08 July 2015 Written by  ጥላሁን ካሳ

ክስ ከተመሠረተባቸው የዞን 9 ጦማሪያን መካከል የ5ቱ ክስ ተቋረጠ

ድረ ገፅ ተጠቅመው የተለያዩ ፅሁፎችን በማውጣት ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል ከተከሰሱት አስር ግለሰቦች መካከል አምስቱ ክሳቸው ተነስቶ ዛሬ ማምሻውን ከእስር ተፈቱ።

ክሱ ሊነሳ የቻለው የፍትህ ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን ትናንት ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደብዳቤ መፃፉን ተከትሎ ነው።

በዚህም መሰረት ክሳቸው የተነሳላቸው ኤዶም ካሳዬ፣ ዘላለም ክብረት፣ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ፣ ተስፋለም ወልደየስ አራጌ እና ማህሌት ፋንታሁን ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የፌደራል ተቋማትን ስልጣን እና ተግባር ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 691/2003 አንቀፅ 16 መሰረት በማናቸውም ሰዓት የተጀመረ ምርመራ እና ክስ የማቋረጥ እና የማንሳት ስልጣን እንዳለው ይታወቃል።

በዚህ መዝገብ አቃቤ ህግ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ የወንጀል ችሎት ምስክሮችን ማሰማቱን ተከትሎ ችሎቱ ብይን ለመስጠት ለሀምሌ 13 ቀን 2007 መቅጠሩ ይታወቃል።

የቀሪ አምስቱ ሶልያና ሽመልስ፣ አቤል ዋበላ ሱጌቦ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ በፍቃዱ ሃይሉ እና አጥናፉ ብርሃኔ ጉዳይ መታየቱ እንደሚቀጥል ከፍርድ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Last modified on Friday, 16 October 2015 16:15