• በስልክ 
 • በአካል ወደ ጸረ ሙስና ኮሚሽን መሥሪያ ቤት በመቅረብ፤
 • በኢሜይል፣ 
 • በፋክስና በፖስታ ቤት ሲሆኑ 
 • ከሥራ ሰዓት ውጪ ቀጠሮ በመያዝ በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥም ጥቆማውን ማቅረብ ይቻላል፡፡ 

 

ማንኛውንም መረጃ በሚሰጡበት ጊዜ ማንነትዎን የመግለጽ ግዴታ የለበዎትም፡፡ የጸረ ሙስና ኮሚሽንም ያለርሶ ፈቃድ ማንነትዎን የመግለጽ መብት የለውም፡፡ ጥቆማዎትን በአካል ለማቅረብ ከወሰኑ ለገሃር ናዝሬት አውቶቡስ ተራ ፊት ለፊት በሚገኘው የኮሚሽኑ ቅፅር ግቢ ቢሮ ቁጥር 214 ድረስ በመሄድ ጥቆማዎትን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ጥቆማውን መስጠት የፈለጉት በፋክስ ወይም በኢሜይል ከሆነ፡-

 

 • የፋክስ ቁጥር 251-115-536991
 • የኢሜይል አድራሻ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በመጠቀም መላክ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም የፖስታ ሳጥን ቁጥር 34798/99ን በመጠቀም መላክ ይቻላል፡፡
 • ነፃ የጥቆማ ስልክ መስመር 988ን በመጠቀም ጥቆማ ማቅረብ የሚቻል ሲሆን በተጨማሪም 251-115-52 77 81/74 (ቀጥታ) ወይም 251-115-52 91 00 የውስጥ ቁጥር 232 የስልክ መስመሮችን በመጠቀም ጥቆማዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ 


የኮሚሽኑ መርማሪዎች ጥቆማዎቹን ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ከተቀበሉ በኋላ የቀረቡት ጥቆማዎች እውነትም የሙስና ወንጀሎች ስለመሆናቸውና በኮሚሽኑ የስልጣን ክልል የሚወድቁ ስለመሆናቸው የማጣራት ስራ ያከናውናሉ፡፡ የሙስና ወንጀሎች መሆናቸው ከተረጋገጠና በኮሚሽኑ የስልጣን ክልል የሚወድቁ ከሆኑ እንዲሁም ምርመራውን ለመቀጠል የሚያስችሉ ሌሎች ሁኔታዎችን ካሟሉ ቀጣይ ምርመራ ይካሔድባቸዋል፡፡ ከዚያም በበቂ ማስረጃዎች በተደገፉትና ምርመራቸው በተጠናቀቁ ጉዳዮች ላይ ክስ ይመሰረታል፡፡ ከኮሚሽኑ የስልጣን ክልል ውጭ የሆኑት ደግሞ ለሚመለከታቸው የፍትህ አካላት ይላካሉ፡፡ ጠቋሚዎች ያቀረቧቸው ጥቆማዎች ያሉበትን ደረጃና እጣ ፋንታቸውን በተመለከተ ኮሚሽኑን ጠይቀው ምላሽ ማግኘት ይችላሉ፡፡


ጠቋሚ ማን ነው?


ማንኛውንም የሙስና ድርጊት፣ ከባድ የሥነምግባር መጣስንና ብልሹ አሠራርን የተመለከተ መረጃ የሚሰጥ ሰው ወይም ድርጅት ማለት ነው፡፡ 


ጠቋሚው የሚጠቁመው ምንድን ነው?


ጠቋሚው የሚጠቁመው ማንኛውንም የተፈፀመ ወይም ሊፈፀም የታቀደ ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ነው፡፡

የፌደራል የሥነምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጥቆማ የሚቀበለው በየትኞቹ ተቋማት ውስጥ ስለተፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ወይም ብልሹ አሠራሮች ነው?

