ከእነ አቶ መላኩ ፈንታ ጋር ታስረው የነበሩ አንድ ተጠርጣሪ ባለሀብት ተፈቱ

Ethiopian Reporter Mar 06 2014

የቀድሞው ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኃላፊ መዝገብ ለብይን ተቀጠረ

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞች፣ ባለሀብቶች፣ ነጋዴዎችና ከተለያዩ ድርጅቶች ባለቤቶች ጋር በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ታስረው የነበሩት አቶ ማሞ ኪሮስ የተባሉ ባለሀብት በዋስ ተለቀቁ፡፡

የፌደራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ፣ በሙስና ወንጀል ጠርጥሯቸው በቁጥጥር ሥር ላለፉት አሥር ወራት በእስር የቆዩት አቶ ማሞ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. የተፈቱት በ30 ሺሕ ብር ዋስ ነው፡፡

አቶ ማሞ ‹‹ከተማ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› የሚባል ድርጅት ያላቸው ሲሆን፣ መንግሥት ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ የፈቀደላቸውን የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማሽኖችን ቢኖሩም፣ ያላስገቡትን እንዳያስገቡ በማስመሰል ሐሰተኛ ሰነድ አቅርበዋል በሚል ተጠርጥረው መታሰራቸው ይታወሳል፡፡ ተጠርጣሪው በጠበቆቻቸው አማካይነት ሲከራከሩ ከርመው፣ በብይን ክሳቸው ሙስና ሳይሆን ‹‹ከባድ የማታለል ወንጀል ነው›› በማስባላቸውና ክሱም መታየት ያለበት በኮሚሽኑ ሳይሆን በፌደራል ዓቃቤ ሕግ በኩል መሆኑን በመግለጻቸው፣ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ተቀብሏቸዋል፡፡ 

የፍርድ ቤቱን ብይን ተከትሎ ጠበቆቻቸው ዋስትና እንደማያስከለክላቸው ለችሎቱ በመግለጻቸውና ፍርድ ቤቱም በመረዳቱ በ30 ሺሕ ብር ዋስ ተለቀዋል፡፡ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን በማሰማቱ፣ አቶ ማሞ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ለማሰማት ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ሌላው የተመለከተው የክስ መዝገብ፣ የእነዳዊት ኢትዮጵያን ነው፡፡ ዳዊት ኢትዮጵያ የለገሀር ጉምሩክ ኃላፊ የነበሩ ናቸው፡፡ ከእሳቸው ጋር ክስ የቀረበባቸው አቶ ዘሱ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ኢዮብ ጌታቸው፣ በላይነህ ደሴና እሸቱ አጥላውን የክስ መቃወሚያ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ፣ መቃወሚያውን እንዳልተቀበለውና ውድቅ ማድረጉን በመግለጽ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ አዟል፡፡ 

ተጠርጣሪዎቹም ክሱን እንደማይቃወሙ፣ ነገር ግን ድርጊቱን እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የእምነትና ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የኮሚሽኑን ዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ለመስማት ለመጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት በዕለቱ የተመለከተው ሌላው መዝገብ የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት የእነ አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤልን የክስ መዝገብ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ይዞ የነበረው ዓቃቤ ሕግ በጽሕፈት ቤት በኩል እንዲያስገባ ታዞ በነበረው 11ኛ ክስ ላይ ባቀረበው የክስ ማሻሻያ ላይ ብይን ለመስጠት የነበረ ቢሆንም፣ በሥራ መደራረብ ምክንያት እንዳልደረሰለት በመግለጽ ለመጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

Read 33833 times Last modified on Mar 06 2014