በህገወጥ መንገድ መሬት የወሰዱት የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባል በ3 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ

Fanabc Mar 10 2014

በህገ ወጥ የመኖርያ ቤት ማህበር ስም 460 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል የተባሉ አንድ የቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት አባል በሶስት ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ።

ለቅጣት ያበቃቸው ወንጀል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ትዕግስት ለፍሬ በተባለ ህገወጥ የመኖሪያ ቤት ማህበር ስም 460 ካሬ ሜትር ቦታ በመመዝበራቸው ነው።

የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቢ ህግ ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀምና መንግስታዊ ሰነዶችን በሀሰት ማዘጋጀት በሚሉ የሙስና ወንጀሎች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ማህበራት ማደራጃ ኦፊሰር የነበሩት አቶ አሊ መሀመድን ፣ አቶ ሙባረክ አብደላን እና ዛሬ ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸውን ሻለቃ አብረሃ ግደይን ከሷቸው ነበር።

ተከሳሾቹ ማንነታቸው ካልታወቁ የክፍለ ከተማው ማህበራት ማደራጃ ጋር በመመሳጠር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ያልሆኑ 12 ግለሰቦች ሀሰተኛ መታወቂያ በማውጣት ማህደራቸው በህገወጥ መንገድ ህጋዊ ሰነድ እንዲሆን በማድረግ 460 ካሬ ሜትር ቦታ ለራሳቸውና ለተለያዩ ግለሰቦች እንዲያውሉ አድርገዋል የሚለው በክሱ ተጠቅሷል።

እኝህ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከአባልነት እስከ አመራርነት ተሳትፈው በጡረታ ላይ ይገኙ የነበሩት ሻለቃ አብርሃ ግደይ በምዝበራው ውስጥ ከነበራቸው ተሳትፎ ባሻገር የህገወጥ ማህበሩ አባላት ውክልና አለኝ በማለት ከ10 ሰዎች ከእያንዳንዳቸው 75 ሺህ ብር መቀበላቸውም ተረጋግጧል።

ከእሳቸው ውጭ የነበሩት ሁለት ተከሳሾች ቀደም ብሎ በነፃ የተሰናበቱ ሲሆን ግለሰቡ ሀሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት ጥፋተኛ መባላቸውን ተከትሎ ያቀረቡትን አራት የጥፋት ማቅለያዎችን የተቀበለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ በሶስት አመት ፅኑ እስራት ቀጥቷቸዋል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በህገወጥ መንገድ የተያዘው 460 ካሬ ሜትር ቦታ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ታዟል።

Read 34578 times Last modified on Mar 10 2014