ግልግሉ፣ አስታራቂነቱ ወይም ሽምግልናው ውጤት እንዲኖረው፣ በተዋዋይ ወገኖች  አስቀድሞ ተቀባይነት ያገኘ በፅሁፍ የተደረገ ስምምነት ወይም ልማዳዊ አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች አስቀድመው ባልተስማሙበት አኳኋን የሚደረግ የግልግል፣ የዕርቅ ወይም የሽምግልና  አሰራር፣ በተዋዋይ ወገኖች ሙሉ ፈቃድ ካልሆነና በፅሁፍ፣ ጥያቄው ካልቀረበላቸው በቀር ይህንን ተግባር ለማከናወን የተመሠረቱ ተቋማት ጉዳዩን ሊያዩት አይችሉም፡፡ በመሆኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የግልግልም ሆነ የዕርቅ ወይም የሽምግልና አሠራር ከሚጠይቃቸው አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል በተዋዋይ ወገኖች የውል ስምምነት ውስጥ የተካተተ ወይም በልዩ የመገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት የተደረገ የጽሁፍ ስምምነት መኖር አንዱ እና ተቀዳሚው ጉዳይ እንደሆነ ተደርጐ በአለም አቀፍ የግልግል፣ የዕርቅና የሽምግልና ህግጋት ተደንግጐ ይገኛል፡፡

በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት መሠረት የሚሠጥ የግልግል ውሳኔበህግ በተገለጸ ክልከላ ካልሆነ በቀር፤ ምንጊዜም ቢሆን ተፈፃሚነት አለው፡፡ ስለሆነም፣ አለም ዐቀፍ የግልግል፣ የዕርቅና የሽምግልና አሠራር በአለም ዐቀፍ ንግድ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት መሠረት የሚቋቋም ወይም በስምምነቱ መሠረት የሚፈጠር፣ የንግድ አለመግባባቶች የሚፈቱበት ስርዓት ነዉ ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በአጠቃላይ አገላለፅ፣ የተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ውጤት ሆኖ ተዋዋዮቹ ያለ-መግባባት ቢኖር ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መውሰድ ሳያስፈልግ እነርሱ በመረጡት መንገድ በግልግል፣ በዕርቅ ወይም በሽምግልና ለመፍታት በውላቸው ምስረታ ወቅት አስቀድመው የሚያደርጉት ውል ሲሆን የፍርድ ቤትን አሰራር የሚያስቀር አማራጭ ስምምነት ነው፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በዚህ ስምምነታቸው ውስጥ በአደረጉት የተለየ ውል መሠረት ጉዳዩ እንደአስፈላጊነቱ በገላጋዮች በአስታራቂዎች ወይም በሸምጋዮች አማካኝነት እንዲያልቅ ከመወሰን በተጨማሪ ግልግሉ… በየትኛው ሕግ ወይም ደንብ መሠረት መታየት እንዳለበት አስቀድመው መወሰን ይችላሉ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ገላጋይ ተቋማትን ወይም ግለሰቦችን አስቀድሞ መምረጥና በዕነዚህ ተቋማት የሚሰጥ ውሳኔ የመጨረሻ እንዲሆን ሊስማሙ ይችላሉ፡፡

የዚህ ምዕራፍ ተቀዳሚ አላማም ዓለም አቀፍ የግልግል የዕርቅና፣ የሽምግልና አሰራርን በማመልከት ጉዳዩን የሚመለከቱ ሕጐችንና ደንቦችን በማስተዋወቅ የግልግል የዕርቅ ወይም የሽምግልና አለም አቀፋዊ  አህጐራዊ እና ብሄራዊ ሕግጋትን መሠረት በማድረግ የተቋቋሙ የግልግል ተቋማትን ለአብነት ያህል በመጥቀስ በሀገራችን የግልግል ስርአት የሚዘረጋበትን አሰራር በሚመለከት የተወሰነ የመግባቢያ ሀሳብ ለመፈንጠቅ ነው በጥናቱ የተካተቱት ተቃማትና ህግጋት፤ ከአላቸው ዓለም አቀፋዊ አህጉራዊና ብሄራዊ ተቀባይነት ወይም ተፈፃሚነት አንፃር ለጥናቱ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል የተባሉት ዕንጂ በጉዳዩ አግባብነት ያላቸው ማዕከላትንና ሕግጋትን በአጠቃላይ ለመዳሰስ የፅሁፍ አላማ አይደለም፡፡ ስለሆነም ከዓለም አቀፍ፤ ከአህጉራዊና ከብሄራዊ የግልግል ተቋማትና ህግጋት መካከል አብነት ሆነው ያገለገሉትን እና በማገልገል ላይ ያሉትን ብቻ በመምረጥ ስለጉዳዮ ጠቅላላ ዕይታ እንዲኖር በማሰብ ቀጥሎ በሚቀርቡ ንዑሳን ክፍሎች ለማካተት  ተሞክሮአል፡፡

አጠቃላይ  

የአማራጭ አለመግባባት መፍቻ ሰርአት ጽንሠ ሃሳብ አለመግባባቶችን በፍርድ ቤቶች አማካኝነት ከመፍታት ይልቅ እንደ ድርድር፣ እርቅ፣ ሽምግልና ወይም ግልግል እና የመሳሰሉት ሌሎች መሰል ማህበረሰባዊ እሴቶችን በመጠቀም በግለሰቦች ፣ በመንግስታት ወይም በድርጅቶች መካከል የሚያጋጥሙ ቅራኔዎችን መፍታት ይቻላል በሚል መርህ ላይ የተመሰረተ ነዉ፡፡ በመሆኑም፣በዚህ አጭር ጽሁፍ ላይ ትኩረት የሚሰጣቸው ቃላት እና ሀረጎች ማለትም ‹ድርድር›፣ ‹ዕርቅ›፣ ‹ሽምግልና›፣ ‹ግልግል› ጥቅም ላይ እንዲዉሉ የተደረጉ ሲሆን አንባቢዉ አንዱ ከሌላዉ ቃል ያለዉን ልዩነት መረዳት ይችል ዘንድ ለቃላቱ የተሰጠዉን ፍቺ ከዚህ ቀጥሎ ለማቅረብ ይሞከራል፡፡

“ድርድር” /Negotiation/

የ“ድርድር” /Negotiation/ ዋነኛ ዓላማ አለመግባባቶችን በንግግር ወይም በውይይት መፍታት ላይ ያለመ የማግባቢያ ዘዴ መሆኑ ነው፡፡ ድርድሩ ለግል ወይም ለጋራ ጥቅም ወይም የተለያዩ ፍላጐቶችን ለማርካት ታቅዶ ተደራዳሪዎች ራሳቸው በሚገኙበት ወይም በወኪሎቻቸው በሚወከሉበት የድርድር መድረክ ይከናወናል፡፡

