15 September 2014 Written by  EthiopianReporter

ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 17 የውጭ ዜጎች ክስ ተመሠረተባቸው

የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው የንግድ ሥራ በመሥራት፣ የንግድ ትርፍ ግብር፣ ተጨማሪ እሴት ታክስ ባለመክፈል፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብና ሐሰተኛ ሰነዶችን በማቅረብ ወንጀል የተጠረጠሩ የሲሪላንካ፣ የህንድ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ የጂቡቲ፣ የኒውዚላንድና ኢትዮጵያውያን 17 ግለሰቦች ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የገቢ ግብርና ቫት ባለመክፈል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ምንጭና ዝውውር በመደበቅና በሕገወጥ መንገድ በመያዝ ተከሰዋል፡፡ 

የፌዴራል  ዓቃቤ ሕግ ጳጉሜን 4 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ክስ የመሠረተባቸው፣ ተጠርጣሪዎች ኢትዮጵያውያን አሽረፍ አወል አብዶና በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት አካፔ ኢምፔክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የሲሪላንካ ዜጋ የሆኑት ሂትራጅግ ያሳንታ ሱሬንድራናታ፣ ፕላንዋታጅ አሲታ፣ ቦፒ ጊድራ አጅት፣ አሳንታ ኡዳያ፣ ኩሩፑ አራችችግ፣ የህንድ ዜግነት ያላቸው አንኪት ሙኪሽ መሂታ፣ አሾክ ሞሃንላል፣ ኩማር ኤም፣ ቪሻል ኩማርና ሙኒሽ ኩማር፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ዜግነት ያላቸው መሐመድ ሽፋን መሐመድ፣ ኦቶ ወርልድ ኢንተርናሽናል ፍሪዞን ኩባንያና ዱባይ ኦቶ ጋላሪ ኤልኤልሲ፣ የኒውዚላንድ ዜጋ ሱሀስ ፓራሳድና የጅቡቲ ዜግነት ያላት ሲና መሐመድ መሐሙድ ይባላሉ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለይ ዱባይ ኦቶ ጋለሪ ኤል.ኤል.ሲና ኦቶ ወርልድ ኢንተርናሽናል ፍሪዞን ኩባንያዎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን አካፔ ኢምፔክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር እንደ ሽፋን በመጠቀም የወንጀል ድርጊት መፈጸማቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
የሲሪላንካ ዜግነት ያላቸው ሂትራጅግ ያሳንታ ሱሬንድራናታ ሂትያራጅጅ (ሱሬንድራ)ና ፕላን ዋታጅ አሲታ ሳራናታ ፔሬር (አሲታ) ድርጅቶችን በሚመለከት ሁለት የሲሪላንካ ዜጐች በኢትዮጵያ የዱባይ ጋለሪ መሪና ረዳት መሪ በሚል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውንም ክሱ ያስረዳል፡፡ ዱባይ ኦቶ ጋለሪና ኦቶ ወርልድ ኢንተርናሽናል ኩባንያዎች፣ በኢትዮጵያዊው አሽረፍ አወልና የጅቡቲ ዜግነት ባላት ሲና መሐመድ ባለቤትነት የተቋቋመውን አካፔ ኢምፔክስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን በሽፋንነት በመጠቀም፣ ሐሰተኛ የሥራ ውል መፈራረማቸውም በክሱ ተጠቅሷል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ምንም ዓይነት የፀና የሥራ ፈቃድ ሳይኖራቸው፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተከለለና ለውጭ ዜጎች ባልተፈቀደ የንግድ ሥራ ዘርፍ በመሰማራት፣ የባጃጅ ምርትና መለዋወጫ በቀጥታ ከዱባይ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገቡ እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ጂቡቲ ውስጥ ከሚገኝ የንግድ ድርጅት ኤስዲሲ በርበራ ፍሪዞን ኩባንያን በመጠቀም በጂቡቲ በኩል ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት፣ በኢትዮጵያ በሚገኙ ክልሎች፣ ዞኖችና የወረዳ ከተሞች በመዘዋወር የገበያ ጥናትና ሌሎች ተያያዥ የንግድ ሥራዎችን በመሥራት ለዱባይ ኦቶ ጋለሪ ኤልኤልሲ ሪፖርት ሲያደርጉ መገኘታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በተቋቋመው አካፔ ኢምፔክስ ተቀጣሪ ሠራተኞች በመምሰል፣ ሐሰተኛ የሥራ ቅጥር ውል በመፈራረምና በድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ኢትዮጵያዊው አቶ አሽረፍ አወልና በድርጅቱ ተጠያቂነት በሌላ የሥራ መደብ ፈቃድ በማውጣት ሲጠቀሙ እንደነበርም ክሱ ይገልጻል፡፡

