Print this page
05 October 2014 Written by  EthiopianReporter

በአስከሬን ምርመራ ውጤት ፖሊስና ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ተፋጠዋል

‹‹በአንድ ቀን መሰጠት ያለበት ውጤት ከወር በላይ እያስቆጠረ ነው›› የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

‹‹ምንም ችግር የለብንም›› ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል

በሰው እጅ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ሕይወቱ በድንገት ያለፈን ሰው አስከሬን በምርመራ (ከትግራይ ክልል በስተቀር) ለሁሉም የአገሪቱ ክልሎች አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል፣ የምርመራ ውጤት ሳይሰጥ ከአንድ ወር በላይ በማዘግየቱ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር እየተወዛገበ መሆኑ ተጠቆመ፡፡ ሆስፒታሉ ግን ምንም ዓይነት ችግር እንደሌለበት ገልጿል፡፡

በተለያዩ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስከሬን ምርመራ ውጤት ለኢንሹራንስ፣ ለፍርድ ቤትና ለሌሎችም ማስረጃነት በመርማሪው ሆስፒታል በፍጥነት መገለጽ ቢኖርበትም፣ ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ግን በጉዳዩ ላይ ግዴለሽነት መምረጡን ከክልልና ከአዲስ አበባ ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው የሞቱባቸው ተጎጂዎች እየገለጹ ነው፡፡

ወንድሟ በሰው የተገደለባት ወ/ሪት ትዕግሥት ፍሰሐ እንደገለጸችው፣ ወንድሟ የተገደለው በሰው እጅ ነው፡፡ አስከሬኑ ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ገብቶ ምርምራ ከተደረገ ከ25 ቀናት በላይ አልፎታል፡፡ የአስከሬን ምርምራ ውጤቱን ለማግኘት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስትሄድ እንዳልደረሰ ይገለጽላታል፡፡ በተደጋጋሚም ብትመላለስም ምላሹ ተመሳሳይ ሲሆንባት፣ ወደ ሆስፒታሉ በመሄድ ለማነጋገር ብትሞክርም ምላሽ የሚሰጣት በማጣቷ ወዴት እንደምትሄድና አቤት እንደምትል ግራ መጋባቷን ትናገራለች፡፡ ወ/ሪት ትዕግሥት ሌላም ሥጋት እንዳላት ጠቁማለች፡፡ የምርመራ ውጤቱ መዘግየት፣ ‹‹ምናልባት ተጠርጣሪውን ለመልቀቅ ታስቦ ይሆን? የምርመራ ውጤቱ ቆይቶ ሲመጣ ግለሰቡ የሞተው በውስጡ በተፈጠረ ሕመም ነው እንባል ይሆን?›› የሚል ሥጋት እንዳደረባት ገልጻለች፡፡ በሁለቱ መሥሪያ ቤቶች መካከል ያለውን ግንኙነት ባለማወቃቸው በእሷና በቤተሰቧ ላይ ሌላ ተደራራቢ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑንም አክላለች፡፡

ሌሎችም በርካታ የአስከሬን ምርመራ ውጤት የዘገየባቸውና በሟች ዘመዶቻቸው ላይ ስለደረሰው ጉዳት በመግለጽ ለኢንሹራንስም ሆነ ለተለያዩ ጉዳዮች መንቀሳቀስ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ችግራቸውን ተመልክቶ መፍትሔ እንዲጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

አስከሬን ወደ ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል በማስገባት ምርመራ እንዲደረግ ኃላፊነት ያለበትን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ነው፡፡ የሟቾች ቤተሰቦች እየገለጹት ስላለው የምርመራ ውጤት መዘግየት በሚመለከት ሪፖርተር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የግድያ ምርምራ ዲቪዚዮንን አነጋግሮ ምላሽ አግኝቷል፡፡

በኮሚሽኑ የግድያ ምርምራ ዲቪዚዮን እንደገለጸው፣ የአስከሬን ምርመራ ውጤት መዘግየት እውነት ነው፡፡ የምርመራ ውጤት በስታንዳርዱ መሠረት ለፖሊስ ሊሰጠው የሚገባው አስከሬኑ ለምርመራ በገባ በአንድ ቀን ውስጥ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ብቸኛውና ከትግራይ ክልል በስተቀር ለሁሉም ለአገሪቱ ክልሎች የአስከሬን ምርመራ የሚያደርገው ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታል ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ግን የምርምራ ውጤት ሳይሰጥ ከአንድ ወር በላይ እያስጠበቀ መሆኑን ዲቪዚዮኑ አረጋግጧል፡፡

ሆስፒታሉ በመገናኛ ብዙኃን የአስከሬን ምርመራ በአንድ ቀን ውስጥ እየሰጠ መሆኑን እየገለጸ ቢሆንም፣ ሐሰትና ትክክል አለመሆኑን የገለጸው ዲቪዚዮኑ፣ በአሁኑ ጊዜ ኮሚሽኑ ከሆስፒታሉ የሚፈልጋቸውና ከአንድ ወር በላይ ያስቆጠሩ ከ100 በላይ ውጤቶች እንዳሉ አስታውቋል፡፡

ሆስፒታሉ የሚያቀርበው ምክንያት የአስተርጓሚ ችግር እንዳለበት መሆኑንን የገለጸው ዲቪዚዮኑ፣ አስከሬን መርማሪዋ (ፓቶሎጂስት) የኩባ ዜጋና የስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆናቸው፣ ከስፓኒሽ ወደ እንግሊዝኛና ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ የሚተረጉም ባለሙያ እንደሌለ እየገለጸ መሆኑን አስረድቷል፡፡ 

በሆስፒታሉ ውስጥ ከሦስት የማይበልጡ አስተርጓሚዎች መኖራቸውን፣ እነሱንም ቢሆን ሆስፒታሉ በአግባቡ እያሠራቸው ለመሆኑ እንደሚጠራጠር የሚናገረው   ዲቪዚዮኑ፣ በተደጋጋሚ በደብዳቤና በአካል እያሳሰበ መሆኑን፣ አሁንም የመጨረሻ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቋል፡፡ ሆስፒታሉ በዚህ ይዞታው ችግሩን የሚፈታው እንዳልመሰለው ግምቱንም ገልጿል፡፡

የሆስፒታሉ ኃላፊዎች ደብዳቤ ሲጻፍላቸውና በአካል ሲያነጋግሯቸው፣ የማስተንፈስ ሥራ ይሠሩና ችግሩ ቀስ በቀስ እየተከማቸ መሆኑን የጠቆመው ዲቪዚዮኑ፣ የሆስፒታሉ የባለሙያ እጥረት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

ችግር የደረሰበት የኅብረተሰብ ክፍል ተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረበ መሆኑንና ኮሚሽኑም በችግር ውስጥ መሆኑን የገለጸው ዲቪዚዮኑ፣ ኮሚሽኑም ውጤቱን በወቅቱ ማግኘት ባለመቻሉ፣ በተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ አጠናቆ ወደ ፍርድ ቤት ለማቅረብ እንደተቸገረ አስረድቷል፡፡ ችግሩ የፖሊስ ኮሚሽኑ ሳይሆን የሆስፒታሉ መሆኑን የሟች ቤተሰቦች እንዲገነዘቡም አክሏል፡፡

የተፈጠረውን ችግር እንዲያብራሩ የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ክበበው ወርቅነህን ሪፖርተር ቢያነጋግራቸውም፣ ‹‹ምንም ችግር የለም፣ ማንም መጥቶ ማየት ይችላል፤›› በማለት ሆስፒታሉ ሥራውን በአግባቡ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