“ድርድር” በንግድ ወይም ለትርፍ ባልተቋቋሙ ድርጅቶች እንዲሁም በመንግስት መ/ቤቶች መካከል ከሚያጋጥሙ አለመግባባቶች አንስቶ የግል አለመግባባትን  በሰላም በመፍታት ጭምር ጥቅም ላይ ሲውል የቆየ የአማራጭ ቅራኔ አፈታት ስርዓት ሲሆን በተደራዳሪዎች ላይ የሚያስከትለው አስገዳጅ ተፈፃሚነት  የለውም፡፡  

የድርድር ተቀዳሚ  አላማ ተቃራኒ ሃሣቦችን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በማቅረብ ማወያየት ወይም ማነጋገር ሲሆን ተደራዳሪ ወገኖች እንደአስፈላጊነቱ የሚጋብዙት  አደራዳሪ ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ተጋባዡ አደራዳሪ ምንም አይነት አስገዳጅ ሀሣብ መስጠት አይችልም፡፡ ተደራዳሪዎቹ ራሳቸው ባመነጩት መደራደሪያ ሃሣብ መሠረት ድርድሩ ይከናወናል፡፡ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥረት በማድረግ፣ድርድሩ ከተሳካ የመግባቢያ ሠነድ ተዘጋጅቶ እንዲፈርሙበት ይደረጋል፡፡ ሰነዱ ተደራዳሪዎቹ በሚስማሙበት ቦታ ይቀመጣል፣ የሃሣብ መግለጫ  እንደሆነ ተደርጐም ይቆጠራል፡፡ አንዳንድ ግዜም እንደ ተዋዋዮቹ ፈቃድ የድርድር ስምምነት ውጤት ሆኖ ይፀድቃል፡፡ ድርድሩ ባልተሳካ ጊዜ ግን ተደራዳሪዎቹ  በመረጡት ሌላ የማግባቢያ ስርዓት አለመግባባት የተፈጠረበት ጉዳይ እንዲታይ ይደረጋል፡:በልማድ እንደሚያጋጥመው ነገሮችን በድርድር መፍታት ካልተቻለ በሽምግልና ወይም በዕርቅ ለመፍታት ሙከራ ይደረጋል፡፡

“ሽምግልና” /Mediation/

በሕግ አነጋገር አማራጭ የቅራኔ መፍቻ ስርዓት ነው ተብሎ የሚታወቅ በሁለት ወይም ከዚያ በላይ በሆኑ ወገኖች የሚያጋጥሙ አለመግባባቶች የሚፈቱበት ስርዓት ነው፡፡ ከድርድር የሚለይበት አንዱና ዋነኛው ነጥብ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ ተሣትፎ የሚኖረው  ሶስተኛ ወገን /ሸምጋይ/ በመኖሩና ተቋማዊ በመሆኑ ነው፡፡ የሶስተኛው ወገን ሚና  ለግልግል ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ያተኮረ ሲሆን እንደ አስፈላጊነቱ ግን ተደራዳሪዎቹ ራሣቸው ባመኑበት መደራደሪያ ሃሣብ ተቀራርበው እንዲነጋገሩ የተቻለውን ያህል ጥረት ያደርጋል&፡ ፍትሀዊ የማግባቢያ ሃሣብ ያቀርባል፤ ውይይቱን በመምራት እና በመሸምገል ድርድሩ አቅጣጫ እንዲይዝ ያደርጋል፡፡“ሽምግልና”፣በድርድር ሂደት የማይስተዋሉ እንደ አደረጃጀት /Structure/፤የጊዜ ሰሌዳ ተለዋዋጭነት /Filexibility/ ባህሪያት እንዲሁም የሚመራባቸዉ ደንቦች አሉት ፡፡ ስለሆነም ተሸማጋዮቹ በሽምጋዩ አደረጃጀት በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ እና በተወሰነ የአሰራር ደንብ መሠረት አለመግባባቶቻቸውን እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡  “ሽምግልና” እንደ መርህ የአስገዳጅነት ውጤት ባይኖረውም፣ አንዳንድ ጊዜ ግን ባለጉዳዮች አለመግባባቶቻቸውን በሽምግልና ለመጨረስ ያደረጉት ውል ካለ በውሉ መሠረት በሽምጋዮች የሚቀርበው የማግባቢያ  ሃሳብ ውሳኔ  ሆኖ  የሚወሰድበት  አጋጣሚ አለ፡፡ ሽምግልና  ውጤት  ካላስገኘ  በቀጣይነት  አለመግባባትን   ለመፍታት ጥቅም ላይ የሚውለው ዘዴ ዕርቅ ይሆናል፡፡

“ዕርቅ”፣ /Concilation/፡-  

ተዋዋይ ወገኖች በወቅቱ ወይም ገና ለወደፊቱ በሚያፈሯቸው ጥቅሞች ላይ አለመግባባት ቢያጋጥም አለመግባባቱን በሶስተኛ ወገን ሙያዊ ወይም የቴክኒክ  ዕገዛ ለመፍታት በሚያደርጉት  ስምምነት መሠረት የሚከናወን ሌላው አማራጭ የቅራኔ አፈታት ስልት ነው፡፡ አስታራቂው፣ አለመግባባቱን ለመፍታት ባለጉዳዮችን በተናጠል በማነጋገር የማስታረቂያ ሰነድ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ከሽምግልና ፣”ዕርቅ”  የሚለይበት አንዱ መሠረታዊ ነጥብ አስታራቂው ሁለቱንም ባለጉዳዮች ግንባር ለግንባር እንዲያገናኝ የማይጠበቅበት መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱን ተዋዋይ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በተናጠል ማነጋገር እና  የደረሰበትን ለባለጉዳዮቹ መግለፅ  እንዲሁም በሚያገኘው ግብዓት አለመግባባቱን መፍታት  የሚያስችል የዕርቅ ሃሣብ (proposal) በፅሁፍ አዘጋጅቶ በማቅረብ ላይ የተመሠረተ ግዴታ አለበት፡፡አስታራቂው በሚያቀርበው ሰነድ ላይ ባለጉዳዮቹ ከተስማሙ በሰነዱ ላይ እንዲፈራረሙበት ይደረጋል፡፡ ስለሆነም በሰነዱ ላይ የሰፈሩትን ግዴታዎች  እንዲፈፅሙ ይገደዳሉ፡፡ በዚህ ረገድ፣ በተለይም የዕርቅ ተግባር በውጤት ሲታይ አስገዳጅ ተፈፃሚነትን  ስለሚያስከትል  አስቀድመን ከተመለከትናቸው ከድርድር እና ከሽምግልና የተሻለ ዉጤታማ ነዉ፡፡ በአንፃሩም ደግሞ በግልግል ዳኝነት እንደሚታየው  የፍ/ቤቶችን አሰራር ስለማይከተል እና የዕርቅ ሰነዱ በተዋዋዮች ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት የሚደረግለት ህጋዊ ጥበቃ  ስለማይኖር፣ “ዕርቅ”  ከግልግል  ያነሰ ተቀባይነት አለው ተብሎ ይገመታል፡፡  

