ይህን ተከትሎ የተከለከሉ ተግባራትን፣ የሚወሰዱ እምርምጃዎችንና የመብት እገዳዎችን በዚህ ደንብ መደንገግ በማስፈለጉ፤

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 3/2012 አንቀፅ 4/1/ መሰረት የሚከተለውን ደንብ አውጥቷል::

1. አጭር ርእስ

ይህ ደንብ ‘‘ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ማስፈፀሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር--------/2012’’ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል::

2. ትርጓሜ

ለዚህ ደንብ አላማ፡-

 1. ‘‘አዋጅ’’ ማለት የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ነው፤
 2. ‘‘የሚኒስትሮች ኮሚቴ’’ ማለት በዚህ ደንብ አንቀፅ 5 የተቋቋመው ኮሚቴ ማለት ሲሆን እንደአስፈላጊነቱ፣ በኮሚቴው የሚቋቋሙና ውክልና የሚሰጣቸው በፌዴራል፣ በክልሎች፣ በከተማና በወረዳ ደረጃ ያሉ ንዑሳን ኮሚቴዎችንም ያካትታል፤
 3. ‘‘ስብሰባ’’ ማለት ማንኛውንም ተግባር ለመፈጸም፣ ለመነጋገር፣ ለመወያየት ወይም መሰል ተግባራትን ለማከናወን የአንድ ቤተሰብ አባላት ከሆኑ ውጪ አራትና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ በአካል መገኘት ነው፤
 4. "ኳራንታይን" ማለት በኮቪድ-19 ተይዘዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ሰዎችን በቫይረሱ መያዝ አለመያዛቸው እስኪረጋገጥ ድረስ በተለየ ቦታ እንዲቆዩ ማድረግ ነው፤
 5. "ለይቶ ማቆየት" ማለት በኮቪድ-19 መያዙ የተረጋገጠ ሰው ቫይረሱን ወደ ሌሎች ሰዎች እንዳያስተላልፍ ከቫይረስ ነፃ እስኪሆን ድረስ ለብቻው ለይቶ እንዲቆይ ማድረግ ነው፤
 6. "ሀገር አቀፍ የህዝብ ትራንስፖርት" ማለት ከአንድ ክልል ከተማ ወደሌላ ክልል ከተማ የሚደረግ ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሆን በአንድ ክልል ውስጥ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ የሚደረግ የህዝብ ትራንስፖርትንም ያጠቃልላል፤
 7. "የከተማ ውስጥ የህዝብ ትራንስፖርት" ማለት በከተማ ውስጥ ትራንሰፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎችን፤ አውቶብሶችና የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አውቶብሶችን ያጠቃልላል፤
 8. "መጠጥ ቤት" ማለት በግልፅ የሆቴልነት ስያሜ ከተሰጠው ቤት ውጪ ያለ ማናቸውም አይነት የአልኮል መጠጥ የሚሸጥበት ቤት ነው፤
 9. "ለማህበራዊ አላማ" ማለት ሰርግ፣ለቅሶ፣ ክርስትና፣ልደት፣ እድር እና ለመሳሰሉት አላማ ማለት ነው
 10. "ፍትህ አካላት" ማለት፣ የክልልና ፌደራል ፖሊስና አቃቤ ህግ ተቋማትና ፍርድ ቤቶች ማለት ነው፣
 11. በአዋጁ ላይ የተሰጡ ሌሎች ትርጓሜዎች ለዚህ ደንብም ተፈፃሚ ይሆናሉ:: 

