ኩነቶቹ በአንድ አገር ዜጎች የሰብዓዊ መብትና የፍትሕ አስተዳደር አልፎም የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አገልግሎት አሰጣጥ ካላቸው ቁልፍ ሚና በመነሳት ኩነቶቹ ሲከሰቱ ማለትም አንድ ሰው ሲወለድ፣ ሲያገባ፣ ሲፋታ ወይም ሲሞት የሚመዘገብበት፣ የሚደራጅበት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውልበት የአመዘጋገብና የመረጃ አጠነቃቀር ሥርዓት የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በመባል ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያም እነዚህ ክስተቶች ማለትም ልደት፣ ጋብቻ ፍቺና ሞት፡-

  • ኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግስትና በሌሎች ሕጎች እውቅና የተሰጣቸውን የግለሰቦች መሠረታዊና ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ወሣኝ የመረጃ ምንጭ በመሆናቸው፣
  • በአገሪቱ ፍትሕ አስተዳደር የግለሰብና የቤተሰብ ጉዳይ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ ወሳኝ ክስተቶች መሆናቸው፣
  • ከሥነ-ህዝብ ለውጥ ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያላቸውን የሕዝብ ብዛትና እድገት ስለሚያሳዩ፣
  • በእነዚህም ላይ ተመሥርቶ ለኅብረተሰቡ ጥቅም ለሚከናወኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እቅዶችና አስተዳደራዊ አገልግሎቶች ዝግጅት የመረጃ መሠረት በመሆናቸው ወሳኝ ተብለው ተለይተዋል፡፡
    • የተፈፃሚነት ወሰን ሀገር-አቀፍ እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች ከወሣኝ ኩነት የሚገኙ መረጃዎች አገራዊ ይዘት ያለው ግለሰባዊ የማንነት ህጋዊ መረጃ ለማደራጀት አስፈላጊ መሆናቸው፣
    • በወሣኝ ኩነቶች ምዝገባ የሚሰበሰቡና በምሥክር ወረቀት የሚዘጋጁ መረጃዎች ዓይነትና መጠን በአገር ደረጃ ትንሹን ስታንዳርድ /Minimum Standard/ ማስቀመጥ የግድ የሚሉ መሆናቸው፣
    • በየክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ አልፎም በአለም አቀፍ ደረጃ ተነፃፃሪ የወሣኝ ኩነቶች ስታቲስቲክስ መረጃ ማደራጀት የግድ ማለቱና በአጠቃላይ የወሣኝ ኩነቶች ምዝገባ ከክልላዊ ይዘቱ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘቱ የሰፋ በመሆኑና አንድ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ ለመፍጠር የጎላ ጠቀሜታ ያሉት በመሆኑ አዋጁ በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈፃሚነት እንዲኖረው ተደርጓል፡፡

ልደትና ሞት በሰው ልጅ ላይ አንድ ጊዜ የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች ናቸው፡፡ ሰዎች በልደት አማካይነት ወደ ዓለም ኅብረተሰብ ይቀላቀላሉ፤ በአንጻሩ በሞት አማካይነት ከዓለም ይለያሉ፡፡ በመሆኑም ልደትና ሞት በሰው ልጅ አፈጣጠርና አኗኗር የሕይወት መነሻና መድረሻ እርከኖች መለያ ናቸው፡፡

ስለሆነም ልደት በዚች ምድር የሰዎች የመኖር ሕጋዊ መብት ምንጭ ኩነት በመሆኑ ማንኛውም ሰው በአንድ በታወቀ የአስተዳደር ክልል (አገር) ለመኖር ሕጋዊ የዜግነትና ማንነት መብት የሚያገኝበትና ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነውን ሕጋዊ ሰነድ በመንግስት የሚዘጋጅበት የህይወቱ የመብት መነሻ እርከን ሲሆን በአንጻሩ ሞት የዚህ መብት መጨረሻ እርከን ነው፡፡

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፍትሐብሔር ሕግ ስለሰው፣ ስለሰው መብትና አሰጣጥ በደነገገበት የሕጉ የመጀመሪያው አንቀጽ (አንቀጽ 1፣ ምዕራፍ 1፣ ክፍል 1፣ ቁጥር 1) “ሰው ከተወለደበት ቀን አንስቶ እስከ ሞተበት ቀን ድረስ የሕግ መብት አለው” በማለት ደንግጓል፡፡ በሌላም በኩል ጋብቻና ፍቺ ሰው “ህጋዊ ሰው” የመሆን መብት በሚያገኝበትና በሚያጣበት የማኅበረሰባዊ አኗኗር ሥርዐት ውስጥ የሚከሰቱ ዋነኛ የሰዎች ማኅበረሰባዊና ሕጋዊ አቋም ለውጥ ጠቋሚ ወሳኝ ኩነቶች ናቸው፡፡ እነዚህ በግለሰቦች ላይ የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊና ማኅበረሰባዊ ለውጦች የአንድን አገር አልፎም የአስተዳደር ክፍል የህዝብ አስተዳደር በሥርዐት ለመመምራት መነሻ መሰረቶች ናቸው፡፡