“ግልግል”/Arbitration/፡-

ተዋዋይ ወገኖች አለመግባባቶቻቸውን በግልግል ዳኝነት በሚሰጥ ውሳኔ ለመፍታት ተስማምተው ጉዳዮቻቸውን ከፍ/ቤት አሠራር ውጭ እንዲታይላቸው ለግልግል አካላት የሚያቀርቡበት ስልት ነው፡፡ አስቀድመን ካየናቸው የቅራኔ አፈታት ዘዴዎች የላቀ ተቀባይነት ያለው፣ በግልግል የሚሰጥ ዳኝነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ “ግልግል”፣ ተመራጭ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች መካከል በባለጉዳዮች ዘንድ ተፈፃሚነት ሊኖረው የሚችል ውሳኔ መስጠት የሚያስችል ስርዓት ከመሆኑም በተጨማሪ በአሠራሩ ከፍ/ቤቶች ሥራ አካሄድ ጋር ተመሳሳይነት ያለዉ የህግ ስርአት  በመሆኑ ነዉ፡፡

በግልግል ዳኝነት ስራ አካሄድ፡ በተዋዋይ ወገኖች በሚደረግ ስምምነት መሰረት የሚመረጡ        ገላጋይ ዳኞች የሚሰየሙበት የግልግል ችሎት መኖር፤ የአመልካች እና ተጠሪ እንደአስፈላጊነቱ መቅረብ፤ እንደገላጋይ ዳኞቹ ፍላጐት ማስረጃዎችን መመርመር፤ ምስክሮችን መስማት፤ ሙያዊ ማብራሪያ መቀበል እንዲሁም ጊዜያዊ የዕግድ ትዕዛዞችን ወይም ብይኖችን መስጠት፤ ወይም በፍ/ቤቶች በኩል ማሰጠት እና በመጨረሻም አለመግባባቱ የተመሰረተበትን ጉዳይ መርምሮ የግልግል ዳኝነት ዉሳኔ በተወሰነ የግዜ ገደብ ዉስጥ መስጠት የተለመዱ ተግባራት ናቸው፡፡

በዚህ ክፍል የተመለከቱት ቃላት ፍቺ፣ ከጽሁፉ ይዘት አኳያ የተሰጠ እንጂ የቃላቱን ጽንሰ ሐሣብ ሙሉ በሙሉ የሚያብራራ ባለመሆኑ ጉዳዩን የሚመለከቱ ሌሎች ጽሁፎችን መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡   

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ቀጥሎ በሚቀርበዉ ጽሁፍ ቃላቱን እንደአስፈላጊነቱ በተለዋዋጭነት ጥቅም ላይ ለማዋል ተሞክሮአል፡፡ በተለይም፣ አለመግባባቶችን ከመደበኛ ፍርድ ቤት አሰራር ዉጭ ለመፍታት በአመዛኙ ጥቅም ላይ ዉሎ የሚገኘዉ አለምአቀፋዊ አሰራር ‹ግልግል› (Arbitration) በመሆኑ የጽሁፉ ትኩረት ግልግል በሚለው ጽንሰ ሃሳብ ላይ እንዲመሰረት ሆኗል፡፡ ስለሆነም፣በዚህ አጭር ፅሁፍ ዉስጥ ‹ግልግል› በሚል አገላለጽ የተሰጠ ማብራሪያ እንደ አስፈላጊነቱ፣በዕርቅና በሽምግልና ተግባራት ላይም ተፈፃሚነት ሊኖረዉ እንደሚችል ማስታወሱ ተገቢ ይሆናል፡፡

ስለ ዓለም አቀፍ ግልግል፣ ዕርቅና ሽምግልና አፈፃፀም

የዓለም አቀፍ የግልግል የዕርቅ ወይም የሽምግልና አሠራር ዋና መገለጫ ነዉ ተብሎ የሚነገረዉ መሰረታዊ ጉዳይ፣ ክንውኑ የሚመራው በተዋዋይ ወገኖች አስቀድሞ በጽሁፍ  በተደረገ ወይም አለመግባባቱ ከተከሰተ በኃላ ጉዳዩን በግልግል፤ በእርቅ ወይም በሽምግልና ለመፍታት በሚደረግ  የውል ስምምነት ላይ የተመሰረተ  ከመሆኑ አንጻር የሚነገረዉ  አብይ ቁም ነገር ነዉ፡፡ የተዋዋይ ወገኖች የተሟላና በነጻነት የሚሰጥ ፈቃደኝነት ወይም ስምምነት ለግልግል፣ ለእርቅ ፣ወይም ለሽምግልና ሥራ አፈጻጸም እንደ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የገላጋይ፤ አስታራቂ ወይም አሸማጋይ ተቋማት ማንነትም ሆነ የገላጋዮችን ቁጥር አስቀድሞ በውል መወሰን ተገቢ ይሆናል፡፡ ገላጋዮችን በመምረጥ ረገድ እንደተዋዋይ ወገኖች ፍላጐት ከሁለት የታወቁ ዓለም አቀፋዊ  አሠራሮች  አንዱን መምረጥ ይቻላል፡፡ ይኼውም፡- 1ኛው አሠራር ለዚሁ አላማ በተቋቋሙ ዓለም አቀፋዊ የግልግል ተቋማት አማካኝነት የግልግል ተግባሩ እንዲከናወን አለመግባባት የተፈጠረበትን ጉዳይ ለተቋማቱ ማቅረብ ሲሆን፣ ሌላዉ  አማራጭ ደግሞ ተዋዋዮቹ በሚያደርጉት የጋራ ስምምነት ለጊዜው ለዚሁ ተግባር ሲባል በሚያቋቁሟቸው ጊዜያዊ ገላጋዮች አማካኝነት አለመግባባቱ እንዳስፈላጊነቱ  በግልግል ፣ በእርቅ ወይም በሸምግልና እንዲያልቅ የሚደረግ  አሰራር  ነዉ፡፡

የግልግል፣ የዕርቅ ወይም የሽምግልና ስርዓት ተመራጭነት እንዲኖረው ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ጉዳይም ተዋዋይ ወገኖች በመረጡት ገላጋይ አስታራቂ ወይም ሽማግሌ የሚታዩበት  የተጠቀሰው አይነት አሰራር መከተሉን ነው፡፡ ይህ አይነቱ አሰራር  ደግሞ ተዋዋይ ወገኖች ራሳቸው ፈቅደው ባላቋቋሟቸውና በማያውቋቸው መደበኛ ፍ/ቤቶች በሚሰጥ ውሳኔ እንዳይገደዱ ስለሚያደርግ  ተመራጭነቱ የጐላ ይሆናል ፡፡ በዚህ ረገድ ተዋዋይ ወገኖች ተቋማቱን መምረጥ ብቻ ሳይሆን ገላጋይ ዳኞችን፤አሰታራቂዎችን ወይም ሸምጋዮችን የመሰየም፣ ዳኞቹ፣ አሰታራቂዎቹ ወይም ሸምጋዮቹ የሚሰሩባቸዉ ተቋማት፣ ሊጠቀሙባቸዉ የሚገቧቸውንም ህጐች የመምረጥ ዕድል ስለሚሰጣቸው በመደበኛ ፍ/ቤቶች በሚሰራበት ብሄራዊ ህግ መሰረት እንዲዳኙ አይገደዱም ፡፡

