በሀይማኖት ስም የሽብር ድርጊት ለመፈፀም የተንቀሳቀሱ 4 ተከሳሾች በ12 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ

Fanabc Feb 27 2014

በእስልምና ሀይማኖት ስም የሽብር ድርጊት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ አራት ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ12 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጡ።

ተከሳሾቹ በደቡብ ትግራይ ዞን፥ ራያ አላማጣ ወረዳ የዋጃ ጥሙጋ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ፥ ሀቢብ ደረሰ ጓንጉል፣ ኢድሪስ ለጋስ መሀመድ፣ መምህር ከድር አደም እድሪስና አብዱልለጢስ ሀሸም ጉባለ የተባሉ ናቸው።

ተከሳሾቹ የእስልምና ሀይማኖትን ሽፋን በማድረግ በአካባቢው የሚገኙ የመንግስት ተሿሚዎች ከስልጣን ይውረዱ፣ የእስልምና ምክር ቤት አባላትን የመንግስት ጉዳይ አስፈፃሚዎች ናቸው እኛን የሚወክሉ አይደሉም፣ በእስልምና ሀይማኖት  ስም የታሰሩ ዜጎች ይፈቱ የሚሉ ጥያቄዎችን በመያዝ 60 የሚሆኑ ሰዎች አካባቢውን ሲረብሹ ነበር ብሏል አቃቤ ህግ።

በዚህም መሰረት የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ አቃቢቤ ህግ፥ በተከሳሾቹ ላይ በህዝብ የተመረጡ የመንግስት አካላትን በሀይል ለማውረድና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሀይል ለማፍረስ ሞክረዋል በማለት ክስ መስርቶባቸዋል።

ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ ቢክዱም ማስተባበል ባለመቻላቸው፥ የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ብሏቸዋል።

በዚህም መሰረት እያንዳንዳቸው በ12 ዓመት ፅኑ እስራት ሲቀጡ ፥ በዚህ መዝገብ ክስ ውስጥ ሌሎች አመስት ተከሳሾች ከቀረበባቸው ክስ ነፃ በመሆናቸው በነፃ ተሰናብተዋል።

Read 35065 times