Print this page
23 October 2014 Written by  EthiopianReporter

በሐዋሳ ከተማ የሕግ ባለሙያውን ገድለዋል የተባሉት ተጠርጣሪ ተያዙ

ተጠርጣሪው በሌላ ወንጀል 12 ዓመታት ተፈርዶባቸው ሲፈለጉ እንደነበር ተገልጿል

በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ ውስጥ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ዳንኤል ዋለልኝ የተባሉ የሕግ ባለሙያን በጥይት ገድለው መሰወራቸው የተገለጸው ባለሀብት፣ ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታወቀ፡፡

ባለሀብቱ አቶ ታምራት ሙሉ መሆናቸውንና በሐዋሳ ከተማ ከሚገኙ ሆቴሎች መካከል አንዱ የሆነው ብሉ ናይል ሆቴልና ኢቪኒንግ ስታር ሆቴል ባለቤት መሆናቸውን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪው ባለሀብት አቶ ታምራት፣ በክልሉ ታዋቂ ጠበቃ መሆናቸው የተገለጸውን አቶ ዳንኤልን ገድለዋል ከተባሉ በኋላ ተሰውረው የከረሙት ለ12 ቀናት ብቻ መሆኑን ምንጮች ሲጠቁሙ፣ ጥቅምት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለው፣ ጥቅምት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ደቡብ ክልል መወሰዳቸውን ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ 

በከተማው ውስጥ ቢቆዩ ለደኅንነታቸው ያሰጋል በሚል፣ ከሐዋሳ ከተማ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ይርጋለም ከተማ አካባቢ በሚገኘው የደቡብ ፖሊስ ማሠልጠኛ አፖስቶ ኮሌጅ ተወስደው መታሰራቸውም ተጠቁሟል፡፡ 

ተጠርጣሪው በጠበቃው ላይ ግድያውን የፈጸሙበትን ምክንያት ምንጮች እንዳስረዱት፣ ‹‹መልጌ መርሳ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ›› በሚባለው ድርጅታቸው ሥር ከሚገኙት ‹‹ብሉ ናይል ሆቴልና ኢቪኒንግ ስታር ሆቴል›› መካከል ‹‹ኢቪኒንግ ስታር ሆቴል›› የተባለውን ሆቴል፣ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ መሆኑ ለተገለጸው አቶ መሐመድ ሰዒድ ለሚባሉ ግለሰብ ይሸጣሉ፡፡ ሁለቱ ወገኖች የሆቴሉን ሽያጭ በሚመለከት በተዋዋሉት መሠረት መፈጸም ባለመቻላቸው፣ አቶ መሐመድ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ የፍትሐ ብሔር ክስ ያቀርባሉ፡፡ 

አቶ መሐመድ ለአቶ ታምራት መጥሪያ ይዘው በአድራሻቸው ሲሄዱ ሊያገኟቸው ባለመቻላቸው ወደ ፍርድ ቤት ይመለሳሉ፡፡ ‹‹አቶ ታምራትን ላገኛቸው ስላልቻልኩኝ በሌሉበት ይታይልኝ፤›› በማለትም ያመለክታሉ፡፡ የአቶ ታምራት ጠበቃ ነኝ ያሉ የሕግ ባለሙያ ቀርበው መቃወሚያ ማቅረባቸውንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአቶ መሐመድ ወኪል የነበሩት ሟች አቶ ዳንኤል፣ አቶ ታምራት በሌላ ወንጀል ተከሰው 12 ዓመታት የተፈረደባቸውና ጠፍተው በመፈለግ ላይ መሆናቸውን ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውንም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪውን ወክለው እንደቀረቡ የሚናገሩትን ጠበቃ ባለቤቱ በሌለበት ውክልና መስጠት ስለማይቻል፣ ተወካይ ነኝ ብለው ለክርክር መቅረባቸው ሕጋዊ መሠረት እንደሌለው ለፍርድ ቤቱ ያስረዳሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ የሟቹን ጠበቃ መከራከሪያ ነጥብ በመቀበል፣ የተጠርጣሪውን ጠበቃ ክርክር ውድቅ ማድረጉንም አክለዋል፡፡ 

ተጠርጣሪው ባለሀብት አቶ ታምራት ሙሉ ቀደም ባሉት ወራትም በደረቅ ቼክ ምክንያት ክስ ተመሥርቶባቸው፣ ሟች ጠበቃ ተከራክረው እንዳሸነፏቸውና መጨረሻ ላይ ከከሳሽ ጋር በሽምግልና ለመጨረስ ለመስከረም 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ የያዙ ቢሆንም፣ መስከረም 27 ቀን 2007 ዓ.ም. አቶ ዳንኤል ዋለልኝን በመግደል መሰወራቸውን ምንጮቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሟች ረዳት ጠበቃ ናቸው የተባሉት አቶ ዳግማዊ አሰፋ በወቅቱ አንገታቸው አካባቢ በጥይት ተመትተው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በኮሪያ ሆስፒታል ቀዶ ሕክምና እንደተደረገላቸውና የአቶ ዳንኤል የቀብር ሥርዓት በሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መፈጸሙን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ተጠርጣሪው አቶ ታምራት 12 ዓመታት ተፈርዶባቸው ነበር የተባለው ከታክስና ከግብር ጋር በተገናኘ መሆኑንም ምንጮች አስታውሰዋል፡፡