የፌደራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሁከት ፈጥረሀል ተብሎ የሰጠው ውሳኔ ተሻረ

Ethiopian Reporter Mar 03 2014

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ዘጠነኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል በአንድ የፌደራል ፖሊስ አባል ላይ የቅጣት ውሳኔ ሲሰጥ፣ ‹‹በፖሊስ አባሉ ላይ›› ሁከት የፈጠረው ችሎቱ መሆኑን በመጠቆም፣ የሰጠውን ውሳኔ ሻረ፡፡

የከፍተኛው ፍርድ ቤት የካቲት 12 ቀን 2006 ዓ.ም. የሥር ፍርድ ቤትን የቅጣት ውሳኔ ሊሽር የቻለው፣ ለፍርድ ቤት ያልተገባ ባህሪ በማሳየት፣ ሁከት በመፍጠርና ዳኛ በማመነጫጨቅ ፍርድ ቤትን በመድፈር ወንጀል፣ የስድስት ወራት እስራት ቅጣት የተጣለባቸው የፌደራል ፖሊስ አባል የሆኑት ኢስፔክተር ሙሉ አሰፋ ባቀረቡት ይግባኝ መሆኑን የፍርድ ዝርዝሩ ያብራራል፡፡

ይግባኝ ባዩ ኢንስፔክተር ሙሉ የሥር ፍርድ ቤት ታኅሳስ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ቅጣት ቢጥልባቸውም፣ ለፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ይግባኝ በማለታቸው ከአራት ቀናት እስራት በኋላ በእግድ መለቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ኢንስፔክተር ሙሉ ጥር 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ይግባኝ፣ ‹‹በሕዝብና በመንግሥት የተጣለብኝን አደራ ለመወጣት በሥራ ላይ በነበርኩበት ወቅት በድንገት በተፈጠረ ችግር ነው፡፡ በቦታው ስላልነበርኩ ስለተባለው ረብሻ የማውቀው ነገር  የለም፡፡ ፍርድ ቤቱ ለምን ፈለገኝ ብዬ ችሎቱ ስገባ ለምን እንደተጠራሁ ሊነገረኝ ሲገባ፣ የለበስኩትን የፖሊስ መለዮ አውልቅና ተፈተሽ በማለት ያልጠበቅኩትን ንግግር ከችሎቱ በመሰማቴ ደንግጬ ነው እንጂ፣ ችሎቱን ለመድፈር ወይም በመናቅ የተደረገ አይደለም፡፡ ጥፋተኛም አይደለሁም፤›› ማለታቸውን ፍርዱ ያብራራል፡፡ በመሆኑም ጥፋተኛ እንኳን ቢሆኑ ውሳኔው የተጋነነ በመሆኑ፣ በገደብ እንዲደረግላቸው፣ ይኼ ከታለፈ ለአገራቸውና ለወገናቸው ከ30 ዓመታት በላይ ያገለገሉ በመሆናቸው፣ ቅጣቱ ተሽሮ በነፃ እንዲሰናበቱ ወይም የታሰሩት በቂ ሆኖ ቀሪው በገንዘብ እንዲቀየርላቸው መጠየቃቸውን ፍርድ ቤቱ ያስረዳል፡፡ የፌደራል ፖሊስ ነገረ ፈጅ ጥብቅና ቆመው ስለኢንስፔክተር ሙሉ መከራከራቸውም በፍርዱ ተጠቅሷል፡፡

የኢንስፔክተር ሙሉን አቤቱታ የሰሙት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ አሰፋ አብርሃ ሲሆኑ፣ የሥር ፍርድ ቤት ችሎት ‹‹የመዘገበው ጥፋት ነው? ጥፋት ከሆነስ ቅጣቱ ተመጣጣኝ ነው?›› የሚሉትን ነጥቦች አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር አገናዝቦ ለመመርመር ‹‹ያስቀርባል›› ማለታቸውንም የፍርድ ሰነዱ ይገልጻል፡፡ የሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔና የይግባኝ ቅሬታቸውንም አግባብነት ካላቸው የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ፣ ኢንስፔክተር ሙሉ በችሎቱ ሰንዝረዋል የተባሉት ንግግርና ችሎቱን ጥሎ መውጣት ‹‹ጥፋት ነው? ወይስ አይደለም?›› የሚለውን ነጥብ በመያዝ መመርመሩንም ፍርዱ ያሳያል፡፡

