Print this page
21 September 2014 Written by  EthiopianReporter

የጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽ ባለድርሻ ደረቅ ቼክ በመስጠት ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ

- የአንድ ሚሊዮን ብር ዋስ አስይዘው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል

ባለፈው ዓመት መጨረሻ ወር አካባቢ ሥራ የጀመረው ጨጨሆ የባህል የምግብ አዳራሽ አክሲዮን ማኅበር ባለድርሻ አቶ ወንድዬ አቻምየለህ፣ ከወራት በፊት በጻፉት የሁለት ሚሊዮን ብር ደረቅ ቼክ ወንጀል ተጠርጥረው መስከረም 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ክስ ተመሠረተባቸው፡፡ 

የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክስ የመሠረተባቸው የጨጨሆ ባህል ምግብ አዳራሽ ባለድርሻ አቶ ወንድዬ አቻምየለህ የተባሉት ባለሀብት፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ አፋጣኝ ችሎት የቀረቡት ለሦስት ቀናት ታስረው ከቆዩበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ ነው፡፡

አቶ ወንድዬ ከጠበቃ ጋር የቀረቡ ሲሆን፣ ክሱ ከተነበበላቸው በኋላ ክሱን መረዳታቸውንና ግልጽ መሆን አለመሆኑን ፍርድ ቤቱ ጠይቋቸው ‹‹ክሱ ግልጽ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የለንም፤›› በማለት በጠበቃቸው አማካይነት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በመቀጠልም ‹‹ቼኩን ጽፌያለሁ፡፡ ጥፋተኛ ነኝ ብዬ ግን አላምንም፤›› በማለት ክደው የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ባለሀብቱ ክደው በመከራከራቸው ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ምስክሩን አቅርቦ እንዲያሰማ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ ዓቃቤ ሕግም የግል ተበዳይ ናቸው ያላቸው ምስክሩ ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ 

ምስክሩ የጉዳዩ ዋና ባለቤት መሆናቸውን ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ ከተጠርጣሪው ጋር ከመጀመሪያ ግንኙነታቸው ጀምሮ ወንጀሉ እንዴት እንደተፈጸመ እንደሚያስረዱለት ጭብጥ በማስያዝ ምስክሩ እንዲሰሙ ተደረገ፡፡

ፍርድ ቤቱ በሌሎች ፍርድ ቤቶች ከሚፈጸመው የመሀላ ዓይነት ማለትም አንድ እጅን በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በቁርዓን ላይ በማስቀመጥ ከሚፈጸም መሀላ በተለየ፣ ምስክሩ የአንድ እጃቸውን መዳፍ ወደ ላይ በማድረግ መሀላ እንዲፈጽሙ ተደርጐ የዓቃቤ ሕግ ዋና ጥያቄ ተጀመረ፡፡

የግል ተበዳይ ናቸው የተባሉት የዓቃቤ ሕግ ምስክር ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ በባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ነበሩ፡፡ እሳቸውና ባለቤታቸው የአቶ ወንድዬ ቤት ነው የተባለውን፣ ነገር ግን በእህታቸው ስም የሆነውን ቤት በመከራየት ‹‹ጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽ›› በሚል ከፍተው ለሦስት ዓመታት ሲሠሩ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ 

ደንበኞቻቸው የአዳራሹን መፀዳጃ ቤት ወደ ሌላ ቦታ እንዲያዘዋውሩ ሲጠይቋቸው፣ አቶ ወንድዬ ሲያማክሯቸው እንዳልተስማሙ የገለጹት ምስክሩ፣ አቶ ወንድዬ ‹‹ለምን ባለድርሻ አድርጋችሁኝ በጋራ አንሠራም?›› የሚል ጥያቄ ማንሳታቸውን መስክረዋል፡፡ 

ተስማምተው ‹‹ጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽ አክሲዮን ማኅበር›› በሚል በጋራ ለአንድ ዓመት ያህል ከሠሩ በኋላ፣ ‹‹አዲስ አበባም ለመሥሪያ የሚሆን ቦታ አለኝ፣ ቁጥር ሁለት ለምን አንከፍትም?›› በማለት አቶ ወንድዬ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ምስክሩ ባለቤታቸውን በማማከር እንደተስማሙና ሥራው እንደ ተጀመረ ተናግረዋል፡፡

ቦታው በአቶ ወንድዬ ስም ባይሆንም የእሳቸው ይዞታ መሆኑን እንደተረዱ የተናገሩት ምስክሩ፣ በወር 30,000 ብር ሒሳብ የአንድ ዓመት ኪራይ ከፍለው የባህል ምግብ አዳራሹን በጋራ ሠርተው ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽ ቁጥር ሁለትን ለፋሲካ (2006 ዓ.ም.) ለመክፈት በዝግጅት ላይ እያሉ፣ አቶ ወንድዬ ‹‹እኔ ከእናንተ ጋር መሥራት አልፈልግም፣ የሠራሁበትን አራት ሚሊዮን ብር ስጡኝ፡፡ ለአዳራሹ ኪራይ ደግሞ በየወሩ 200,000 ብር እንድትሰጡኝ ውል ፈርሙልኝ፡፡ ወይም እኔ ድርሻችሁን ልስጣችሁና ልቀቁልኝ፤›› ማለታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