3. የተከለከሉ ተግባራት

 1. ለሀይማኖታዊ ወይም ማህበራዊ አላማ፣ ለመንግስታዊ ወይም ፖለቲካዊ ስራ ወይም ሌላ መሰል አላማ አምልኮ በሚደረግባቸው ቦታዎች፣ በመንግስት ተቋማት፣ በሆቴሎች፣ በማናቸውም የመሰብሰቢያ አዳራሾችና በማናቸውም ቦታ አራትና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ ላይ መገኘት  የተከለከለ ነው፤
 2. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 1 የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ አስገዳጅ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ወይም በኮሚቴው የሚቋቋሙና ውክልና የሚሰጣቸው በክልሎች፣ በከተማና በወረዳ ደረጃ ባሉ ንዑሳን ኮሚቴዎች ስብሰባ እንዲደረግ ሊፈቅድ ይችላል፡፡
 3. ማንኛውም ሰው ለሰላምታና ሌላ ማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ ክልክል ነው፣
 4. ማንኛውም ሀገር-አቋራጭ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ሰው በማንኛውም ጊዜ ከተሸከርካሪው ወንበር ብዛት 50% በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤
 5. ማናቸውም የከተማ ውስጥ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ታክሲ፣ አውቶቡስ፣ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አውቶቡስ ከተሸከርካሪው የወንበር ቁጥር 50% በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤
 6. ማንኛውም የግል ተሸከርካሪ ሾፌሩን ሳይጨምር ከተሸከርካሪው የወንበር ቁጥር 50%  በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤
 7. የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ከዚህ በፊት ሲጭን ከነበረው አቅሙ 25% በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው፤
 8. የኢትዮ-ጂቡቲ የምድር ባቡር ከወንበር ቁጥሩ 50% በላይ ሰዎችን ጭኖ መንቀሳቀስ ተከለከለ ነው፤
 9. ማንኛውንም ታራሚን ወይም ተጠርጣሪን በአካል በመገኘት በማረሚያ ቤት ወይም ፖሊስ ጣቢያ መጠየቅ ክልክል ነው፤ ሆኖም ይህ ድንጋጌ በፖሊስ ጣቢያ ለሚገኝ ተጠርጣሪ፣ ከተጠርጣሪው ጋር በአካል ሳይገናኙ  ስንቅ ማድረስን አይከለክልም፤ 
 10. በጭፈራ ቤቶችና በመጠጥ ቤቶች ማናቸውንም የመጠጥና መዝናኛ አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፤
 11. በማናቸውም ቦታ የሺሻ ማስጨስና ጫት ማስቃም አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፤
 12. የሲኒማ፣ ቲያትርና በአንድ ቦታ ብዙ ሰዎችን የሚያሰባስቡ መሰል የመዝናኛ አገልግሎቶችን መስጠት ክልክል ነው፣
 13. ሆቴሎች፣ ካፌዎች ወይም ምግብ ቤቶች አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ በአንድ ጠረጴዛ ላይ ከሶስት ሰው በላይ እንዲቀመጥ ማድረግ የተከለከለ ሲሆን ተገልጋዮች በሚቀመጡባቸው ጠረጴዛዎቹ መካከል ያለው ርቀትም ሁለት የአዋቂ እርምጃ መሆን አለበት፤ ሆኖም ተገልጋዮች የሚገለገሉት በጠረጴዛ ላይ ካልሆነ በመካከላቸው የሚኖረው ርቀት ሁለት የአዋቂ እርምጃ መሆን አለበት፤በድንበር አካባቢዎች በሚገኙ ኬላዎች በኩል ወደ ሀገር ውስጥ መግባትም ሆነ ወደ ውጪ መውጣት የተከለከለ ነው፣
 14. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 11 የተመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ በውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በኬላዎች በኩል ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ፈቃድ ሊሰጥ ይችላል፤
