Print this page
06 October 2014 Written by  FanaBC

በስለላ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው 3 ግለሰቦች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ የወንጀል ችሎት በስለላ ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ሶስት ግለሰቦች እንዲከላከሉ ብይን ሰጠ። ተከሳሾቹ ነጋሲ ብርሀነ ሹማይ፣ ተበጀ በረኸ እና ብለፅ ገብረፃድቃን በትግራይ ከልል ምስራቃዊ ዞን ጉለመዲ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌያት የሚኖሩ ናቸው።

በኢትዮጵያ ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ ለውጭ ሀገር ጥቅም ሲሉ ከኤርትራ መንግስት የደህንነት አባላት ጋር በመገናኘት ዛላንበሳ ስለሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንቅስቃሴ መረጃ ሰጥተዋል በሚል ነው አቃቤ ህግ የከሰሳቸው።

ለዚህ ውለታው ከኤርትራ የደህንነት አባላት በተለያዩ ጊዜያት ገንዘብ ተቀብለዋል የሚለውም በክሱ ተጠቅሷል። በኤርትራ መንግስት የደህንነት አባላትም ስለ ስለላ ስልጠና መውሰዳቸ በክሱ ተጠቅሷል።

ከሳሽ አቃቤ ህግ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ተኛ የወንጀል ችሎት ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ አሰምቷል።

የአቃቤ ህግን ምስክር የመረመረው ችሎቱ ተከላከሉ ሲል ብይን ሰጥቷል። ውጤቱንም ለመጠበቅም ለህዳር 5 2007 አ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።