Print this page
28 October 2014 Written by  EthiopianReporter

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀረበ

‹‹የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅን ይቃረናል›› የፓርላማ አባላት

ለሥነ ጹሑፍ፣ ለኪነ ጥበብና ለሳይንሳዊ የፈጠራ ሥራዎች ጥበቃ የሚያደርገውን አዋጅ ቁጥር 410/96 የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ሐሙስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡

ረቂቅ አዋጁ ባለ አምስት ገጽ ማሻሻያ አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡ በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ጥበቃ የሚያደርግለትን የታተመ ሥራ አንድ ኮፒ ለግል ዓላማ ማባዛት እንደሚቻል ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ የባለመብቱን ጥቅም ያከበረ ድንጋጌ ባለመሆኑ፣ ‹‹ጥበቃ የሚደረግለት ሥራ ለግል ፍጆታ አንድ ቅጅ ለማባዛት በቅድሚያ የቅጂው ኦርጅናል ሥራ ሊኖር ይገባል፤›› ሲል ማሻሻያ አስገብቷል፡፡ በመሆኑም ይህ ማሻሻያ እንዲህ ሆኖ የሚፀድቅ ከሆነ፣ ጥበቃ የሚደረግለትን የታተመ ሥራ የቅጂ ቅጂ ማድረግ አይቻልም ማለት ነው፡፡

በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ለንግድ ዓላማ የታተመ የድምፅ ቅጂ ወይም በቀጥታ ብሮድካስቲንግ ወይም በሌላ መንገድ ለሕዝብ ከቀረበ ተጠቃሚው ለከዋኙ፣ ለድምፁ ሪከርዲንግ ፕሮውዲሰር ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ አንድ ጊዜ እንደሚከፍል ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን የፈጠራ ባለመብቶችን ጥቅም ለማስከበር ተጠቃሚው እንዴትና የት እንደሚከፍል የሚደነግግ አሠራር ባለመዘርጋቱ፣ በሕግ የተፈቀደው ጥቅም ሳይከበር እንደቆየ የረቂቅ አዋጁ ማብራርያ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ከላይ የተጠቀሰውን ጥቅም የማግኘት መብት የሚሰጠው የድምፅ ሪከርዶች ለሆኑ ብቻ መሆኑ ተገቢ ባለመሆኑ፣ ሁሉም ጥበቃ የሚደረግላቸው ሥራዎች ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ ከዋሉ ተጠቃሚው ክፍያ እንዲከፍል በማሻሻያ ረቂቁ ተካቷል፡፡

በመሆኑም ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ ጥበቃ የሚደረግለትን የፈጠራ ሥራ ጥቅም ላይ የሚያውሉ እንደ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ ካፌዎች፣ የምሽት ጭፈራ ቤቶችና የመሳሰሉት የሮያሊቲ ክፍያ እንዲከፍሉ በማሻሻያ አዋጁ ላይ ተቀምጧል፡፡

ይኼንን ክፍያ በመሰብሰብና ለባለመብቶች የማከፋፈል ሥራ እንዲያከናውን ኃላፊነቱን ለጋራ አስተዳደር ማኅበር፣ ማለትም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ባለቤቶች መብቶቻቸውን በጋራ ለማስተዳዳር ለሚያቋቋሙት ማኅበር ሰጥቷል፡፡

ጥበቃ የሚያገኙ ሥራዎች ባለመብቶች መብቶቻቸውን በጋራ ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን የጋራ አስተዳደር ማኅበር በአዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዕውቅና ሊመሠርቱ እንደሚችሉ የሚገልጽ ድንጋጌ በማሻሻያው እንደ አዲስ ተካቷል፡፡

የማሻሻያ አዋጁ በፓርላማው ለውይይት ክፍት በሆነበት ወቅት የምክር ቤቱ የውጭና የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተስፋዬ ዳባ፣ የጋራ አስተዳደር ማኅበር ሊመሠረት የሚገባው በበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ መሠረት ካልሆነ እንደሚጣረስ አስረድተዋል፡፡

‹‹በአዕምሮአዊ ንብረት ጽሕፈት ቤት ዕውቅና ቢመሠረት ሕጋዊ ሰውነት ማግኘት አያስችለውም፡፡ ምክንያቱም ማኅበራት የሚመሠረቱት በበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጅ መሠረት ነው፡፡ በመሆኑም ማሻሻያውን በዝርዝር የሚመለከተው ኮሚቴ ይኼንን የሕግ መጣረስ ማጣራት አለበት፤›› ሲሉ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ጥበቃ የሚያገኙ መብቶችን ሆን ብሎ የጣሰ ማንም ሰው ከአምስት እስከ አሥር ዓመት፣ እንዲሁም በቸልተኝነት የጣሰ ከአንድ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት እንደሚጣልበት በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ይደነግጋል፡፡ ይሁን እንጂ ማሻሻያ አዋጁ የእስራት ቅጣት ብቻ ጥሰቶችን አያስወግድም በሚል ምክንያት ጥበቃ የሚደረግለትን መብት ሆን ብሎ የጣሰ ከ25,000 ብር እስከ 50,000 ብር፣ በቸልተኝነት ከሆነ ከ5,000 ብር እስከ 25,000 ብር የገንዘብ ቅጣት በተጨማሪነት እንደሚቀጣ አስቀምጧል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጋር በተያያዘ የሚነሱ የፍትሐ ብሔር ክሶችን የማየት ሥልጣን ጽሕፈት ቤቱ የሚያቋቁመው የአዕምሮአዊ ንብረት ትሪቡናል እንደሚሆን በማሻሻያው ተካቷል፡፡ በዚህ ትሪቡናል ውሳኔ ቅር የተሰኘ በ60 ቀናት ውስጥ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችልም በማሻሻያው ተካቷል፡፡

በዚህ የማሻሻያ አዋጅ አንቀጽ ላይም አቶ ተሰፋዬ ዳባ ያላቸውን የሕግ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ ማንኛውም የሕግ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ መዳኘት የሚገባው በሕግ በተቋቋመ ክርክር መሆኑን ገልጸው፣ ይኼንን የአዕምሮአዊ ጉዳይ የፍትሐ ብሔር ፍርድ ቤት በጽሕፈት ቤቱ ወደሚመራው የአዕምሯዊ ንብረት ትሪቡናል ማምጣት ለምን አስፈለገ? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ይህ ዓይነቱ አሠራር የፍትሕ ሥርዓቱ ሥልጣንን የሚሸረሽር በመሆኑ ጉዳዩ በዝርዝር ሊታይ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም መሠረት ማሻሻያ አዋጁን በዝርዝር ተመልክቶ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