 15. ለዚሁ አላማ ከተቋቋመው ኮሚቴ ወይም በተመሳሳይ መልኩ በክልሎች ደረጃ በሚቋቋሙ ንዑስ ኮሚቴዎች ወይም ተመሳሳይ አደረጃጀቶች አማካኝነት ፈቃድ ከተሰጠው ሰው ውጪ በማንኛውም የክልልም ሆነ የፌዴራል መንግስት ባለስልጣን ወይም ባለሙያ ኮቪድ-19ኝን በተመለከተ የፌዴራል ወይም የክልል መንግስትን ወክሎ መግለጫ መስጠት የተከለከለ ነው፣
 16. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 11 የተመለከተው ክልከላ ቫይረሱን አስመልክቶ የወጡ ህጎችን በተመለከተ የሚደረግ የሙያ ትንተናን ወይም በህክምና ባለሙያዎች የሚደረጉ ማብራሪያዎችን ወይም በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየእለቱ የሚሰጡ መረጃዎችን አይመለከትም፤
 17. ማንኛውም የመኖሪያም ሆነ የንግድ ድርጅት ቤት አከራዮች በተከራዩ ስምምነት ካልሆነ በስተቀር ቤቱን እንዲለቅ ማድረግ ወይም የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ የተከለከለ ነው፤
 18. ማናቸውም በአዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት የሚተዳደሩ ሰራተኞችን የሚያስተዳደሩ የግል ድርጅቶች በስራቸው ያሉ ሰራተኞችን የስራ ውል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚያስቀምጠው ስርአት ውጪ ማቋረጥ የተከለከለ ነው፣
 19. ማንኛውም የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋም በትምህርት ቤት ወይም በሌላ ማናቸውም ቦታ አስተማሪና ተማሪዎች በአካል ተገናኝተው መማር ማስተማር ስራ እንዲሰራ ማድረግ ወይም ማስተማር የተከለከለ ነው፤
 20. ማንኛውም ሁለትና ከዚያ በላይ ሰው በመሆን የሚጫወቱባቸውን ጨዋታዎች፣ ማጫወትም ሆነ መጫወት የተከለከለ ነው፤
 21. ማናቸውንም የስፖርት ውድድሮች ወይም የቡድን ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የተከለከለ ነው፤
 22. የህፃናት ማጫዎቻ ቦታዎች አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው፣
 23. ማንኛውም ሰው የባንክ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች፣ በገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ በሱቆች፣ በመድሀኒት መሸጫ አካባቢዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች ከሁለት የአዋቂ እርምጃዎ በታች በሆነ ርቀት መቆምም ሆነ መቀመጥ የተከለከለ ነው፡፡
 24. መሰረታዊ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት እንደ መብራት ሀይል፣ ከውሃ አቅርቦት ጋር ግንኙነት ያለው ስራ የሚሰሩ ተቋማት ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የህክምና ተቋማት፣ ባንኮች፣ ከምግብ አቅርቦት ጋር ግንኙት ያለው ስራ የሚሰሩ ተቋማት፣ የጽዳት ስራዋችን የሚሰሩ ተቋማትና ባለሙያዎች፣ ከድንገተኛ ና የእሳት አደጋ መከላከል ጋር የተያያዙ ስራዎችን የሚሰሩ ተቋማት፣ ከጥበቃና ደህንነት ጋር የተያያዙ ድርጅቶች እና ተቋማት በማንኛውም መልኩ ስራን አለመስራተ ማቋረጥ ማስተጓጎል እና መሰል ተግባራትን መፈጸም የተከለከለ ነው፤
 25. የደረቅና የፈሳሽ ጭነት አገልግሎትን፣ የምርት ስራን፣ የእርሻ ስራን ወይም የግንባታ ስራን ማቋረጥ፣ ማሰተጓጎል ወይም አለመስራት የተከለከለ ነው፣
 26. ኮቪድ-19ኝና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ማህበረሰቡ እንዳይረጋጋ የሚያደርግና በማህበረሰቡ ላይ ስነ-ልቦናዊ ጫና የሚፈጥር ማናቸውንም መረጃ ማሰራጨት የተከለከለ ነው፡፡

