የቀድሞው አገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ እህት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን መነፈጋቸውን ተናገሩ

Ethiopian Reporter Feb 24 2014

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከወንድሞቻቸው ጋር በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የአገር ውስጥ ድኅንነት ኃላፊ አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል እህት፣ ወ/ሪት ትርሐስ ወልደ ሚካኤል የፌደራል ማረሚያ ቤት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንደነፈጋቸው የካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ወ/ሪት ትርሐስ በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት እንዳስረዱት፣ ባለቤታቸው የውጭ አገር ዜጋ መሆናቸውን በማስረዳት በስልክ እንዲያገናኟቸው የማረሚያ ቤቱን ኃላፊዎች ሲጠይቁ መከልከላቸውን፣ ነገር ግን ለሌሎች እንደሚፈቀድ አመልክተዋል፡፡

ባቢ አንጄሎ የተባሉ የውጭ አገር ዜጋ የሆኑት ባለቤታቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ፈቃድ ጠይቀውና አስፈቅደው፣ እንዲሁም የፈቃድ ወረቀት ይዘው ማረሚያ ቤት ቢሄዱ እንደተከለከሉ የገለጹት የወ/ሪት ትርሐስ ጠበቆች፣ እንዲያውም በወ/ሪት ትርሐስ ምክንያት ለሌሎችም ክልከላ መደረጉን ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡

ባለቤታቸው በችሎት ተገኝተው ወደመጡበት ጣሊያን የሚመለሱት የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. መሆኑን በማስረዳት፣ ፍርድ ቤቱ በችሎት ስለወለዱት ልጅ እንዲነጋገሩ አንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡

በፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳር፣ በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት የሴቶች ማረሚያ፣ ማረፊያና ጥበቃ ደኅንነት ዘርፍ አስተባባሪ ሱፐር ኢቴንዴንት ለተእግዚአብሔር ገብረመድኅን በችሎት ቀርበው እንዳስረዱት፣ ወ/ሪት ትርሐስ ‹‹ተከልክያለሁ›› የሚሉት ከእውነት የራቀ መሆኑን ነው፡፡ ማንም ቢሆን ከውጭ አገር በሕጋዊ መንገድ መግባቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይዞ ወደ ማረሚያ ቤቱ ከቀረበ፣ እንደማንኛውም ዜጋ እንደሚስተናገድ አስረድተዋል፡፡

የውጭ ዜጋ በስልክ እንዳይገናኝ ለምን አንደተከለከለ ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባፀደቀው ደንብ ቁጥር 138/99 አንቀጽ 13 (1እና2) መሠረት ማንኛውንም ዜጋ እንደማያስተናግዱ፣ ስልክን በሚመለከት ደንቡ ስለማያካትት የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልታከለበት በስተቀር እንደማያገናኙ አስተባባሪዋ ገልጸዋል፡፡

የወ/ሮ ትርሐስ ባለቤት በሕጋዊ መንገድ መግባታቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መረጋገጡ ተገቢ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በመግለጽ፣ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጻፈላቸውን ደብዳቤ እንዲያቀርቡ ጠይቋል፡፡

ያልተሟሉም ቢሆን በቀረቡት ማስረጃዎች ወ/ሪት ትርሐስና ባለቤታቸው ልጅ መውለዳቸውን የሚያረጋጥ ሰነድ  መኖሩን፣ ባልና ሚስትም ናቸው ማለትም እንደሚቻል በመግለጽ፣ ለአሥር ደቂቃ ያህል እንዲነጋገሩ ችሎቱ በመፍቀዱ ሊገናኙና ሊነጋገሩ ችለዋል፡፡

የእነ አቶ ወልደ ሥላሴ የክስ መዝገብ ለየካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም. ተቀጥሮ የነበረው፣ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በመዝገቡ 11ኛ ክስ ላይ የነበረውን ክስ አሻሽሎ እንዲያቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ ዓቃቤ ሕግ ‹‹ቢሮ ውስጥ ጠረጴዛ ላይ ረስቼው ስለመጣሁ ከሰዓት በኋላ ከመዝገቡ ጋር አያይዛለሁ›› በማለቱ ፍርድ ቤቱ፣ ‹‹ይህም ነገር በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ነው ጥንቃቄ አድርጉ፤›› በማለት አስጠንቅቆ፣ ከመዝገቡ ጋር እንዲያያዝና የተጠርጣሪ ጠበቆችም ከጽሕፈት ቤት እንዲወስዱ በመንገር ለየካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Read 34099 times Last modified on Feb 24 2014