ይግባኝ ባዩ በፍርድ ቤቱ ግቢ የሚገኙ ፖሊሶች ኃላፊ በመሆናቸው ሁከት  ፈጥረዋል ስለተባሉት ፖሊሶች እንዲያስረዱ ከመጠራታቸው ውጪ፣ ሁከት ፈጥረዋል ከተባሉት የፖሊስ አባላት ጋር አለመሆናቸውን ፍርዱ ይገልጻል፡፡ በወቅቱ የሥር ፍርድ ቤት ምስክሮችን ስለማዳመጡም የሚያውቁት ነገር ስለመኖሩ በቅጣት መዝገቡ ላይ የተገለጸ ነገር አለመኖሩንም በፍርዱ ተችቷል፡፡ ኢንስፔክተሩ የፍርድ ቤቱን ግቢ ለመጠበቅና ለማስጠበቅ በመንግሥት እምነት ተጥሎባቸው በሥራ ላይ ያሉ መሆናቸውንም ያብራራል፡፡

በፍርድ ቤቱ አሠራር ስለእያንዳንዱ ነገር እንዲያስረዳ የታዘዘ ሰው ወይም ኃላፊ የተፈለገበት ጉዳይ ተነግሮት፣ ስለጉዳዩ እንዲያስረዳ ከማድረግ ውጪ፣ እንደተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ እንደድፍረት በመቁጠር ያለቅድመ ሁኔታ ወደ ችሎት እንደገባ ያለምንም ጥያቄ ‹‹ተፈተሽ›› ማለት ከተለመደው የፍርድ ቤት ዳኝነት አሠራር በጣም ያፈነገጠ መሆኑንም ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ይግባኝ ባዩ የሚያስተዳድሯቸው ፖሊሶች ፈጽመዋል ስለተባለው ጉዳይ እንዲያስረዱ ሲቀርቡ፣ በድንገት ‹‹ተፈተሽ›› ማለት የሕግ መሠረት በሌለው ሁኔታ መብታቸውን መጣስና ማወክ መሆኑን፣ አንድ ሰው በሕግ ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ ንፁህ ሆኖ የመገመት መሠረታዊ መብቱንም የሚጋፋ መሆኑን ያትታል፡፡ በመሆኑም ይግባኝ ባይ እንዲቀርቡ የተፈለገበት ጉዳይ ሳይነገራቸው ‹‹ተፈትሽ›› ሲባሉ፣ ‹‹አልፈተሽም›› በማለት ከችሎት መውጣታቸው ‹‹ፍርድ ቤትን መድፈር ነው? ወይስ ንፁህ ሆነው የመቆጠር መብታቸውን ለመጠበቅና ለማስከበር ነው?›› የሚለውን ለማሳየት መገደዱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ድፍረት (Contempt) የሚለውን ቃል በብላክ ሎው መዝገበ ቃላት (Black Law Dictionary) ተርጉሞ በዝርዝር ያስቀመጠው ፍርድ ቤቱ፣ ፍርድ ቤት የመድፈር ድርጊት ፈጻሚ ወገን ሳያውቀው የተዘጋጀ የክስ ማመልከቻ የሚቀርብበትና ሳይሟገትና ክርክር ሳያደርግ ወዲያውኑ እንደሚወሰንበት ፍርዱ ያብራራል፡፡ የክስ ሒደቱ ግን፣ በክስ ሒደት ሥርዓት ያለውን መብት ሁሉ የሚያሳጣ ወይም የማይከተል ስለሆነ፣ ከመደበኛው የክስ ሥርዓት ያፈነገጠና በቀጥታ ወዲያውኑ የሚቀጣ መሆኑን ያክላል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን፣ በሕገ መንግሥቱ ከተረጋገጡት የመስማት፣ የመከራከርና በሕግ አግባብ የመዳኘት ዋስትናዎችን የሚጥስና ሥልጣኑን መጠቀም እጅግ አሳሳቢና አስጨናቂ በመሆኑ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልግ መሆኑን ያብራራል፡፡ በውኃ ቀጠነ ሊፈጸም የሚገባ አለመሆኑን፣ የዳኝነት ሥራ አስቸጋሪ ባህሪ የሚገለጽበት ጥቅል የሆነ አስተዋይነትንና ሆደ ሰፊነት የሚያስፈልገው፣ በችሎታ፣ በፀባይና በተግባር ፍርድ ቤትን ለሚፈሩት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ መሆኑንም ፍርዱ ያትታል፡፡

