በዚህም መሠረት አከራይ ከሆኑ የሚያከራዩትን ሰው ማንነት ማለትም ስም፣ አደራሻ እንዲሁም መታወቂያ ወይም ፓስፖርት ወይም ማንኛውም ዓይነት ማንነትን የሚገልጽ ማስረጃ ኮፒ በማድረግ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ በመሔድ የማሳወቅ ግዴታ አለበዎት፡፡
በተለይ የቤት ኪራይ በመኖሪያ ቤትዎ እያከራዩ ከሆነና ያከራዩት ሰው ማንነት የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው ከሆነ የፓስፖርቱን ቅጂ የመያዝና ለፖሊስ የማቅረብ ግዴታ ያለበዎት መሆኑን ይኼው አዋጅ በአንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 2 ሥር ደንግጓል፡፡
ይህንን ግዴታ ያልተወጡ እንደሆነ ማለትም አከራይተው ስለአከራዩት ሰው ማንነት ለፖሊስ ያላሳወቁ እንደሆነ ከሦስት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እሥራት ሊያስቀጣዎት እንደሚችል የጸረ ሽብር ሕጉ አንቀጽ 35 ደንግጎት ይገኛል፡፡
እንዲህ ዓይነት የማከራየት ዕድል ሳይገጥምዎ ተከራይ የሆኑ እንደሆነ ወይም አከራይ ዘመድ፣ ጓደኛ፣ ቤተሰብ ያለዎት እንደሆነ ይህንን የሕጉን ግዴታ በማሳወቅ የድርሻዎን መወጣትዎን አይርሱ! ወይም አከራይዎት ስለማንነትዎ በጠየቀ ጊዜ ወይም መታወቂያዎትን ኮፒ እንዲያደርጉ ሲጠይቆዎት መተባበርን አይዘንጉ፡፡