ልደትና ሞት የህዝብ ብዛትና እድገትን በቀጥታ ከሚያሳዩ ክስተቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ይኼውም የህዝቡ ቁጥር መጨመር፣ መቀነስ ወይም ባለበት መቆየቱ የሚታወቀው በአንድ ሀገር በሚከሰተው የልደትና ሞት ኩነት ብዛት ነው፡፡ በተመሣሣይ መልኩ ጋብቻና ፍቺም የአንድ ሀገር ህዝብ ብዛትና እድገት መጨመርን ወይም መቀነስን በተዘዋዋሪ ከሚወስኑ ሁኔታዎች አንዱ ነው፡፡

ጋብቻ የአንድ ኅብረተሰብ መሠረት እንደመሆኑ መጠን ምንም እንኳን ከጋብቻ ውጪ የሚከሰት የልደት ኩነት ቢኖርም በአብዛኛው የልደት ኩነት የሚከሰተው ኅብረተሰቡ ከሚመሠርታቸው ጋብቻዎች ናቸው፡፡ በአንፃሩ የፍቺ ኩነቶችን የፍቺ ኩነቶች በተከሰቱ ቁጥር የሚከሰቱ የልደት ኩነቶችም በዚያው መጠን ይቀንሳሉ፡፡ በተመሣሣይ መልኩ የልደትና የሞት ኩነቶች ክስተት በቀነሰ ቁጥር የህዝብ ቁጥር እድገትም በዚያው መጠን ይቀንሳል፡፡

በአለማችን የተለያዩ አገራት ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ አሰራሮችን አልፎም ከላይ የተመለከቱትን መሰረታዊ አገልግሎቶች ባገናዘበ መልኩ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን በህግ ድጋፍ ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት የማከናወኑን ስራ ከጀመሩ ረጅም ዕድሜን አስቆጥረዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም የወሳኝ ኩነቶች መመዝገብ መብት መሆኑና መንግስታትም ይህን መብት ለማስፈጸም አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወስዱ የሚጠይቁ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ፀድቀዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ውስጥ በአገሪቱ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባን ለመዘርጋት ተብለው በርካታ አንቀጾች እንዲካተቱ ያደረገች ቢሆንም የዚህ ህግ የህዝብ የክብር መዝገብ የሚመለከቱት አንቀጾች በዚሁ ህግ በቁጥር 3361(1) እነዚህን ድንጋጌዎች ለማስፈጸም የተለየ ደንብ እስከሚወጣ እንዳይተገበር አግዷቸዋል፡፡ በመሆኑም ላለፉት 48 ዓመታት ምዝገባን የሚመለከቱት አንቀጾች ስራ ላይ ሳይውሉ በመቅረታቸው በህጉ የተመለከቱት አደረጃጀቶችም ሆኑ የምዝገባ አፈጻጸም ሥርዓቱ በስፋት ሳይተገበር ቆይተዋል፡፡

ይህ በመሆኑ ምክንያት አዋጅ ቁጥር 760/2004 የወሳኝ ኩነት ምዝገባና የብሔራዊ መታወቂያ አዋጅ በ2004 ዓ.ም ወጥቷል፡፡

ይህ አዋጅ በመላ ሀገሪቱ ባሉ አካባቢዎች ወይም በማንኛውም ኢትዮጵያዊ ላይ ተፈፃሚ የሚሆን ሲሆን፡

በአዋጁ የወሳኝ ኩነት መረጃዎች የሚመዘገቡት መዝገብ የክብር መዝገብ ተብሎ የተተረጎመ ሲሆን አዘጋጃጀቱ በቋሚነት ለማገልገል በሚችል፣ ለአያያዝ በሚያመች በጥራዝ መልክ ሆኖ ለእያንዳንዱ የወሳኝ ኩነት ዓይነት የተለየ  የክብር መዝገብ እንደሚኖረው ተደንግጓል፡፡

በአዋጁ ማንኛውም ወሣኝ ኩነት መመዝገብ እንዳለበትና ኩነቱም አንድ ጊዜ ብቻ መመዝገብ እንዳለበት በግልጽ ተመልክቷል፤ ይህ ማለት ከተጋቡ፣ ወይም ከተፋቱ ወይም ልጅ ከወለዱ ኩነቱን የማስመዝገብ ኃላፊነት አለበዎት ማለት ነው፡፡ ወሣኝ ኩነት ሲከሰት እንዲያስመዘግብ ኃላፊነት ወይም ግዴታ የተጣለበት አስመዝጋቢ በአቅራቢያ በሚገኝ የምዝገባ ጽ/ቤት በመገኘት ኩነቱን የማስመዝገብ ግዴታን አለመወጣት ለልዩ ልዩ ኃላፊነቶች ያጋልጠዎታል ማለት ነው፡፡

የወሣኝ ኩነቶች ምዝገባ ሁሉን አቀፍ፣ ቀጣይ፣ ቋሚና አስገዳጅ መሆኑ የምዝገባው ልዩ ባህሪይ መሆን ስለሚገባው ህብረተሰቡና የማስመዝገብ ኃላፊነት የተጣለባቸው ሌሎች አካላት ምዝገባውን እንዲያከናውኑ የምዝገባው የጊዜ ገደብ ተመልክቷል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያን ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት ሊያዘገይ የሚችል በቂ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ማንኛውም ወሣኝ ኩነት ከልደት በስተቀር ከተከሰተበት ወይም ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ በ30 ቀናት ውስጥ መመዝገብ እንዳለበት በአዋጁ ተመልክቷል፡፡ ማንኛወም ልደት በ90 ቀናት ውስጥ መመዝገብ አለበት፡፡