 

4. የተጣሉ ግዴታዎች

 

 1. ማንኛውም ኮቪድ-19 እንዳለበት የተጠረጠረ ሰው ወይም ወደ ሀገር የሚገባ አለማቀፍ መንገደኛ ኳራንታይን የመደረግና የኮቪድ-19 ምርመራ የማድረግ ግዴታ አለበት፤
 2. ወደ ሀገር የገባ አለማቀፍ መንገደኛ ኳራንታይን በሚደረግበት ጊዜ የራሱን ወጪ የመሸፈን ሀላፊነት ያለበት ሲሆን፣ መንገደኛው የመክፈል አቅም የሌለው ከሆነ መንግስት ለዚሁ አላማ ባዘጋጀው ቦታ እንዲቆይ ይደረጋል፣
 3. በኮቪድ-19 መያዙ የተረጋገጠ ማንኛውም ሰው መንግስት በሚያዘጋጀው ለይቶ ማቆያ ክፍል የመቆየት ግዴታ አለበት፤
 4. በጉዞ ወቅት ኮቪድ-19 አለበት ተብሎ የሚጠረጠር መንገደኛ ሲኖር የማጓጓዣ አንቀሳቃሹ በአቅራቢያው ላለው ወይም ለሚያርፍበት የመግቢያና መውጫ ኬላ ሀላፊ ወይም የኮቪድ-19 ምርመራ ለሚያደርግ ቡድን የማሳወቅ ሀላፊነት አለበት፤
 5. የኮቪድ-19 ያለበት ወይም አለበት ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ሰለመኖሩ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ወይም ለፖሊስ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፣
 6. የባንክ አገልግሎት በሚሰጥባቸው አካባቢዎች፣ በገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ በትራንስፖርት ውስጥ፣ በሱቆች፣ በመድሀኒት መሸጫ አካባቢዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች የሚገኝ ማንኛውም ሰው አፍና አፍንጫው ላይ መሸፈኛ የማድረግ ግዴታ አለበት፤
 7. በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 6 የተመለከተው የአፍና አፍንጫ መሸፈን ግዴታ ለዚሁ አላማ ተብሎ በፋብሪካ በተሰራ፣ በቤት ውስጥ ከተለያዩ ጨርቃጨርቆች በተዘጋጀ ወይም በማናቸውም አይነት ልብሶች ሊፈጸም  ይችላል፡፡
 8. ማንኛውም አገልግሎት የመንግስትም ሆነ የግል አገልግሎት ሰጪ ተቋም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሶችን ማዘጋጀትና ተገልጋዮች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጋቸውን የማረጋገጥ ሀላፊነት አለበት
 9. ማናቸውም አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስትም ሆነ የግል ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ተቋማቱ የሚሄዱ ተገልጋዮች ሁለት የአዋቂ እርምጃ ተራርቀው የሚቆሙበትን ቦታ ምልክት የማድረግ ሀላፊነት አለባቸው፤
 10. የመንግስት የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችና የግል የሚዲያ ተቋማት ኮቪድ-19ኝና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚያስተላልፏቸው መረጃዎች፣ የዜና ትንተናዎች ወይም ፕሮግራሞች ሳይጋነኑ ወይም ሳይቃለሉ ተገቢው መረጃ ወደ ሕዝቡ የማድረስ እና አላግባብ የሆነ ድንጋጤና ሽብርን የማይፈጥሩ መሆን አለባቸው::
 11. ማንኛውም በፌዴራልም ሆነ በክልል የሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በተቋሙ ስር ለሚገኙ ሰራተኞች ስለቫይረሱ አስፈላጊውን መረጃ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የማድረስ፣ በመግቢያና መውጫ በሮችና ሌሎች አስፈላጊ ቦታዎች ላይ ቢያንስ እጅ ለመታጠብ የሚያስችል ውሃና ሳሙና ማዘጋጀት ፣ በተቻለ መጠን ሌሎች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፤
 12. ማንኛውም በፌዴራልም ሆነ በክልል የሚገኙ የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት በተቋሙ ስር የሚገኙ ሰራተኞች በአንድ ክፍል ውስጥ፣ በአንድ መስሪያ ቦታ ወይም በአንድ ትራንስፖርት ውስጥ ተጨናንቀውና አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ በማያስችል መልኩ እንዳይሰሩ ለማድረግ አስፈላጊውን ፈረቃ ማመቻቸት፤ ሰራተኞቹ ቤታቸው ሆነው የሚሰሩበትን ሁኔታ ወይም እረፍት በመውሰድ ስራ ቦታ እንዳይመጡ የማመቻቸት ሀላፊነት አለበት፤
 13. ማንኘውም የፌዴራልም ሆነ የክልል የመንግስት ተቋምና በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 መሰረት የሚተዳደሩ ሰራተኞችን የሚስተዳድር የግል ድርጅት ሰራተኞቹ ወደ ስራ ቦታ ለመሄድ ትራንስፖርት መጠቀም አስፈላጊ ከሆነ በስራ ላይ ለሚገኙ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት የማመቻቸት ሀላፊነት አለበት፤
 14. ፖሊስ ኮሚሽን ወይም ማረሚያ ቤት ተጠርጣሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር የሚገናኙበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሀላፊነት አለበት፤
 15. ማንኛውም የቤት፣ የሆቴል፣ የአፓርታማ፣ የተሽከርካሪ፣ የአዳራሽ ወይም የማንኛውም ንብረት ባለቤት መንግስት የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ለሚያደርገው ጥረት አስፈላጊ የሆነ ንብረቱን ለዚህ አላማ አገልግሎት ላይ እንዲውል በሚኒስትሮች ኮሚቴ ወይም ኮሚቴው ውክልና በሰጠው የመንግስት አካል ሲወሰንና ሲጠየቅ ንብረቱን ለእለት ከእለት ፍጆታው የሚጠቀምበት ካልሆነ በሰተቀር ውሳኔውን ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለበት፤
 16. ማንኛውም አምራች ወይም አገልግሎት ሰጪ ድርጅት፣ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ለሚያደርገው ጥረት አስፈላጊ የሆነ አግለግሎት እንዲሰጥ፣ አገልግሎቱን እንዲያሰፋ፣ ምርት እንዲያመርት፣ የሚያመርተውን ምርት መጠን እንዲጨምር፣ አዲስ ምርት አይነት እንዲያመርት ወይም ምርቱን መንግስት በሚወስነው ተመጣጣኝ ዋጋ ለመንግስት፣ ለሾማቾች ወይም ለህብረት ስራ ማህበራት እንዲሸጥ በሚኒስትሮች ኮሚቴ ወይም ኮሚቴው ውክልና በሰጠው የመንግስት አካል የሚሰጠውን ትዕዛዝ ተግባራዊ ማድረግ አለበት።
 17. ሆቴሎች ለደንበኞቻቸው አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ የእጅ መታጠቢያ ውሀና ሳሙና የማቅረብ ሀላፊነት ያለባቸው ሲሆን፣ የሆቴሉ ተጠቃሚዎችም እጃቸውን መታጠባቸውንና አስፈላጊውን ንፅህና አጠባበቅ ስርአት ተግባራዊ ማድረጋቸውን የማረጋገጥ እንዲሁም ደንበኞች ከተጠቀሙ በኋላ የተገለገሉባቸውን ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮችና ሌሎች እቃዎች የማከም ግዴታ አለባቸው
 18. ማንኛውም በስራ ላይ ያለ፣ ጡረታ የወጣ ወይም በትምህርት ላይ ያለ የጤና ወይም የሌላ ሙያ ባለቤት ወይም ማንኛውም ዜጋ የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት አስተዋፅዖ እንዲያደርግ በመንግስት ጥሪ ሲደረግለት የመተባበር ግዴታ አለበት፡፡