እነዚህ ጉዳዮች በአንድ ላይ ተጣምረው በገላጋዮች የሚሰጡ ውሳኔዎች በተዋዋይ  ወገኖች ዘንድ የታመኑ  እንዲሆኑና ተቀባይነት እንዲኖራቸው ይረዳሉ፡፡

በዘመናችን በመካሄድ ላይ ባለው ዘርፈ- ብዙ የንግድ እንቅስቃሴ በተለይ፤ የግልግል፤ የእርቅ ወይም የሽምግልና አሠራር ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል፡፡ ንግድ በባህሪው የተለያዩ ወገኖችን ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደመሆኑና የተለያዩ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ወይም የንግድ ኩባንያዎች የሚገናኙበት ኢኮኖሚያዊ  እንቅስቃሴ በመሆኑ፣ በንግድ ሂደት የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን የሚዳኝ ወይም የሚሸመግል ገለልተኛ አካል እንዲኖርና በሚሰጥ የግልግል ወይም የሸምግልና ውሳኔ ለመገዛት ቅድመ ስምምነት ማድረግ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ይህንን አለምአቀፋዊ ፍላጎት ለማሳካት እንዲሁም የንግዱን ህብረተሰብ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከዘመናዊዉ ነባራዊ የንግድ እንቅስቃሴ አንጻር ለመምራት እንዲቻል፣ እንደ አሸን እየተበራከቱ የመጡ ዓለም አቀፋዊ  የንግድ ግንኙነቶች ከመኖራቸው ጐን ለጐን ቁጥራቸው የበዛ ዓለም አቀፋዊ፣አህጉራዊ እና ብሄራዊ የግልግል እና የሽምግልና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ወይም አካላት ተመስርተው ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

የግልግል፣ የዕርቅ ወይም የሽምግልና ሥርዓት በዓለም አቀፋዊ እና በብሄራዊ ኢኮኖሚያዊ የስራ መስክ እንዲሁም የንግድ ግንኙነት  ተመራጭ የሚሆንባቸው ምክንያቶች  አያሌ  ቢሆኑም  ግንባር ቀደም ከሆኑት መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-

አለም አቀፋዊም ሆነ ብሄራዊ  የንግድ ግንኙነት በአቅርቦት እና ፍላጎት (supply and demand) ላይ የተመሰረተ ከመሆኑ በቀር የተጠቃሚዎችን ማንነት ወይም ማህበራዊ አቋም ግምት ዉስጥ ያስገባ አይደለም፡፡አንዱ ወገን ምርቱን ወይም አገልግሎቱን በፍላጎት ለሚቀበለዉ  አሽቀድሞ ለሚያዉቀዉ ወይም ለማያዉቀዉ ሁለተኛ ወገን ያቀርባል፤ እንዲሁም ሌላዉ ወገን በፍላጎቱ መጠን የቀረበለትን ምርት ወይም አገልግሎት ይረከባል፡፡ ስለሆነም ግንኙነቱ የተለያየ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ኩባንያዎች የሚሳተፉበት  ከመሆኑ አኳያ ይህንን የሚገዛ ወይም የሚመራ አንድ ወጥ መንግስታዊ አካል ወይም አስተዳደር አይኖርም፡፡ በመሆኑም፣ ተዋዋይ የንግዱ ህብረተሰብ አባላት በዜግነት ሳይወሰኑ አለመግባባቶቻቸውን ሊፈቱበት የሚችሉ ገለልተኛ ፍርድ ቤት በሌለበት ሁኔታ በተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ የሚመሠረት ገለልተኛ አካል መኖር አስፈላጊ ይሆናል፡፡   ይህንን ፍላጐት ሊያሟላ የሚችል  አካል ደግሞ በተዋዋይ ወገኖች ፈቃድ እና የጋራ ቁጥጥር የሚመሠረት የግልግል፣የእርቅ ወይም የሽምግልና  አካል በመሆኑ  ስርዓቱን ተመራጭ ያደርገዋል፡፡

በንግድ ግንኙነት ተሳትፎ የሚኖራቸዉ ተዋዋይ ወገኖች የተለያየ አገር ዜጐች  ሊሆኑ ስለሚችሉ፣ ለየትኛውም አገር ፍ/ቤት ውሳኔ ተገዥ እንዲሆኑ አይገደዱም፡፡ ስለሆነም በዜግነት ጉዳይ ገደብ በማይኖረው ገለልተኛ የግልግል ስርአት ከመደበኛ ፍ/ቤት ስርአት ውጪ የንግድ አለመግባባታቸውን ስለሚፈታላቸው የግልግል ሥርዓት ተመራጭ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በሌሎች አገሮች የሚሰጥ የፍርድ ውሳኔ በየትኛውም አገር ተፈፃሚነት እንዲኖረው የሚያስገድድ አለም ዓቀፍ ስምምነት ወይም ሕግ የለም፡፡ በአንፃሩ ግን በየትኛውም አገር የሚሰጥ የግልግል ዳኝነት በውጭ አባል አገራት ዕውቅና እንዲያገኝ እና እንዲፈፀም የሚያስገድድ እ.ኤ.አ በ1958 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣ የኒዉዮርክ ስምምነት ስላለ፣ በስምምነቱ መሠረት በግልግል የተሠጠን ዳኝነት የዜግነት ገደብ ሳይኖርበት ስምምነቱን ባፀደቁ የውጭ ሀገራት ማስፈፀም ይቻላል፡፡

ስለሆነም፣ በግዛት ወሰን እንዲሁም በዜግነት ሊሰጥ እና ሊፈፀም ከሚገባ የመደበኛ ፍ/ቤት ውሳኔ ይልቅ የግዛትም ሆነ የዜግነት ገደብ የማይደረግበት የግልግል ሥራ ተመራጭነት ይኖረዋል ፡፡

ተዋዋይ ወገኖች በሌላው ተዋዋይ ወገን ብሄራዊ ፍ/ቤት በሚሰጥ ውሳኔ ላይ ሙሉ እምነት የላቸውም፡፡ በፍ/ቤቶቹ ነፃ ዳኝነት ላይ ይጠራጠራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መደበኛ ፍ/ቤቶች ጉዳዮችን የሚያዩት በብሄራዊ ሕግ አውጪ አካላት በወጡ ሕጐች መሠረት   ስለሚሆን፣ የተዋዋይ ወገኖችን ፍላጐት ወይም የሕግ ምርጫ ተግባራዊ ለማድረግ ይሳናቸዋል፡፡ በአንጻሩ ግን የግልግል ተቋማት የየትኛውም አገር የግዛት ወሰን የማይገድባቸው ከመሆናቸውም ሌላ ፈቃድ ያገኙበትና ተመዝግበዉ የሚሰሩበት አገር ቢኖርም፣ በግለሰብ ደረጃ ሲታይ የዉጭ ሀገር ዜጎች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ለዜጐቻቸው ያዳላሉ ወይም በመንግስት ተፅእኖ ይደረግባቸዋል የሚልን ግምት በማስቀረት በተዋዋይ ወገኖች ምርጫ በተለያዩ ህጐች መሠረት ጉዳዮችን የማየት አሠራርን ስለሚከተሉ ሕጐችን በመምረጥ ረገድ ተዋዋይ ወገኖች የሚሳተፉበት ዕድል  ይኖራል፡፡