 

 • የፌደራል መንግሥት በጀት በሚመደብላቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የፌደራል መንግሥቱ ሥራዎች በሚከናወኑባቸው መሥሪያ ቤቶች፣ 
 • ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የፌደራል መንግሥት ባለአክስዮን በሆነባቸው የልማት ድርጅቶች፣ 
 • የፌደራል መንግሥት ለክልሎች በሚያደርገው ድጐማ ላይ ሙስና ከተፈፀመ፣ 
 • የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች የተካፈሉበት ከሆነ በግሉ ዘርፍም የሚፈፀመውን ሙስና አስመልክቶ ጥቆማ ማቅረብ ይቻላል፡፡ 
 • ከላይ የተጠቀሱት ቢኖሩም ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ከግንቦት 16/1993 ዓ.ም በፊት በምርመራና በፍርድ ቤት ሒደት ላይ የነበሩ ጉዳዮችን አይመለከትም፡፡

ጥቆማ እንዴት ይቀርባል?


ለኮሚሽናችን ጥቆማ ለማቅረብ የሚፈልጉ ጥቆማ አቅራቢዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን መረጃ በተቻለ መጠን እንደሚከተለው አደራጅተው ቢያቀርቡ አሠራራችንን ቀና ያደርግልናል፡፡ 

 • የራሳቸውን ስምና አድራሻ (መግለጽ የሚፈልጉ ከሆነ ብቻ)፣ 
 • የተፈጸመው የሙስና ወንጀል ምን እንደሆነ፣ 
 • ወንጀሉን ፈጸመ የተባለው ተጠርጣሪ ማንነት (ስም፣ ሙያ ወይም ስራ፣ አድራሻ፣ እድሜ እና የመንግስት ሰራተኛ ከሆነ የስራ መደቡን) 
 • ወንጀሉ የተፈፀመበት መስሪያ ቤት ወይም ድርጅት፣ 
 • ወንጀሉ የተፈፀመበት ቦታና ጊዜ፣ 
 • በወንጀሉ የተጠቀሙ ሰዎች ወይም የተጎዱ ሰዎች፣ 
 • በገንዘብ ሊገመት የሚችል ከሆነ በወንጀሉ የተገኘ ጥቅም መጠን ወይም የደረሰ ጉዳት ግምት፣ ወይም ከወንጀሉ መፈጸም ጋር በተያያዘ የተደረገ ውል፣ ብድር፣ ቀረጥ፣ ወዘተ... ገንዘብ መጠን፣ 
 • የሚታወቅ ከሆነ የተገኘው ጥቅም የሚገኝበት ቦታና ሁኔታ፣ 
 • የሚታወቅ ከሆነ በተጠርጣሪው ስም ያለው ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት፣ 
 • የጉዳዩን እውነትነት ሊያስረዱ የሚችሉ የሰነድ ማስረጃዎች የሚገኙበት ቦታ ወይም ጉዳዩን የሚያውቁ ሰዎች ወይም ምስክሮች ስምና አድራሻቸውን እንዲሁም፣ 
 • ጉዳዩን በተመለከተ ተጀምሮ ያለ ምርመራ መኖር ያለመኖሩን ወይም በጉዳዩ ላይ ለፍርድ ቤት ቀርቦ ክርክር እየተደረገበት ወይም ውሳኔ የተሰጠበት መሆኑን ለኮሚሽኑ የጥቆማ ክፍል በዝርዝር ቢቀርብ የምርመራውን ሥራ ቀልጣፋና ውጤታማ ያደርገዋል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪም ጠቋሚዎች የሰጡትን መረጃ (ጥቆማ) በራሳቸው እጅ ጽፈው እንዲፈርሙ ይህ ካልሆነ ደግሞ ለኮሚሽኑ ባለሙያ በቃል የሰጡት ዝርዝር መረጃ ተነቦላቸውና ትክክለኛነቱን አረጋግጠው ፊርማቸውን እንዲያስቀምጡበት ኮሚሽኑ ትብብራቸውን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ሌላ በተቻለ መጠን ጥቆማ አቅራቢዎች የሚሰጡትን መረጃ በጥቆማ ተቀባዩ ፊት በራሳቸው እጅ ጽሁፍ ጽፈው ቢፈርሙ ለኮሚሽኑ አሠራር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ሆኖም ግን ጠቋሚዎች መረጃቸውን በጽሁፍ ለማቅረብ ካልተስማሙ ወይም በፅሁፍ ለማቅረብ የማይችሉ ከሆነ ጥቆማቸውን ለኮሚሽናችን ባለሙያ በዝርዝር ካቀረቡ በኋላ ቢቻል ያቀረቡት መረጃ ተነቦላቸውና ትክክለኛነቱን አረጋግጠው እንዲፈርሙበት ይጠየቃሉ፡፡