ከቤት ውጪ የሚደረግን ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍን በሚመለከትአግባብ ያላቸው ሥርዓቶች ሊደነገጉ ይችላሉተብሎ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 1 ቢደነገግም ሰላማዊ ሰልፍን በሚመለከት የወጣውና ሥራ ላይ ያለው ሕግ በሽግግር መንግሥት 1983 .ም የታወጀውየሰላማዊ ሰልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 3/1983” ነው፡፡

ይህ አዋጅ መሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግን አስመልክቶ ሕግ ማውጣት ያስፈለገበትን ምክንያት በመግቢያው በሚከተለው መልኩ ይደነግጋል፡፡

ሰላማዊ ሰልፍንና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባን በሚያካሄዱ ግለሰቦችና በሌሎች ግለሰቦች መካከል ሊነሣ የሚችል አምባጓሮን በመቆጣጠርና የሕዝብ ሰላምና ፀጥታ የሚያውክን ሁኔታ ማስወገድ፤

በዲሞክራሲያዊ መብቶች በመጠቀም በሚደረግ ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ሳቢያ በግለሰቦችና በንብረት ላይ ሊደርስ የሚችል ጉዳትና ጥፋትን መቆጣጠር፤

እነዚህንም መብቶች በሚገባ ተግባር ላይ እንዲውሉ የኀብረተሰቡን የዕድገት ደረጃና የኑሮ ሥርዓት በማገናዘብ የተመለከቱት ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሕዝብ እንዲጠቀምባቸው ማድረግ፤

ይህ አዋጅ የወጣው በአንድ በኩል ዜጎች የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙባቸው ማስቻል ሲሆን በሌላ በኩል ይህንን መብት ዜጎች በሚጠቀሙበት ጊዜ የሕዝብ ሰላምና ጸጥታ እንዳይታወክ ወይም በግለሰቦችና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስተዳደር እንደሆነ ለመረዳት ይቻላል፡፡

ሰላማዊ ሰልፍ፣ ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የማድረግ መብትዎ

በአዋጅ ቁጥር 3/1983 መሠረት ሰላማዊ ሰልፍ ማለት ብዙ ሕዝብ በአደባባይ፣ በመንግድ ወይም በሌላ ለሰላማዊ ሰልፍ ምቹ በሆነ ሥፍራ የጦር መሣሪያ ሳይዙና የኀብረተሰቡን ሰላም ሳያውኩ ሃሳባቸውን በንግግር በዘፈን መፈክርን በማሰማት፤ ጽሑፍን በማንገብ ወዘተ በሥርዓትና በይፋ የሚገልጹበት ሂደት ነው፤ በተመሳሳይ መልኩ ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ምን ማለት እንደሆነ አዋጁ ሲደነግግ ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ማለት ብዙ ሕዝብ በቤት፣ በግቢ፣ በአደባባይ ወይም በሌላ ለስብሰባ ምቹ በሆነ ሥፍራ የጦር መሣሪያ ሳይዙና የኀብረተሰቡን ሰላም ሳያውኩ፣ ካስፈለገ በድምፅ ማጉሊያ መሣሪያም ጭምር እየተጠቀሙ ፖለቲካዊና ፖለቲካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በይፋ ውይይት የሚያካሂዱበት ስብሰባ ነው፡፡

ከእነዚህ ሁለት ድንጋጌዎች ስንነሳ ሰላማዊ ሰልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ የማዘጋጀትና በነዚሁ የመሣተፍ መብት አለዎት፡፡ ያስተውሉ ይህንን መብትዎን መገልገል የሚችሉት፡-

  • መሣሪያሳይዙ እንደሆነ፤
  • የሚሳተፉበት ወይም የሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍ በሕዝብ እንቅስቃሴ ላይ ችግር የማይፈጥር ሲሆን፡፡
  • የሚሳተፉበት ወይም የሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍ የሌሎችን ሰዎች የመሰብሰብ መብት ወይም የሌሎችን ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ወይም የሕዝብ ሞራልን የሚጥስ ካልሆነ ነው፡፡

ስለማሳወቅ ግዴታ

አዋጅ ቁጥር 3/1983 በአንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 2 ሥር ሰላማዊሰልፍ ወይ ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ለማድረግ የሚፈልግ አካል የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ከሚካሄድበት ጊዜ ቢያንስ ከ48 ሰዓታት በፊት በጽሑፍ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

የማሳወቂያው ጽሑፍ ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ በከተማ ከሆነ የሚደረገው ለከተማው አስተዳደር ጽ/ቤት፤ ከከተማ ውጭ ከሆነ ለወረዳው አስተዳደር ጽ/ቤት መሆን እንዳለበትም በግልጽ ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም፡-

ማንኛውንም ዓይነት ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ከማድረግዎ በፊት በጽሑፍ በአቅራቢያዎ ለሚገኝ አስተዳደር ስለጉዳዩ በጽሑፍ ማሳወቅ እንዳለብዎ አይዘንጉ፡፡

በጽሑፍ ጉዳዩን ሲያሳውቁ የሚከተሉትን ስድስት ነጥቦች የያዘ መሆኑን ልብ ይበሉ!