ስለሆነም የግልግል ስርዓት፡ ከአድልዎ የፀዳ፣ እምነት የሚጣልበት፣ በተዋዋዮች ፈቃድ መሠረት የሚመራ፣በተዋዋይ ወገኖች ፍላጎት ወይም ፈቃድ የተመረጡ  ገለልተኛና ነፃ ገላጋይ ዳኞች ፣አስታራቂዎች ወይም ሸምጋዮች በሚሰየሙበት አካል ጉዳዩ የሚታይ በመሆኑና  በተለያዩ ሕጐች መሠረት ውሳኔ  ወይም ዳኝነት የሚሰጥበት በመሆኑ ዓለም አቀፉዊና ብሄራዊ የንግድ እንቅስቃሴን ለማጐልበት እና የንግዱን ህብረተሰብ ፍላጐት ለማርካት ተመራጭነት አለው ተብሎ በብዙዎች  ዘንድ  ተቀባይነት እያገኘ በመምጣት ላይ ይገኛል፡ በመሆኑም ይህንን አለማቀፋዊ የግልግል ስርዓት  የሚመሩና የሚተገብሩ ልዩ ልዩ  ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች፣ ቃል ኪዳኖችና  ውሎች እንዲሁም ብሄራዊ የግልግል፣ የእርቅ/የሽምግልና ህግጋት እና ደንቦች መኖራቸዉ ይታወቃል፡፡     

የግልግል ወይም የሽምግልና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ቁጥር እንደመደበኛ ፍ/ቤቶች የተወሰነ አይደለም፡፡ አገልግሎቱን በሚፈልጉ ወገኖች ስምምነት  በጊዜያዊነት እንደ አስፈላጊነቱ  ሊቋቋሙ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ከመደበኛ ፍ/ቤቶች ይልቅ  የግልግል አካላት ተደራሽነት የተሻለ ሆኖ ይገኛል፡፡

በመደበኛ ፍ/ቤቶች የሚታዮ ጉዳዮች ከተጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ውሳኔ  እስኪሰጥባቸው  ያለው የጊዜ ምጣኔ  ገደብ የለውም፡፡ በፍ/ቤቶች የፍርድ አካሄድ  የሚወሰን ነው፡፡ ነገር ግን በግልግል  የሚታዮ ጉዳዮች በምን ያህል ጊዜ ማለቅ እንደሚገባቸው  ተዋዋይ ወገኖች መወሰን ስለሚችሉ የግልግል ወይም የሽምግልና  አሠራር ጊዜ  ቆጣቢ ነው፡፡

በመደበኛ ፍ/ቤቶች ስለሚመደቡ ዳኞች ቁጥር እና  ብቃት ተገልጋዮች የሚወስኑበት ዕድል የላቸውም ፡፡ ይሁን እንጂ በግልግል ወይም በሽምግልና ጉዳዮችን ስለሚያዩ  ዳኞች የሙያ ብቃትንና ቁጥርን የመወሰን መብት የተዋዋይ ወገኖች በመሆኑ በግልግል የሚሰጥ ውሳኔ በዳኞች የአቅም ማነስ ወይም አናሳ ቁጥር ለሚመጣ የውሳኔ ጥራት ማነስ ተገልጋዮች አይጋለጡም፡፡

ከቦታ አኳያ ሲታይ መደበኛ ፍ/ቤቶች ቋሚ የማስቻያ ቦታ ስላላቸው በተለየ አሰራር ካልሆነ በቀር ከቦታ፣ ቦታ ተዛውረው እንዲያስችሉ በተገልጋዮች አይገደዱም፡፡ በግልግል ወይም በሽምግልና በሚቀርቡላቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዲሰጡ ጥያቄው የቀረበላቸው ተቋማት ወይም ግለሰቦች ግን የግልግል ወይም የሽምግልና አገልግሎት የሚሰጡበት ቦታ ተዋዋይ ወገኖች በሚያደርጉት የቅድመ ውል ሊወሰን ይችላል፡፡ በመሆኑም አገልግሎቱ በየትኛውም ቦታ እንደተዋዋይ ወገኖች ፍላጐት ሊሰጥ ስለሚችል አገልግሎት አሰጣጡ ተመራጭ ይሆናል፡፡

መደበኛ ፍ/ቤቶች የሚያስችሉበት ቋንቋ፣የትርጉም አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ ከመኖሩና ይህም አስቀድሞ በህግ የተወሰነ ከመሆኑ በስተቀር የተዋዋይ  ወገኖችን ፍላጎት  የሚያስተናግድ አይደለም፡፡በአንፃሩ ግን በግልግል ወይም በሽምግልና አገልግሎት  ስራ ላይ የሚውለው ቋንቋ በተዋዋይ  ወገኖች ምርጫ ሊወሰን የሚችል እንጂ በአስገዳጅነት ጥቅም ላይ የሚውል አይሆንም፡፡ በዚህም ረገድ ቢሆን፣ የግልግል ሥርዓት ተመራጭ የሚሆንበት አጋጣሚ አለ፡፡  

በመደበኛ ፍ/ቤቶች የሚሰጥ ውሳኔ የተራዘመ ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል ወጪ ቆጣቢ ነዉ ለማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በግልግል ወይም በሽምግልና አንድ ጉዳይ ታይቶ ውሣኔ  ለመስጠት የሚወስደው ጊዜ አስቀድሞ በአግልግሎት ሰጪ ተቋማት የግልግል ደንብ ወይም በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት የሚወሰን  አጭር ጊዜ ስለሚሆን  ወጪ ቆጣቢ ነው፤የባለጉዳዮችንም  መመላለሰ ያስቀራል፡፡

በእነዚህና በሌሎች መሰል ምክንያቶች፣ በተለይ ድንበር ዘለል በሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተሳትፎ ያላቸዉ ባለጉዳዮች ፣ጉዳያቸው በመደበኛ ፍ/ቤቶች ከሚታይላቸው ይልቅ በግልግል፣አስታራቂ ወይም በአሸማጋይ ተቋማት ታይቶ እንዲወሰንላቸው ይመርጣሉ፡፡ ስለሆነም በብዙ የዓለም ሀገሮች፣ ብሄራዊና ዓለም አቀፋዊ የግልግል ወይም ሽምግልና ተቋማት ተቋቁመው የሚገኙ ሲሆን ሁሉም ሀገሮች ሊባል በሚችል መጠን፣ ይነስም ይብዛ የግልግል፣የእርቅ እና የሽምግልና ህጐች አሏቸው፡፡ እንዲሁም፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የግልግል የዕርቅ ወይም የሽምግልና ሥርዓቶች የሚመሩባቸው መሠረታዊ ዓለምአቀፋዊ የግልግልና የእርቅ ማሣያ ህጐች  አሉ፡፡ በዋናነትም፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም አቀፍ የንግድ ህግ ኮሚሽን (UNCITRAL) አለም አቀፍ የንግድ ግልግልና እርቅ ሞዴል ህጎች ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡

