Print this page
17 December 2014 Written by  EthiopianReporter

ታዳጊዋን በቡድን በመድፈር ለሞት ዳርገዋታል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ ተመሠረተ

ሃና ላላንጎ የተባለች የ16 ዓመት ታዳጊ ተማሪ በቡድን በመፈራረቅ አስገድደው በመድፈር ለሞት ዳርገዋታል በሚል በተጠረጠሩ አምስት ግለሰቦች ላይ፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ታኅሳስ 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ መሠረተ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሳምሶን ስለሺ፣ በዛብህ ገብረ ማርያም፣ በቃሉ ገብረ መድኅን፣ ኤፍሬም አየለና ተመስገን ፀጋዬ የተባሉ የታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች ሲሆኑ፣ ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የመሠረተባቸው፣ ‹‹ዕድሜያቸው 13 ዓመት በሆነና 18 ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ድፍረት በደልና ከባድ የሰው መግደል ወንጀሎች›› የሚሉ ሁለት ክሶች ናቸው፡፡

የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተጠርጣሪዎቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለማድረግ አስበው፣ መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡00 ሰዓት፣ ሟች ተማሪ ሃና ላላንጎን በታክሲ አሳፍረው ቀራኒዮ አደባባይ አካባቢ ወስደዋታል፡፡ የ16 ዓመቷን ታዳጊ የወሰዷት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ጦር ኃይሎች ከሚባለው አካባቢ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ሟቿን ቀራኒዮ አደባባይ ከወሰዷት በኋላ እስከ ምሽቱ 2፡30 ሰዓት ድረስ ሳምሶን ስለሺ ከተባለው አንደኛ ተጠርጣሪ ጋር አምሽተው፣ ለሁለተኛ ተከሳሽ ስልክ በመደወል መጥቶ እንዲወስዳትና እሱም ተመልሶ እንደሚያገኛቸው ተነጋግረው፣ በዛብህ ገብረ መድኅን የተባለው ተጠርጣሪ ወደሚኖርበት ቤት እንደወሰዳት ክሱ ያስረዳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ‹‹አንችን አሉ›› በመባል በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ሁለተኛና ሦስተኛ ተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት ወስደዋት፣ በግምት ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ሙሉ ሌሊት እየተፈራረቁ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጽሙባት እንዳደሩ ክሱ ያብራራል፡፡ በተፈጸመባት የቡድን የግብረ ሥጋ ግንኙነት ምክንያት በማህፀኗና በፊንጢጣዋ ደም ይፈሳት እንደነበር ክሱ ያክላል፡፡

ሟች ሃና ድርጊቱ ሲፈጸምባት የድረሱልኝ ጩኸት ስታሰማ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ ይገልጻል፡፡ ሟች እየደማች ተጠርጣሪዎች ድርጊቱን እየተፈራረቁ መፈጸማቸው ጨካኝነታቸውን፣ ነውረኛነታቸውንና አደገኛነታቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አካቷል፡፡

ሟች ሃና ሕክምና እንዳታገኝ በሁለተኛና በሦስተኛ ተጠርጣሪዎች ቤት ለአምስት ቀናት እንድትቆይ ማድረጋቸውንና በሦስተኛ ተከሳሽ አማካይነት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው ጦር ኃይሎች ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ወስደው እንደጣሏት ክሱ ይጠቁማል፡፡ በመሆኑም ተጠርጣሪዎቹ በፈጸሙት ከባድ የሰው መግደል ወንጀልና የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስረድቷል፡፡