ይግባኝ ባዩ ‹‹ተፈተሽ›› ሲባሉ ‹‹አልፈተሽም›› ብለው ከችሎት ወጥተው ከመሄዳቸው ሌላ ‹‹በፍርድ ቤቱ አላፌዙም፣ ድንጋይ አላነሱም ወይም ብረት አላነሱም፤›› ይኼንንም ኢንስፔክተሩ ለሥር ፍርድ ቤት ድርጊቱን ከመፈጸማቸውንና በይግባኙም ማረጋገጫቸውን በመጥቀስ፣ ይግባኝ ባዩ ፍርድ ቤት በቀና መንፈስ የቀረቡት ፍርድ ቤትን በማክበር መሆኑን ይገልጻል፡፡

ይግባኝ ባዩ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ለመፈጸም ቢሆንም፣ ፍርድ ቤትን የመድፈርና የመናቅ ወንጀል ለመፈጸም እንደሆነ የሥር ፍርድ ቤት የውሳኔ መዝገብ እንደሚያስረዳም ያክላል፡፡

የኢንስፔክተር ሙሉ ድርጊት በዓይን ሲታይና በጆሮ ሲሰማ የፍርድ ቤት ድፍረት ሊመስል እንደሚችል የሚያትተው ፍርዱ፣ በትክክል በይግባኝ ንፁህ ሆኖ የመገመት መብት ላይ ሁከት የፈጠረው የሥር ፍርድ ቤት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ይግባኝ ባይ የሕግ ተገዥ ሆነው ከቀረቡት የፍትሕ ማስከበሪያ አደባባይ ከሆነው የሥር ፍርድ ቤት፣ ከተለመደው የዳኝነት አሠራር ባፈነገጠ መንገድ፣ ባልተገባ ሁኔታ የፌደራል ፖሊስ አባሉን ያለተግባራቸው በመፈረጅ ያለቅድመ ሁኔታ ‹‹ተፈተሽ›› ማለት ግለሰቡ ንፁህ ሆነው የመገመት መብትን በማወክና በመድፈር ‹‹የግለሰቡን መብት የመጣስ ተግባር የፈጸመው የሥር ፍርድ ቤት፤›› ነው ብሏል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የሰጠው የቅጣት ውሳኔ ወንጀልን የሚያቋቁሙት ሦስት የወንጀል ማቋቋሚያ መመዘኛዎች መሟላታቸውንና አለመሟላታቸውን በተገቢው ሁኔታ ሳያገናዝብ የሰጠው ውሳኔ ሆኖ ስለተገኘ፣ ኢንስፔክተር ሙሉ አሰፋ ጥፋተኛ አለመሆናቸውንና የተወሰነባቸው የቅጣት ውሳኔ መሻሩን አስታውቋል፡፡ 

የፌደራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘጠነኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ታኅሳስ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. በኢንስፔክተር ሙሉ አሰፋ ላይ የስድስት ወራት የእስራት ቅጣት መወሰኑን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ቅጣቱ ታግዶላቸው መለቃቃቸው መዘገቡም አይዘነጋም፡፡

Read 34540 times