 

5. የሚኒስትሮች ኮሚቴ ስለመቋቋምና ስልጣና ተግባር

 

 1. የሚኒስትሮች ኮሚቴ ከዚህ በኋላ "ኮሚቴ" እየተባለ የሚጠራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰብሳቢነት የሚመራ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ ኮሚቴ በዚህ ደንብ ተቋቁሟል፤
 2. የኮሚቴው አባላት ስብጥር እና ብዛት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይወሰናል፤
 3. ኮሚቴው የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ይኖሩታል፣

ሀ. የኮቪድ-19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚሰራውን ስራ በበላይነት ይመራል ፣ ያስተባብራል፤

ለ. የቫይረሱን ስርጭት በተመለከተ አስፈላጊውን መረጃና ማስረጃ ይሰበስባል፣ ይተነትናል፤ በትንተናው ላይ ተመስርቶ አስፈላጊውን አቅጣጫ ይሰጣል፤

ሐ. በስሩ የተለያዩ ንዑሳን ኮሚቴዎችን በፌዴራል፣ በክልል፣ በከተማና ወረዳ ደረጃ ያቋቁማል፣ አስፈላጊውን መረጃ፣ ማስረጃና የስራ ስምሪት ይሰጣል፣ ሪፖርታቸውን ይገመግማል አቅጣጫ ያስቀምጣል፤