የግልግል (ARBITRATION) መገለጫ ባህሪያት

የገበያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ በተለያዩ  ማህበራዊ ግንኙነቶች በተለይም ከንግድ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ሊያጋጥም የሚችል  አለመግባባትን በአጭር ጊዜ ውስጥ በአነስተኛ ወጪ እና ውጤታማ በሆነ አሰራር ለመፍታት  የሚያስችል የግልግል ስርዓት መዘርጋት ወይም ማደራጀት የማይታለፍ ወቅታዊ ግዴታ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ አለመግባባቶች በግልግል በሚፈቱበት  አጋጣሚ፣  በንግድም ሆነ በሌላ ጉዳይ ግንኙነት ያላቸው የስራ ተጓዳኞች /Partners/  በመካከላቸው የነበረው የተረጋጋ  ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወይም ግንኙነት በነበረበት የሚቀጥልበት  ዕድል እንደሚኖር በተግባር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ  አንፃር ተጠቃሽ የሚሆነው ምክንያት፣ ግልግሉ የሚካሄደው በግል እና መደበኛ ባልሆነ የቅራኔ አፈታት ዘዴ በመሆኑ ነው፡፡

“ግልግል”፣ በተለይ እያንዳንዱ  የንግድ  ተጓዳኝ የሸሪኩን ሀገር ሕግ  ሊያውቅ በማይችልበት ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ ጠቀሜታው የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም የግልግል ዳኝነት የሚከናወነው፣ በተዋዋይ ወገኖች ምርጫ በሚወሰን ሕግ ዕንጂ ሀገሮች ዜጐቻቸውን በሚያስተዳድሩባቸው ሕጐች መሠረት አይደለምና ነዉ፡፡ የግልግል ዳኝነት፣ ከዚህም በተጨማሪ፣ ባለጉዳዩች በአንድ ሀገር ፍ/ቤቶች ገለልተኝነት  እና ነፃነት ላይ ሊኖራቸው የሚችልን  ጥርጣሬ ለማስወገድ ጉዳዩ ባለጉዳዩቹ ራሳቸው በመረጧቸው ገለልተኛ ገላጋይ ዳኞች ስለሚታይ፣ ግልግል ተመራጭነት አለው፡፡ የግልግል ዳኝነት ከሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች አንዳንዶቹን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡

የግልግል ዳኝነት ከተወሰኑ ህጋዊ ሁኔታዎች በቀር ውሳኔው እንደተሰጠ ይግባኝ ሳይባልበት ስለሚፈፀም እና የመጨረሻ በመሆኑ፤

የግልግል ዳኝነት በግል ፍላጐት በሚወሰን፣ለህዝብ ግልጽ ባልሆነ ችሎት ስለሚከናወን የግለሰቦች ሚስጥራዊነት እንዲጠበቅ ሁኔታው የተመቻቸ በመሆኑ፤

ባለጉዳዮች አለመግባባቱ ስለተከሰተበት ጉዳይ የጠለቀ ዕውቀት ያላቸውን  ባለሙያዎች በገላጋይነት የሚሰይሙበትን ዕድል ስለሚፈጥር፤

አስፈላጊነት የሌላቸው እና የባለጉዳዮችን የግል ህይወት የሚነኩ ማጣራቶች እንዲደረጉ የማያስገድድ  እና  ያላስፈላጊ  ወጪ  በአጭር  ጊዜ የሚከናወን በመሆኑ፤ እንዲሁም የባለጉዳዮችን የንግድ ግንኙነትና የስራ ሚስጥር ተጠብቆ እንዲቆይ ስለሚያስችል፣…

ግልግል ከማንኛውም  የፍ/ቤቶች አሰራር የሚመረጥበት  አጋጣሚ አለ፡፡

ከላይ ከተመለከቱት መሠረታዊ ምክንያቶች አንፃር የግልግል ዳኝነት ሥራ አካሄድ ጠቀሜታው የጐላ ቢሆንም፣ ለግልግል የሚቀርቡ እና የማይቀርቡ ጉዳዮች ስለ መኖራቸው፣ በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ወይም በህግ የሚገለጽበት አሰራር መኖሩን ያስታውሷል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ ዓለም አቀፍ የንግድ ግንኙነትን በሚመለከት የሚያጋጥሙ አለመግባባቶች በአመዛኙ በግልግል ታይተው እንዲወሰኑ  ይደረጋል፡፡

በግልግል ሂደት ሊወሳ የሚገባው ሌላው ቁም ነገር የግልግል ስምምነት ውል መኖር አስገዳጅነት ነው፡፡ በባለጉዳዮች ነፃ ፈቃድ የተደረገ የግልግል  ስምምነት ውል በሌለበት ሁኔታ  ስለ  ግልግል ዳኝነት ማሰብ አይቻልም፡፡ ለግልግል ዳኝነት መሠረቱ የግልግል ስምምነት ውል መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የግልግል ስምምነት ውል በሁለት  መንገዶች ሊደረግ ይችላል፡፡ 1ኛው መንገድ፣ ዋናው ውል በሚደረግበት ጊዜ  በውሉ ውስጥ በአንድ በተለየ  አንቀጽ ወይም በተለየ ሰነድ ስምምነቱ ሊሰፍር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አለመግባባቱ በተከሰተበት አጋጣሚ የግልግል ስምምነቱ ውል መዋዋል የሚቻልበት ሁኔታ እንዳለም ይታወቃል፡፡  ስምምነቱ በየትኛውም ደረጃ ቢደረግ  ከዋናው ውል ተነጥሎ ይታያል እንጂ ዋናው ውል ቢፈርስም እንኳን የግልግል ስምምነቱ ውል አይፈርስም፡፡ በግልግል ስምምነቱ በሚወሰነው መሠረት ጉዳዩን ለግልግል ዳኝነት ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እንደ ውሉ፣ ለጊዜው በሚቋቋም የግልግል ዳኝነት አካል /ADHOC/ ወይም በግልግል  ተቋም ዳኝነቱ እንዲታይ ይደረጋል፡፡