ምስክሩ እንዳስረዱት በጓደኞቻቸውና በሽማግሌዎች አብረው እንዲሠሩ ቢያስጠይቋቸው ሊስማሙ ባለመቻላቸው፣ ሽማግሌዎች አቶ ወንድዬ ድርሻቸውን አራት ሚሊዮን ብር እንዲሰጧቸው በማስማማት፣ ሚያዝያ 27 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀነኒሳ ሆቴል ውስጥ ሁለት ሚሊዮን ብር ወዲያውኑ ከፍለዋቸው፣ የሁለት ሚሊዮን ብር ቼክ በመጻፍ ግንቦት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. እንዲያወጡ መስማማታቸውን አስረድተዋል፡፡

ቼኩን የሚያወጡበት ቀን ሲደርስ አቶ ወንድዬ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጧቸው ምስክሩን ሲጠይቋቸው መስማማታቸውን፣ ከሁለት ወር በኋላ ስልክ ደውለው ሲጠይቋቸው ‹‹እኔና አንተ ቁጭ ብለን ብንነጋገር ይሻላል፣ አለበለዚያ ገንዘቡን አታገኘውም፡፡ እኔ ከታሰርኩ ማንም ሊሰጥህ አይችልም፤›› እንዳሏቸው ምስክሩ ገልጸዋል፡፡ በመሀል ሽማግሌዎች በመላክ 20 ቀናት ብቻ እንዲሰጧቸው ሲለምኗቸው በመስማማት 22 ቀናት ሰጥተው በጳጉሜን 2006 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሀል ከተማ ቅርንጫፍ ሄደው ሲጠይቁ፣ በቂ ገንዘብ (ስንቅ) የለውም መባላቸውን ተናግረዋል፡፡ ባንኩ እንዲመታላቸው ሲጠይቁ ‹‹ደንበኛችን ነው›› በማለት አልመታ ብሏቸው ከብዙ ትግል በኋላ እንደመታላቸውና ለፖሊስ መስጠታቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የተጠርጣሪ ጠበቃ ለምስክሩ ጨጨሆ የባህል ምግብ አዳራሽን በጋራ ስለማቋቋማቸው መስቀለኛ ጥያቄ ሲያቀርቡላቸው ‹‹አዎ አብረን አቋቁመናል›› የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የማጣሪያ ጥያቄ ጠይቋቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አቶ ወንድዬ ‹‹ጥፋተኛ ነኝ ብዬ አላምንም›› ያሉበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ተጠይቀው ቤተሰብ መሆናቸውን፣ ሁለት ሚሊዮን ብር ስለከፈሏቸውና ቀሪውን ለመክፈል በመሯሯጥ ላይ እያሉ ምስክሩ ቼኩን ማስመታታቸውን ገልጸዋል፡፡ ቼኩን የጻፉት ለመተማመኛነት እንጂ ለክፋት አስበው አለመሆኑን በማስረዳት፣ በቅን ልቦና ያደረጉት ነገር እንደ ወንጀል ይወሰድብኛል የሚል ሐሳብ ስለሌላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

የጨጨሆ የባህል አዳራሽ አክሲዮን ማኅበር 70 በመቶው ድርሻ የእሳቸው መሆኑን፣ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል የያዘ ድርጅት የሚመሩትና የሚያስተዳድሩት እሳቸው መሆናቸውን፣ ከ90 በላይ ለሆኑ ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጣራቸውንና የሚያስተዳድሩት እሳቸው መሆኑን፣ ትምህርት ቤት የሚያመላልሷቸውና የሚንከባከቧቸው ሁለት ሕፃናት ልጆች እንዳሏቸው፣ የሚያስተዳድሯቸው ቤተሰቦችም በርካታ በመሆናቸው፣ ይህንን ሁሉ ኃላፊነት ወደ ጐን በመተው የሚያስጠይቅ ወንጀል ሊፈጽሙ እንደማይችሉ ለፍርድ ቤቱ በማስረዳት ጥፋተኛ ነኝ ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ወዲያውኑ የሁለቱንም ወገኖች ክርክር መርምሮ፣ አቶ ወንድዬ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ አቶ ወንድዬ ዋስ ተፈቅዶላቸው በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ለፍርድ ቤቱ በማመልከቻ አቅርበዋል፡፡ 

ዋስትናውን በሚመለከት ዓቃቤ ሕግ ተጠይቆ ስለልጆቻቸውም ሆነ ቤተሰቦቻቸው ያቀረቡት ማስረጃ እንደሌለ ተናግሯል፡፡ በመቀጠልም ተጠርጣሪው ‹‹የእኔ ንብረት ነው›› ከማለት ባለፈ በሰነድ የተረጋገጠ ንብረት ስለሌላቸው በዋስ ቢወጡ ይቀርባሉ የሚል እምነት እንደሌለው በመግለጽ፣ በወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት ቁጥር 67(ሀ) መሠረት ዋስትናው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪው ከላይ ያብራሩትን በመጥቀስ ዋስትና ቢከለከሉ ሊተካ የማይችል ጉዳት በድርጅታቸው፣ በቤተሰባቸው፣ በሠራተኞቻቸውና በራሳቸውም ላይ ሊደርስ እንደሚችል በማስረዳት፣ ፍርድ ቤቱ በበቂ ዋስ እንዲለቃቸው በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የዋስትና ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ፣ ተጠርጣሪው የአንድ ሚሊዮን ብር ዋስትና አስይዘው እንዲለቀቁ አዟል፡፡ በቀረበባቸው ክስ እንዲከላከሉ በተሰጠው ብይን መሠረት፣ ተጠርጣሪው የመከላከያ ማስረጃቸውን ለታኅሣሥ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ አዟል፡፡