ፍርድ ቤቱ በእነ አቡበከር አህመድ መዝገብ የሚገኙ የሁለት ተከሳሾች ቃልን አደመጠ

Apr 11 2014

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት  4ኛ ወንጀል ችሎት ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የሽብር ተግባር ወስጥ ተሳትፎ አድርገዋል በሚል ከተከሰሱት ግለሰቦች መካከል የ8ኛ ተከሳሽ መሀመድ አባተና የ9ኛ ተከሳሽ አህመድ ሙስጠፋን የተከሳሽነት ቃላቸውን ትናንት አድምጧል።

8ኛ ተከሳሽ መሀመድ አባተ ሐምሌ 7 2004 ዓ.ም በአንዋር መስጊድ ለተሰበሰበው ህዝብ በአውሊያ መስጊድ ፖሊስ ሙስሊሞችን ስለገደለ ለሟቾች ፀሎት እና ሰላት እንዲደረግ መልዕክት አስተላልፎ እንደነበር ለችሎቱ ገልጿል።

ይሁንና በእለቱ የሞተ ሰው አለመኖሩ መረጃ ሲደርሰኝ ወዲያውኑ አስተባብያለሁ ብሏል።

ከፖሊስ ጋር ምንም አይነት ግጭት ውስጥ መግባት የለብንም በማለት ህዝቡን ከረብሻና ከስሜታዊነት እንዲወጣ ሳረጋጋ ነበር ሲልም ተናግሯል።

ተከሳሹ ሰኔ 21 2004 ዓ.ም ምሽት በፈቲ መስጊድ መንግስት ሃይማኖታችንን እየከፋፈለ ነው ብሎ አለመናገሩንና በስአቱም ሰው አለመኖሩን ለችሎቱ ገልጿል።

ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ፖለቲካዊ ግብ ለማሳካት በህቡዕ አልተንቀሳቀስኩም ሲል ለክሱና ለቀረበበት ማስረጃ ምላሽ ሰጥቷል።

9ኛ ተከሳሽ አህመድ ሙስጠፋ በበኩሉ ከራሴ አስተሳሰብ ውጭ የሌላው አስተሳሰብ እንዳይኖር በማድረግ  አክራሪነትን አላራመድኩም ፤ ሃይማኖታዊ መንግስት የማቋቋም አላማም አልነበረኝም ብሏል።

አቃቤ ህግ በክስና በማስረጃዎቹ ከሀገር ውጭ ስልጠና በመውሰድ ሃይማኖታዊ መንግስት መመስረት ስለሚቻልበት ሁኔታ መክሯል ቢልም የወሰድኩት ስልጠና ስለሃይማኖት መቻቻል እንዲሁም ስለ አመክኒዮ ነው ሲል ለችሎቱ አብራርቷል።

ከመፅሀፍ ሀሳብ ተወስዶ ውይይት የተካሄደበት ጉዳይም ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት ያሉት የሽግግር ደረጃዎች የተዳሰሱበት ሳይሆን ስለ ስልጣኔና የህዳሴ ጉዞ ሳይንሳዊ ትንታኔ የተሰጠበት ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

አቃቤ ህግ ደግሞ ከዚህ በፊት የተሰጠ ማስረጃና ብይን እየቀረበ የተከሳሽነት ቃል መሰጠቱ የስነ ስርአት ህጉን የተከተለ አይደለም የሚል አቤቱታ ለችሎቱ አቅርቧል።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው አቃቤ ህግ አቤቱታ ያቀረበው ተከሳሾቹን በማቋረጥ ሀሳብ እንዲጠፋባቸው ለማድረግ ስለሆነ ጥያቄው ተገቢ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል።

ችሎቱም የስነ ስርዓት ህጉን የሚጥስ የክርክር አመራር ባለመስተዋሉ የተለየ ትዕዛዝ እንደማይሰጥ በመጥቀስ የግራ ቀኙን ክርክር ሳይቀበል ቀርቷል።

ችሎቱ የቀሪ ተከሳሾችን የተከሳሽነት ቃል ዛሬ የሚያዳምጥ ይሆናል።

Read 38011 times
Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)