ነገር ግን የአንዳንድ ሀገሮች የግልግል ህጉች ለግዜው ለሚቋቋም የግልግል  አካል የግልግል ዳኝነት ጥያቄ ለማቅረብ  የተደረገን ስምምነት ህጋዊነት አይቀበሉም፡፡ እንደማሳያም የቻይናን የግልግል ሕግ እዚህ ላይ ማስታወሱ ይበጅ ይሆናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለጊዜው በሚቋቋም የግልግል ዳኝነት አካል እና ተቋማዊ  በሆነው የግልግል ስርዓት መካከል የጎላ ልዩነት አለ፡፡ተቋማዊ የሆነዉ የግልግል አካል  የዳበረ አስተዳደራዊ መዋቅር እና የዳበረ የግልግል ደንብ ሲኖረው፣ በአንፃሩ ግን በጊዜያዊነት የሚቋቋመው የግልግል አካል  አገልግሎቱን  ሊሰጥ የሚችልበት መዋቅርም ሆነ የግልግል ደንብ አይኖረውም፡፡ እንዲሁም ጊዜያዊው የግልግል አካል ሙሉ በሙሉ በባለጉዳዮች በሚወሰን  የጊዜ ሰሌዳ እና  በባለጉዳዮቹ በሚመረጥ የግልግል ሕግ መሠረት ጉዳዮችን በዉሉ በሚመለከት አጭር ጊዜ ዉስጥ የመወሰን ግዴታ የሚኖርበት ሲሆን፣ ተቋማዊ  የግልግል  አካል ግን  በተቋሙ የግልግል ደንብ አስቀድሞ በተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የግልግል ዳኝነት ስለሚሰጥ ጉዳዩ ሊጓተት ይችላል፡፡ በባለጉዳዮቹም ላይ አላስፈላጊ ወጪ ሊያስከትል የሚችልበት አጋጣሚ ይኖራል፡፡ እነዚህን በመሳሰሉ ነጥቦች  የግልግል አካላቱ የየራሳቸው የሆነ አዎንታዊና አሉታዊ ጐን ይታይባቸዋል፡፡

ከላይ ለመነሻ ያህል የተጠቃቀሱ ነጥቦች ቢኖሩም፣ የግልግል ስምምነት ውል የሚከተሉትን አንኳር ነጥቦች በግልጽ ማመልከት ይጠበቅበታል፡፡

የግልግል ስምምነቱን የተፈፃሚነት ወሰን

በስምምነቱ የሚሸፈኑ ጉዳዮችን ዝርዝር እና አፈፃፀም በግልጽ ማመልከት ይኖርበታል፡፡

የግልግልዳኞችምርጫ

የዳኞች አመራረጥ ሂደት ምን መምሰል እንደሚኖርበት በስምምነቱ መወሰን፣ ይህ ሳይሆን ቢቀር የግልግል ተቋማቱ  ደንቦች በሚያዙት መሠረት ክፍተቱን መሸፈን እንደሚቻል በስምምነቱ ማመልከት፣በግልግል የቀረበው ጉዳይ ዓለም አቀፍ የንግድ  ግልግል ህግን የሚመለከት  በሆነ ጊዜ የግልግል ዳኝነቱ ቢያንስ  ሶስት ዳኞች በሚሠየሙበት ፖነል እንዲካሄድ እና እያንዳንዱ ወገን አንዳንድ ዳኛ የሚመርጥበት እና ሶስተኛው ዳኛ በጋራ ወይም  በግልግል ተቋሙ የሚመረጥበትን       ሥነ-ስርዓትእና ጉዳዩ የተለየ ሙያ ወይም ችሎታ የሚጠይቅ ሲሆን ይህንን ሊያሟላ በሚችል  የግልግል ዳኛ  የግልግል ዳኝነቱ እንዲመራ በስምምነቱ ላይ በግልጽ  ማመልከት ያስፈልጋል፡፡

ለግልግል መሠረት የሚሆነውን ሕግ በስምምነት መምረጥ

ተዋዋይ ወገኖች ግልግሉ የሚመራባቸውን መሠረታዊ እና የስነስርዓት ህጐች በስምምነታቸው ማመልከት፣ይህ ሳይሆን ቢቀር ደግሞ ግልግሉ የሚካሄድበትን ሀገር ሕግጋት ስለሚኖራቸው ተፈፃሚነት መስማማት፣ በዚህ ረገድ፣ ለግልግል የቀረበው  ጉዳይ ግልግሉ በሚደረግበት  ሀገር ሕግ መሠረት ለግልግል የማይቀርብ በህግ የተከለከለ  እንዳይሆን ተገቢውን ጥንቃቄ ለማድረግ ግንዛቤ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

የግልግል ዳኝነቱ የሚካሄድበትን ቦታ በግልጽ ማመልከት

ቦታ በመወሰን ረገድ ግልግሉ የሚካሄድባቸው ሀገሮች ስለውጪ አገሮች የግልግል ዳኝነት ዕውቅና መስጠትና ማስፈፀም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተደረገውን የኒውዮርክ ስምምነት ያፀደቁ ሀገሮች ቢሆኑ ይመረጣል፡፡ እንዲሁም የሀገሮቹ የግልግል ሕግ በግልግል ዳኝነት ላይ  ለፍ/ቤቶች  የሚሰጠውን የስልጣን  ክልል ግምት ውስጥ ማስገባት፣ ስለሰዎችና ስለሰነዶች ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ስለመኖራቸው ግንዛቤ መውሰድና ግልግሉ የሚደረግበትን  ከተማ በስም ለይቶ ማመልከት ያስፈልጋል፡፡

የግልግል ዳኝነቱ የሚካሄድበትን ቋንቋ  መወሰን  

ተዋዋይ ወገኖች አንድ ወይም ከዚያ በላይ ቋንቋ መምረጥና የትርጉም አገልግሎት  የሚሰጥበትን  ሁኔታ በስምምነቱ ላይ በግልጽ  ማመልከት ይኖርባቸዋል፡፡

ግልግሉ የሚካሄድበትን  የግልግል ደንብ  መምረጥ

በዚህ ረገድ የሚመረጠው የግልግል ደንብ ግልግሉ የሚታይበትን ቦታ በመምረጥ፡ ወጪና  ኪሣራን  በመወሰን፣ ስለ ዳኞች አመራረጥ እና ለግልግል ዳኞች  ስለተሰጠው  ስልጣን  ወሰን፣ ዳኝነቱ የሚካሄድበትን  ቋንቋ፣ ተፈፃሚነት  ስለሚኖራቸው ህጐች፣ ባለሙያን ለመጠቀም ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ የግልግል ዳኝነቱ የሚጠናቀቅበትን  እና ውሳኔ የሚሰጥበትን  የጊዜ ሰሌዳ፣ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የሌሎች አስተዳደር አካላት ሚና፣ ጊዜያዊ የመፍትሄ ዕርምጃ ስለሚወሰድበት አሰራር፣ እና ባለጉዳዮች ሌላ አማራጮችን ለማቅረብ ያላቸውን ዕድል በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ የባለጉዳዩችን መብት እና ጥቅም የሚያስከብር ስለመሆኑ ማረጋገጥ፤ ያስፈልጋል፡፡

በንብረት ወይም በማስረጃ ስለሚሰጥ  ጊዜያዊ የዕግድ የመያዣ ትዕዛዝ

ስምምነቱ የዕግድ ትዕዛዝ የሚሰጠው አካል ፍ/ቤት ወይም የግልግል ተቋም ስለ መሆኑ በግልጽ ማመልከት የሚኖርበት ሲሆን የዕግዱ ወይም የመያዣው ትዕዛዝ ለፍ/ቤት እንዲሰጥ ቢደረግ ስለሚኖረው ተመራጭነት በስምምነቱ ላይ ማመልከት ያስፈልጋል፡፡