መ. በዚህ ደንብ ላይ የተደረጉ ክልከላዎችና የተጣሉ ግዴታዎች ቀሪ የሚሆኑበትን አግባብ እየገመገመና ችግሩ እየቀነሰ ከሄደ ክልከላዎቹና የተጣሉ ገደቦች ቀሪ እንዲሆኑ ይወስናል፣ በሚመለከተው ንዑሳን ኮሚቴ በኩል ለማህበረሰቡ እንዲደርስ ያደርጋል፤

ሠ. የቫይረሱ ስርጭት እየሰፋ እና እየጨመረ በመሄዱ ምክንያት ተጨማሪ ክልከላዎቸንና የሚጣሉ ግዴታዎችን በደንብ መደንገግ አስፈላጊ መሆኑን ባመነበት ጊዜ አስፈላጊው ደንብ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ትእዛዝ ይሰጣል፤ 

 1. የኮሚቴውን ስብሰባ እና ዝርዝር የአሰራር ስነ-ስርዐት በሚያወጣው መመሪያ ይወስናል፤
 2. ኮሚቴው ለክልሎችና ለከተማ መስተዳደሮች ለተመሳሳይ አደረጃጀቶች ስራቸውን በተመለከተ መመሪያና ውክልና ሊሰጥ ይችላል፡፡

 

6. ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች

 1. በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርአት ህጉና ሌሎች ስነ-ስርአታዊ ጉዳዮችን በሚደነግጉ የወንጀል ህጎች ላይ የተመለከቱ ድንጋጌዎችን እንደተጠበቁ ሆነው፣ የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ጸንቶ በሚቆይበት ጊዜ የፍትህ አካላት የጊዜ ቀጠሮና ፍርድ ቤት መቅረቢያ ጊዜን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን የማክበር ግዴታ ለባቸውም፣
 2. የክልልና ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጉዳዮችንና ከምርት መደበቅና ዋጋ መጨመር ጋር የተያያዙ የወንጀል ደርጊቶችን በተመለከተ በአፋጣኝ ውሳኔ የሚሰጡ ችሎቶችን የማዘጋጀት  ሀላፊነት አለባቸው፤
 3. በፌደራል እና በክልል ጠቅላይ ፍርድቤቶች ውሳኔ መሰረት የክልል እና የፌደራል ፍርድ ቤቶች የፍትሃ ብሄር ጉዳዮችን በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ማስተናገድ ሊያቆሙ ይችላሉ።
 4. በኮቪዲ-19 ምክንያት ህይወቱ ያለፈ ማንኛውም ሰው የቀብር ስርአቱ የሚፈጸመው በመንግስት አማካኝነት ለዚሁ አላማ በተለዩ ቦታዎች ሲሆን በቀብሩ ላይ የሚገኘውን የሰው ብዛትና የቀብሩ ዝርዝር አፈፃፀሙ  በመመሪያ ይወሰናል፣
 5. በዚህ አዋጅ አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ 4፣ 5 እና 6 ከተመለከቱት ተሸከርካሪዎች ውጪ ያሉትን በተመለከተ በሚወጣ መመሪያ ይወሰናል፣
 6. በዚህ ደንብ የተከለከሉ ተግባራትን የፈፀመ ወይም የተጣሉ ግዴታዎችን የተላለፈ ማንኛውም ሰው በአዋጁ ላይ የተመለከተው ቅጣት ተፈፃሚ ይሆንበታል፡፡

 

7. መመሪያ የማውጣት ስልጣን

የሚኒስትሮች ኮሚቴ  አዋጁን እና አዋጁን ተከትሎ የወጣውን ይህን  ደንብ ለማስፈፀም ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያ ያወጣል::

8. ደንቡ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ አዋጁ በስራ ላይ ባለበት ጊዜ ተፈፃሚ ይሆናል::

 

አዲስ አበባ

መጋቢት 2012 ዓ/ም

አብይ አህመድ/ዶ.ር/

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር