ኅብረት ኢንሹራንስ ለሰጠው ዋስትና የ84 ሚሊዮን ብር ክስ ተመሠረተበት

Ethiopian Reporter Feb 24 2014

በአማራ ክልል በጎንደር ዞን ከሳንቻ እስከ ቀራቀር ያለውን መንገድ በመገንባት ላይ የነበረው ጥበብ ኮንስትራክሽን በውሉ መሠረት ሥራውን ሊሠራ ባለመቻሉና የኮንትራት ውሉ በመቋረጡ፣ ለኮንትራክተሩ የቅድመ ክፍያ ዋስትና የሰጠው ኅብረት ኢንሹራንስ 84 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ክስ መሠረተበት፡፡

ባለሥልጣኑ በድርድር 52 ሚሊዮን ብር ክፍያ እንደተፈጸመለት ተሰምቷል፡፡

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ጥበብ ኮንስትራክሽን በውሉ መሠረት ሥራውን ባለመሥራቱ ፕሮጀክቱ እንዲነጠቅ ሲወሰን፣ ለቅድመ ክፍያ የተሰጠው ዋስትና ገቢ መደረግ ስላለበት ኢንሹራንስ ኩባንያው ተጠይቋል፡፡

በዚህም መሠረት ለኮንትራክቱ የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና የሰጠው ኅብረት ኢንሹራንስ የሰጠው የመድን ሽፋን 100 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ ኮንትራክተሩ የሠራው ሥራና የተከፈለው ክፍያ ተቀንሶ ባለሥልጣኑ 84 ሚሊዮን ብር እንዲከፈለው ኢንሹራንስ ኩባንያውን ጠይቋል፡፡ ሆኖም ኢንሹራንስ ኩባንያው ክፍያውን እንዲፈጽም በተሰጠው የጊዜ ገደብ ባለመፈጸሙ ባለሥልጣኑ ወደ ክስ መሄዱን  ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢንሹራንስ ኩባንያውም በሰጠው ዋስትና መሠረት ክፍያውን ለመክፈል እንደሚችል ገልጾ፣ በተጠየቀው የክፍያ መጠን ላይ መደራደር እንደሚፈልግ በማስታወቁ፣ በተደረገው ድርድር መሠረት መክፈል የሚገባው 52 ሚሊዮን ብር ነው በማለት ይህንኑ ክፍያ ፈጽሟል፡፡ ባለሥልጣኑ ግን ሊከፈለኝ ይገባል የሚለው ክፍያ 84 ሚሊዮን ብር በመሆኑ በቀሪው ክፍያ ላይ ለመደራደር ቀጠሮ ተይዟል፡፡

ኅብረት ኢንሹራንስ በበኩሉ፣ ለሰጠው ዋስትና ክፍያው መከፈል እንዳለበት በማመን ወደ ድርድር በመግባት ትክክለኛ ክፍያ ነው ብሎ ያመነበት 52 ሚሊዮን ብር በመሆኑ ይህንኑ ፈጽሜያለሁ ብሏል፡፡ ቀሪውን ክፍያ በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ባይሰጥም፣ ቀረ በሚባለው ክፍያ ላይ ተጨማሪ ውይይት እየተደረገ መሆኑን ግን አምኗል፡፡ ባለሥልጣኑ ግን ክሱ አሁንም እንዳለና ከድርድሩ የሚገኘው ውጤት የማያረካው ከሆነ ክሱን ይቀጥላል ብሏል፡፡

በባለሥልጣኑ ክስ መሠረት ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመመልከት ለመጋቢት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙም ታውቋል፡፡

 ኅብረት ኢንሹንስ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በእንዲህ ዓይነት ዋስትና የከፈለው ክፍያ በግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ታሪክ ትልቅ ነው ተብሏል፡፡ ከኩባንያው አቅም አንፃር ይህንን ያህል ክፍያ መክፈሉ ከፍተኛ ቢሆንም፣ ለጥበብ ኮንስትራክሽን ኩባንያ  የሰጠው ዋስትና የጠለፋ ዋስትና ተገብቶለት ስለነበር፣ ኅብረት ኢንሹራንስ ከ52 ሚሊዮን ብር ውስጥ የከፈለው ከአንድ ሚሊዮን ብር ያነሰ መሆኑ ይነገራል፡፡ ቀሪው ክፍያ ግን በጠለፋ ዋስትና ሰጪው ኩባንያ አማካይነት የተከፈለ መሆኑን ከኅብረት ኢንሹንስ የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡ 

እንደ ኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን መረጃ፣ ከጥበብ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር የነበረው ውል ከአንድ ዓመት በፊት እንዲቋረጥ በመደረጉ የመንገዱ ሥራ ቆሟል፡፡ ቀሪውን ሥራ በአዲስ ሥራ ተቋራጭ ለማስቀጠል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ በቅርቡም አሸናፊው ኮንትራክተር ይፋ ተደርጐ ሥራው ይጀመራል ተብሏል፡፡ ጥበብ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተረከበው የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በአማራ ክልል ጎንደር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ለዚህ ፕሮጀክት ጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 550 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡

Read 35239 times Last modified on Feb 24 2014