ህንዳዊው አሾክ ሞሃንላል ሻርማና ኒውዚላንዳዊው ሱሀስ ፓራሳድ በቱሪስት ቪዛ ወደ አገር ውስጥ ገብተው፣ ያለምንም የሥራ ፈቃድ የባጃጅ መለዋወጫ ሽያጭ ንግድ ሥራ ውስጥ በመሰማራት በክልሎች በሚገኙ የዞንና የወረዳ ከተሞች በመዘዋወርና የገበያ ጥናት በማድረግ፣ ለዋና ድርጅታቸው ሪፖርት ሲልኩ መገኘታቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያቋቋሙትን አካፔ ኢምፔክስ በሽፋንነት በመጠቀም ለኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ብቻ የተከለለና ለውጭ ዜጎች በማይፈቀድ የአስመጭነት፣ የጅምላና የችርቻሮ ንግድ ሥራ ውስጥ ተሰማርተው መገኘታቸውንና ምንም ዓይነት የሥራ ፈቃድና የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሽፋን በመስጠት፣ በቱሪስት ቪዛ ብቻ የባጃጅ ንግድ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

አካፔ ኢምፔክ፣ ዱባይ ኦቶ ጋለሪ ኤልኤልሲና ኦቶ ወርልድ ኢንተርናሽናል ፍሪዞን ኩባንያዎች ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥሮችን የወሰዱ ቢሆንም፣ የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው ለውጭ ባለሀብት የማይፈቀድ ሥራ ላይ በመሰማራት ካገኙት ገቢ ግብር አለመክፈላቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ በመሆኑም ሐሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የገቢ ንግድ ግብርና ተጨማሪ እሴት ታክስ አለመክፈላቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ ከ416 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ምንጩንና ዝውውሩን መደበቃቸው ተጠቅሷል፡፡ እንዲሁም ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ በኢትዮጵያዊው አሽረፍ አወልና በድርጅቱ አካፔ ኢምፔክስ ስም በተለያዩ ባንኮች በማስቀመጥ፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው ማቅረባቸውን ክሱ ይዘረዝራል፡፡

ህንዳዊው ቪሻል ኩማር ላክሃኒ ደግሞ የባጃጅ መገጣጠሚያና ማምረቻ ንግድ የሥራ ዘርፍ፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ የኢንቨስትመንት ፈቃድና የንግድ ፈቃድ በማውጣት፣ እንዲሁም ኤሽያ አፍሮ አውቶሞቢልስ በሚል ከንግድ ሚኒስቴር በተሰጠው የንግድ ስያሜ ቪሻል ኩማር ላክሀኒ የሚል ድርጅት ማቋቋሙን ክሱ ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን የመገጣጠሚያ ፋብሪካውን ሳያቋቁምና ምንም ዓይነት የአስመጪነት፣ የአከፋፋይነትና የችርቻሮ የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖረው፣ ባጃጅ ከውጭ አገር በማስመጣት ሳይገጣጠም በጅምላና በችርቻሮ ሲሸጥ እንደነበር በክሱ ተካቷል፡፡ ተጠርጣሪው ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ የገቢ ግብርና ተጨማሪ እሴት ታክስ ካለመክፈሉም በላይ፣ በሕገወጥ ንግድና ግብር ሲሠራ ያገኘውን ከ330 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ፣ ከወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ የገንዘቡን ምንጭና ዝውውር መደበቁን ክሱ ያብራራል፡፡

የጂቡቲ ዜግነት ያላት ተጠርጣሪ ሲና መሐመድ መሐሙድ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በዱባይ የኢትዮጵያ ቆንሲላ ጽሐፈት ቤት ቀርባ፣ ‹‹የቤት እመቤት›› የሚል ሐሰተኛ መረጃ በመስጠት መታወቂያ በማግኘት ስትገለገልበት በመክረሟና ሐሰተኛ የሆነ ኦፊሴላዊ ሰነድ በማጭበርበር ማግኘት ወንጀል መከሰሷን የዓቃቤ ሕግ ክስ በዝርዝር ያሳያል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በአጠቃላይ ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ የገቢ ንግድ ግብርና ቫት ባለመክፈል፣ ከ716 ሚሊዮን ብር በላይ ምንጩንና ዝውውሩን በመደበቅ፣ እንዲሁም ከ104 ሚሊዮን ብር በላይ በሕገወጥ መንገድ በመያዝ ክስ ተመሥርቶባቸዋል፡፡

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ለደንበኞቻቸው የዋስትና መብት እንዲጠበቅላቸው በጽሑፍ ለፍርድ ቤቱ በማቅረባቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ለጥያቄው በጽሑፍ ምላሽ እንዲሰጥ ለመስከረም 6 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