣቸው  ድርጅቶች  ከውል  ውጭ  በሚደርስ አላፊነት እንዴት በአላፊነት ሊጠየቁ እንደሚችሉ  ተደንግጓል፡፡ ቁጥር  2129  እነዚሁኑ ሠራተኞች የማህበሩ  እንደራሲዎች ፣ ወኪሎች ወይም ደሞወዝተኞች  በማለት  ዘርዝሮ ያስቀምጣቸዋል፡፡

ቁጥር 457  እንደ ቁጥር 2129 እነዚህ ሠራተኞች  የተሰጣቸውን ሥራ በሚያከናውኑበት ጊዜ አላፊነት  የሚያስክትል ሥራ  የፈፀሙ  እንደሆነ በፍትሐብሔር የሚጠየቁት እነዚህ ማህበሮች  መሆናቸውን ይደነግጋል፡፡

 

በተመሳሳይ  ቁጥር 213ዐ አንድ ሠራተኛ  ሥራውን የሚሰራበት ጊዜ አላፊነትን የሚያስከትል ጥፋት  የሰራ እንደሆነ በፍትሐብሔር  በአላፊነት የሚጠየቀው አሰሪው  ነው በማለት ደንግጓል፡፡ ሥራውን በሚሠራበት ጊዜ  የሚለውንም ሐረግ 2132 ስር ሕጉ የሕሊና ግምት ወስዷል፡፡ በዚህ ቁጥር መሠረት ሠራተኛው  በሚሰራበት ቦታና  ጊዜ የጥፋት ተግባር የፈፀመ እንደሆነ ጉዳቱን ሥራውን በማከናወን ላይ  ሳለ እንደሰራው ይቆጠራል፡፡