  1. የሰላማዊ ሰልፉ ወይም የሕዝባዊ ፖለቲካ ስብሰባው ዓላማ፤
  2. ሰላማዊ ስልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው የሚደረግበት ቦታ፤ ሰላማዊ ስልፉ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር ከሆነም የሚተላለፍባቸው መንገዶችና አደባባዮች፤
  3. ሰላማዊ ስልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው የሚደረግበት ቀንና ሰዓት፤
  4. ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው የሚወሰደው ጊዜ ግምትና የተሳታፊው ሕዝብ ብዛትና ማንነት ግምት፤
  5. ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው በሚደረግበት ጊዜ ሰላምና ፀጥታን ለማስጠበቅ ከመንግሥት የሚፈለገው ዕርዳታ፤ እና
  6. የሰላማዊ ስልፉ ወይም የሕዝባዊ ፖለቲካ ስብሰባ አደራጅ ግለሰብ ወይም ቡድን ሙሉ ስም፣ አድራሻና ፊርማ፤ በድርጅት ስም የሚዘጋጅ ከሆነም የድርጅቱ የአመራር አካል ተወካዮች ሶስት ተጠሪዎች ስም$ አድራሻና ፊርማ፡፡

የአስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊነት

ከላይ በዚህ ጽሑፍ የሕጉን ዓላማ ባብራራንበት ክፍል አዋጁ ከወጣበት አንዱ ምክንያት ዜጎች የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን እንዲጠቀሙባቸው ማስቻል ነው ብለናል፡፡ ይህንን መሠረታዊ መብት ዜጎች አንዲጠቀሙበት ለማስቻል ደግሞ ኃላፊነት ከተጣለባቸው አካላት አንዱ በየአካባቢው ያሉ የአስተዳደር ጽ/ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት የሰላማዊና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ጥያቄ በጽሑፍ ሲቀርብላቸው ጥያቄውን በመቀበል የዜጎችን ጥያቄ በግልጽ ማስተናገድ እንዳለባቸው ሕጉ በግልጽ ደንግጓል፡፡

የሰላማዊና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ጥያቄው በደረሳቸው በ12 ሰዓት ውስጥ በጽሑፍ ለጠያቂው አካል የማሳወቅ ኃላፊነት ሕግ ጥሎባቸዋል፡፡ የአስተዳደር ጽ/ቤቶች የሰላማዊና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ጥያቄውን ሰላምን ከማስፈን ፀጥታን ከማስጠበቅና የሕዝቡን ዕለታዊ ኑሮ እንዳይሰናከል ከማድረግ አንፃር አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ በማየት፡-

  1. ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባውን የመፍቀድ፤ ወይም
  2. ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባውን በሌላ ጊዜ ወይም በሌላ ሥፍራ እንዲደረግ አስተያየት ከእነ ምክንያቱ ለጠያቂው አካል የማሳወቅ

ግዴታ አለባቸው፡፡

የአስተዳደር ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፉ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባው ምን ጊዜም በየትኛውም ቦታ ሊካሄድ አይችልም ብሎ ለላማዊ ሰልፉ ወይም ለሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ጥያቄው መልስ መስጠት አይችልም፤

የፀጥታ አስከባሪዎች ኃላፊነት

የግለሰቦችን መብት ለማስከበር፣ በግለሰቦች ላይ ሊደርስ የሚችል የአካልም ሆነ የንብረት ጉዳትና ጥፋት እንዲሁም በኀብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመጠበቅ የፀጥታ አሰከባሪዎች በማናቸውም ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ በመገኘት የሕዝብን መብት ሰላምና ደኀንነት የማስከበር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ያስተውሉ!

  1. ማናቸውም ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ቦታዎች 100 ሜትር ርቀት ውስጥ ሊደረግ አይችልም፤
  2. በኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሥራ ቦታና የመኖሪያ ቤት፤
  3. በቤተክርስቲያን በመስጊድና በመሳሰሉት የጸሎት ቤቶች እንዲሁም በሆስፒታልና በመካነ መቃብር ዙሪያ፤
  4. በኤሌክትሪክ፣ ማመንጫዎች በግድቦችና በመሳሰሉት አደጋ ሊያስከትሉ በሚችሉ ቦታዎች ዙሪያ፤ እና
  5. በገበያ ቀን ሰላማዊ ስልፎችን ወይንም የሕዝብ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ አስቸጋሪ በሚሆን የገበያ ቦታዎች፡፡
  6. ማናቸውም ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ በጦር ኃይሎች$ በጥበቃና የሕዝብን ሰላምና ደኀንነት በሚቆጣጠሩ የመንግሥት የሥራ ክፍሎች አካባቢ 5ዐዐ ሜትር ርቀት ውስጥ ሊደረግ አይችልም፡፡
  7. ማናቸውም ሰላማዊ ሰልፍ ወይም ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ፤ የዘር$ የቀለም$ የሃይማኖት$ የጾታና የመሳሰሉትን የእኩልነት መብቶችን በሚጻረር ልዩነቶች በማድረግ ላይ የተመሠረተ ዓላማን ወይም በብሔር፣ በብሔረሰብና በሕዝቦች በዘረኝነት ላይ የተመሠረተ የጥላቻ አሉባልታንና ዘረኛ ጥርጣሬን ለማራመድና ለማነሳሳት በሕጉ መሠረት አይፈቀድለትም፡፡