Print this page
28 September 2014 Written by  EthiopianReporter

የአቶ ሳሙኤል ዘሚካኤል የዋስትና ጥያቄ ለብይን ተቀጠረ

-  ክሱ ገና አልተሰማም

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ‹‹ዶ/ር ኢንጂነር›› በሚል ሐሰተኛ ማዕረግ በመጠቀም የማታለል ወንጀል ፈጽመዋል በማለት ክስ የመሠረተባቸው አቶ ሳሙኤል ዘሚካኤል፣ በፍርድ ቤት ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ለብይን ተቀጠረ፡፡

የተጠረጠሩበት የወንጀል ክስ ዋስትና የማያስከለክል መሆኑን በመግለጽ የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ሦስት ተቃውሞዎች በማቅረብ ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ባቀረበው የመጀመሪያ መቃወሚያ እንዳስረዳው፣ ተጠርጣሪው ሦስት ተደራራቢ ክሶች ቀርበውባቸዋል፡፡ በመሆኑም ቅጣቱን በመፍራት ሊሰወሩ እንደሚችሉ በመግለጽ ዋስትናውን ተቃውሟል፡፡ የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 13 እና 14 ላይ፣ ተጠርጣሪዎች ተደራራቢ ክስ ከተመሠረተባቸው ዋስትና እንደማይፈቀድላቸው ውሳኔ እንደሰጠበትም ዓቃቤ ሕግ አክሏል፡፡

የተጠርጣሪው ጠበቆች (ሁለት ናቸው) ዓቃቤ ሕግ ላቀረበው የመጀመሪያ መቃወሚያ በሰጡት ምላሽ ሦስት ተደራራቢ ክሶች በደንበኛቸው ላይ እንደቀረበባቸው አረጋግጠው፣ በፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ቅጽ 13 እና 14 ላይም የተላለፈው ውሳኔ እውነት መሆኑን አክለዋል፡፡ ነገር ግን የሰበሩ ውሳኔ የሚለው በከባድ ወንጀል ስለሚከሰስ ተጠርጣሪ እንጂ፣ በደንበኛቸው ላይ የተመሠረተው ክስና የተጠቀሰው አንቀጽ ዓይነት እንዳልሆነ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ደንበኛቸው በመገናኛ ብዙኃን እንደተነገረውና እንደተወራው ሳይሆን፣ እጅግ በጣም ቀላልና ትንሽ በሆነ ከሁለት ሺሕ ብር እስከ 58 ሺሕ ብር የሚደርስ አነስተኛ ገንዘብ የተጠረጠሩ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም የዓቃቤ ሕግ መቃወሚያ ክሱን ያላገናዘበ በመሆኑ ውድቅ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ በሁለተኛነት ባቀረበው መቃወሚያ ተጠርጣሪው በኢንተርፖል ተፈልገው የመጡ በመሆናቸው፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና ቢፈቅድላቸው አክብረው ይቀርባሉ የሚል እምነት እንደሌለው በመጥቀስ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡

ደንበኛቸው ዓቃቤ ሕግ እንዳለው ኮብልለው ከአገር ሳይሆን፣ ሕጋዊ ፓስፖርታቸውን ተጠቅመው በኢትዮጵያ አየር መንገድ የወጡ መሆናቸውን በመግለጽ፣ ሁለተኛውን የዓቃቤ ሕግ ተቃውሞን የተቃወሙት የተጠርጣሪው ጠበቆች፣ በወቅቱ በመገናኛ ብዙኃን ከሚነገረውና ከሚወራው ባለፈ በሕግ አስፈጻሚው ፖሊስ በኩል እንደሚፈለጉ እንዳልተገለጸላቸው (መጥሪያ እንዳልደረሳቸው) አስረድተዋል፡፡ ‹‹ኮብልለው በኢንተርፖል አማካይነት ነው የመጡት›› እንደማያስብልም አስረድተዋል፡፡ ተፈልገው ቢጠፉ ኖሮ ሊወጡ ሲሉ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሊያዙ ይችሉ እንደነበርም አክለዋል፡፡ ደንበኛቸው ኬንያ በነበሩበት ወቅትም እንደሚፈለጉ ተነግሯቸው ስላልቀሩ፣ ‹‹በኢንተርፖል ተይዘው መጥተዋል›› በሚል የዋስትና መብታቸው ሊታለፍ ስለማይገባው የዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ ውድቅ እንዲደረግላቸው አመልክተዋል፡፡ 

ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በስተመጨረሻ ያቀረበው የዋስትና መቃወሚያ ተጠርጣሪው ቀደም ባሉት ጊዜያት በቼክ ተከሰው ጥፋተኛ ተብለው እንደነበር በማስታወስ፣ በዋስ ቢወጡ ሕግ አክብረው ይቀመጣሉ የሚል እምነት እንደሌለው በማስረዳት የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግለት አመልክቷል፡፡ 

ቼክ ሕጋዊ ገንዘብን ተክቶ የሚሠራ መሆኑን በመናገር አንዳንድ ጊዜ ‹‹በቂ ስንቅ የለውም›› ተብሎ እንደሚመለስ ለፍርድ ቤቱ ያስረዱት የተጠርጣሪው ጠበቆች፣ ዓቃቤ ሕግ ቀደም ብሎ የተሰጠን ውሳኔ ለክርክር ማቅረቡ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 138ን መተላለፍ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ደንበኛቸው ዋስትና ሊከለከሉ የሚችሉበት ምንም ዓይነት የሕግ ድጋፍ ስለሌለ፣ የዓቃቤ ሕግ መቃወሚያ ውድቅ ተደርጐ ደንበኛቸው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የሁለቱን ወገኖች ክርክር ካዳመጠ በኋላ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