የአሠሪ ግዴታዎች

አሠሪ የሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፡፡

  • ሥራ የመስጠትና ውሉ በሌላ ሁኔታ ካልገለጸ በስተቀር መሣሪያና ጥሬ ዕቃ የማቅረብ ግዴታ
  • ደሞዝና ሌሎች ክፍያዎችን የመፈጸም ግዴታ
  • የሰራተኛውን ሰብአዊ ክብር፣ ከስራ ጋር የተያያዘ ጤንነትና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ
  • ሕጉ በሚያዘው መሰረት የተለያዩ ሁኔታዎችን በመዝገብ የመያዝ እና አግባብ ባለው አካል ሲጠየቅ መዝገብ የማቅረብ ግዴታ
  • የስራ ዓይነቱን ዘመንና ሲከፈለው የነበረውን ደሞዝ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ለሰራተኛው የመስጠት ግዴታ እና
  • በሕጎችና በሥራ ውል ደንቦች እና መመሪያዎችን እንዲሁም ትዕዛዞችን የማክበር ግዴታዎች አሉበት፡፡

የሠራተኛ ግዴታዎች

ሠራተኛየሚከተሉት ግዴታዎች አሉበት፡፡

  • ሥራውን እራሱ የመስራት (በሌላ ሰው ማሠራት የተከለከለ ነው)፣ በአካልና በአዕምሮ ሁኔታ በስራ ቦታ ብቁ ሆኖ መገኘትና ትዕዛዝን የመፈጸም፡፡ አሠሪው የሚሰጣቸው ትዕዛዛት ግን ሁልጊዜም በስራ ውሉና በስራ ደንቡ መሠረት የተሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉ ትዕዛዛትን ሠራተኛው የመፈጸም ግዴታ የለበትም፡፡
  • መሣሪያዎችና ዕቃዎችን ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ
  • የንብረትና የህይወት አደጋ እንዳይደርስ ወይም አስጊ ሁኔታ ሲፈጠር ተገቢውን ዕርዳታ የመስጠትና እነዚህ እና የድርጅቱን ጥቅም የሚነኩ ሌሎች ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወዲያውኑ ለአሠሪው የማስታወቅና
  • በሕጎችና በሥራ ውል ደንቦች እና መመሪያዎችን እንዲሁም ትዕዛዞችን  የማክበር ግዴታዎች ናቸው፡፡

እነዚህን ግዴታዎች አለመወጣት እንደሁኔታው ከስራ እስከማባረር የሚያደርስ ውጤት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል አንድ ሰራተኛ የአሰሪውን ንብረት ከአደጋ መከላከል የሚገባው ሆኖ ሳለ በተቃራኒው በአሰሪው ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ወይም በከባደ ቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ ያለማስጠንቀቅያ ከስራ የሚያስባርር ድርጊት ነው፡፡