ኪሣራና ወጪ

የኪሣራን እና የወጪን አከፋፈል በተመለከተ በስምምነቱ ላይ በግልጽ ማመልከት& ኪሣራ እና  ወጪው በጋራ ወይም በዳኝነት  ባለዕዳው ሊሸፈን ስለሚችል ከሁለቱ አማራጮች አንዱን መወሰን ያስፈልጋል፡፡

የግልግል ዳኝነት ውሳኔ ይዘትና ፎርም

ስምምነቱ ውሳኔው በሙሉ ድምጽ ወይም በአብላጫ ጽምጽ እንዲሰጥ እና ስራ ላይ ባሉት ህጉች መሠረት እንዲሆን ማመላከት እንዲሁም ውሳኔው በጽሁፍ ወይም በቃል ብቻ እንዲሆን ማመልከት  ይገባዋል፡፡

የመንግስታት ሚና

የሕግ ማዕቀፍ

የግልግል፣ የእርቅ እና የሽምግልና ተግባራት የነባሩን ህብረተሰብ እድገት ደረጃ በደረጃ ተከትለዉ የመጡ ማህበረሰባዊ እሴቶች መሆናቸዉ አያጠያይቅም፡፡ እነዚህን ማህበረሰባዊ እሴቶች ለማጠናከር የሚቻለዉ መንግስታት ለዘርፉ የሚሰጡት ልዩ ትኩረት ሲኖር ነዉ፡፡

ከእነዚህ አንዱ የግልግል እና መሰል ተግባራት በህግ እንዲመሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ተጠቃሽነት ይኖረዋል፡፡

ስለሆነም የግልግል የዕርቅና የሽምግልና ጉዳይ ከሚያበረክተዉ የላቀ ማኅበረሰባዊ አገልግሎት አንጻር በማየት እና ዘርፉ ከሚያበረክተዉ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ አኳያ ለእዚህ አቢይ ተልእኮ መሳካት ሲባል ጉዳዩን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችሉ ህግጋትን ማዉጣት ወቅታዊ ጉዳይ ከመሆኑም ሌላ እግረ መንገዱን፣  ማህበረሰባዊ እሴትን ከማሳደግ አንጻርም ሊታይ የሚገባው ዋጋ ያለው ቁም ነገር ነዉ፡፡ በዚህ ረገድ የዘመኑን ህብረተሰብ አሰተሳሰብ ከነባሩ ማህበረሰባዊ እሴት ጋር በማቀናጀት ተስማሚ ሆነዉ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚሰራባቸዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አለም-ዓቀፍ የንግድ ህግ ኮሚሽን ሞዴል የግልግል ና የእርቅ ህግጋት አንጻር የተቃኙ ዘመናዊ አዳዲስ ህግጋትን ማዉጣት ወይም ነባር ህግጋትን እንደአስፈላጊነቱ ማሻሻል ከመንግስታት የሚጠበቅ ተግባር ይሆናል፡፡

ተቋማትን ማስፋፋት ወይም ማደራጀት

የግልግል፣ የእርቅ ወይም የሽምግልና ጉዳይ በአመዛኙ የግል ተቋማትን ወይም የግለሰቦችን ሚና የሚጠይቅ ቢሆንም ተቋማቱ ከታች እስከ ላይ ባለ የመንግስት መዋቅር ድጋፍ እንዲደረግላቸዉ እና ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸዉ አስፈላጊዉን ሁሉ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ እንዲህ ሲሆን በመንግስት በኩል የሚወጡ የግልግል፣የእርቅ ወይም የሽምግልና ህግጋት ተፈፃሚነት ኖሯቸው በዘርፉ እንዲሣካ የሚፈለገው አላማ ግቡ ላይ ለማድረስ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

አለም አቀፋዊ ስምምነቶችን ማድረግ  

የግልግል፣ የእርቅ ወይም የሽምግልና ጉዳዮችን ለማከናወን በባለጉዳዮች የሚደረግ የዉል ስምምነት መኖር ተቀዳሚ ጉዳይ ነዉ፡፡

ስለሆነም የአንድ አገር መንግስት ከሌሎች የዉጭ አገር መንግስታት ወይም ኩባንያዎች ጋር ያለዉን ኢኮኖሚያዊ ትስስር በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ለመምራት እንዲሁም አለመግባባቶች ሲከሰቱ በግልግል፣ በእርቅ ወይም በሽምግልና ለመፍታት የሁለትዮሽ (Bilaterial) ወይም የሦስትዮሽ (multilateral) ስምምነት ማድረግ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡

በዉጭ ሀገር የተሰጠ የግልግል ዳኝነት ዉሳኔዎችን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ዓለም-አቀፋዊ ስምምነቶችን ማጽደቅ

በዚህ ረገድ በፅሁፉ ልዩ ልዩ ክፍሎች ለማሰገነዘብ እንደተሞከረዉ የግልግል ጉዳይ ተመራጭ ከሚሆንባቸው አበይት ምክንያቶች መካከል፣ በአንድ ሀገር የተሰጠን የግልግል ዳኝነት ዉሳኔ በሌላ አገር ለማሰፈጸም ያለዉ ብቃት ነዉ፡፡

እንዲህ ሲሆን ግን የግልግል ዳኝነቱ እንዲፈጸም ጥያቄ የሚቀርብበት አገር መንግስት ለጉዳዩ ተገቢነት ያለዉ አ.ኤ.አ. በ1958 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣዉን የኒዉዮርክ ስምምነት ያጸደቀ መሆን አስፈላጊ ይሆናል፡፡       

የተጠቀሰው ስምምነት፣ በውጪ ሀገር የተሰጠን  የግልግል ዳኝነት  ዕውቅና ስለመስጠትና ስለ ማስፈፀም የሚመለከት ስለሆነ፣ የአብዛኛዎቹ ሀገራት መንግስታት በመንግስት ደረጃ  ወይም በዜጐቻቸው እና በውጭ ኩባንያዎች መካከል የሚያጋጥሙ አለመግባባቶችን  በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመፍታት እንዲቻል እንዲሁም በየአገሮቻቸው  የሚሰጡ የግልግል ዳኝነት ውሣኔዎችን  አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ  በውጭ ሀገራት ለማስፈፀም  ሲባል  የኒውዮርክ ስምምነቱን በማጽደቅ የስምምነቱ አባል አገራት  ሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ  ይታወቃሉ፡፡

በእነዚህ ሀገሮች ዘንድ በግልግል ዳኝነት  የሚሰጥን ውሣኔ ለመፈፀምም ሆነ ለማስፈፀም  አዳጋች አይሆንም፡፡

ከላይ የተዘረዘሩት ዋና ዋና ነጥቦች በማንኛውም የግልግል ውል ላይ ሊካተቱ የሚገባቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ የእነዚህ ነጥቦች መጓደል ስምምነቱን  የተሟላ እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም ተዋዋይ ወገኖች የሚያደርጉት የግልግል ስምምነት ውል ከእነዚህ ነጥቦች አኳያ የተቃኘ መሆን ይጠበቅበታል፡፡