03 September 2014 Written by  EthiopianReporter

ሐሰተኛ ሰነዶችን ሕጋዊ አስመስሎ በማዘጋጀት ወንጀል የተጠረጠሩት የፈጣን መደብር ባለቤት ታሰሩ

-ፈጣን መደብር የሞዝቮልድ ድርጅት አካል ነው በሚል ካርታው መክኗል   -ሁለት የመሬት አስተዳደር ኃላፊዎች የነበሩ ግለሰቦች በክሱ ተካተዋል

ሕጋዊ ባልሆነና መንግሥታዊ ሰነዶችን አስመስሎ በማዘጋጀት ፍርድ ቤትን በማሳሳት፣ ከሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የይዞታ ማረጋገጫ ጋር ተካቶ ፈጣን መደብር ተብሎ ይጠራ የነበረን ድርጅት፣ ‹‹ፈጣን የችርቻሮ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› በሚል ወደ ግል ይዞታነት በማዘዋወር የተጠረጠሩት አቶ ፍቃዱ ወርቁ ክስ ተመሥርቶባቸው ታሰሩ፡፡

ከአቶ ፍቃዱ ወርቁ ጋር በመመሳጠር ፈጣን መደብር የሞዝቮልድ ንብረት መሆኑን እያወቁና በአንድ ካርታ ተጠቃሎ የይዞታ ማረጋገጫ (ካርታ) ሰነድ እንዳይሠራ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ፣ የቀድሞ የአዲስ አበባ መሬት አስተዳደር ባለሥልጣን የቦታና ውል ምዝገባና የውል ማስፈጸሚያ ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ዘለለውና ውል መዝጋቢና አጣሪ የነበሩት አቶ አሀዱ ኤሊያስም በክሱ ተካተዋል፡፡ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ክስ የመሠረተው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ለክሱ መነሻ የሆነው ምክንያት በዝርዝር አቅርቧል፡፡  ክሱን በመመርመር ላይ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ነው፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ ፈጣን መደብር (አሁን የችርቻሮ ንግድ ኃ/የተ/የግ/ማ) በአራዳ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ወረዳ 2 ቀበሌ 12 ሲኒማ ኢትዮጵያ አካባቢ ይገኛል፡፡ መደብሩን የግል ተበዳይ ሆነው ለክሱ መጀመር ምክንያት የሆኑት አቶ ፍቃዱ አምባዬና አሁን በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል የታሰሩት አቶ ፍቃዱ ወርቁ፣ በጋራ ከመንግሥት ቤቶች ሽያጭ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ይገዙታል፡፡ ሁለቱም ባለድርሻዎች ሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርን ገዝተው ስለነበር፣ ፈጣን መደብርን ከሞዝቮልድ ጋር በመቀላቀል ካርታ እንዲሠራ የመንግሥት ቤቶች ሽያጭ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት በደብዳቤ አሳውቋቸው እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡ 

የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዱ (ካርታው) ሁለቱ ባለድርሻ አካላት ባለቤት በሆኑበት ሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም መዘጋጀት ሲገባው፣ ተጠርጣሪው አቶ ፍቃዱ ወርቁ ከልጆቻቸው ጋር በመሆን ፈጣን መደብርን፣ ‹‹ፈጣን የችርቻሮ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› በሚል ስም የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ፣ ከአቶ ሀብታሙ ዘለለውና አቶ አሀዱ ኤልያስ ጋር በመመሳጠር ማሠራታቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡

ተጠርጣሪው አቶ ፍቃዱ ይኼንን ሊያደርጉ የቻሉት፣ የግል ተበዳይ የሆኑት አቶ ፍቃዱ አምባዬ በትውልድ ኤርትራዊ በመሆናቸውና በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ከአገር በመውጣታቸው ምክንያት መሆኑንም ክሱ አብራርቷል፡፡ የድርጅቱ ስም ‹‹ፈጣን የችርቻሮ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› በሚል ስያሜ እንዲቀጥል በመደረጉም፣ በአቶ ፍቃዱ አምባዬ ላይ የ1.5 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉት በዋናነት በአስተዳደሩ የቦታና ውል ምዝገባና የውል ማስፈጸሚያ ቡድን መሪ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ዘለለው መሆናቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡ 

በመሬት አስተዳደር ባለሥልጣን ውል መዝጋቢና አጣሪ የነበሩት አቶ አሐዱ ኤልያስ በበኩላቸው፣ የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ፈጣን መደብርን አካቶ በሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም እንዲዘጋጅ ተገልጾና በማህደሩ ተያይዞ እያለ፣ በትክክል ያልተሞላውን ሰነድ ‹‹በትክክል ተሞልቷል›› በማለት መፈረማቸው በክሱ ተገልጿል፡፡ አቶ አሐዱ፣ አቶ ሀብታሙና አቶ ፈቃዱ ወርቁ በመመሳጠር ‹‹ፈጣን መደብር›› የሚለውን ስም ‹‹ፈጣን የችርቻሮ ንግድ ኃ/የተ/የግ/ማ›› በሚል ስም ተቀይሮ መሠራቱን አቶ ሀብታሙ አረጋግጠው በፈረሙበት ደብዳቤ ላይ፣ ምልክት (ፓራፍ) በማድረግ ስለትክክለኛነቱ በማረጋገጣቸው፣ በአቶ ፍቃዱ አምባዬ ላይ የ1.5 ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ ፍቃዱ ወርቁ የአቶ ፍቃዱ አምባዬን ከአገር የመውጣት አጋጣሚ በመጠቀም፣ አስቸኳይ ስብሰባዎችን በማድረግና ቃለ ጉባዔዎችን በመያዝ፣ የአቶ ፍቃዱ አምባዬ ተወካይ የነበሩትንና በክሱ አራተኛ ተጠርጣሪ ሆነው የተካተቱትን አቶ መላኩ ፈለቀን፣ ድርጅቱን ለቀው እንዲወጡ ማድረጋቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ ተወካዩ ከወጡ በኋላ አቶ ፍቃዱ አምባዬ ባለድርሻ የሆኑበት ሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የባንክ ዕዳ እንዳለበት ሲያውቁ፣ አቶ ፍቃዱ ወርቁ ከአቶ ሀብታሙና አቶ አሐዱ ጋር በመመሳጠር፣ ‹‹ፈጣን የችርቻሮ ንግድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር›› በሚል የይዞታ ማረጋገጫ በልጆቻቸውና በራሳቸው ባለቤትነት ለተቋቋመ ድርጅት ማውጣታቸውንና አቶ ፍቃዱ አምባዬን የነበራቸውን መብት እንዲያጡ ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ተጠርጣሪው ተገቢ ያልሆነ መብትና ጥቅም ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ለማስገኘት እንዲሁም በሌላ ሰው ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ፣ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ከአቶ ፍቃዱ አምባዬ ጋር በነበራቸው የፍትሐ ብሔር ክርክር ላይ ሕጋዊ ያልሆነ ሰነድ በማቅረብ፣ ፍርድ ቤቱን ማሳሳታቸውን ክሱ ይጠቁማል፡፡ ተጠርጣሪው ያቀረቡት ሰነድ፣ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽሕፈት ቤት የተጻፈ በማስመሰል ‹‹ለሚመለከተው ሁሉ›› በሚል ሸኝ ደብዳቤ አቶ ፍቃዱ አምባዬ ለጠበቆቻቸው የሰጡት ውክልና የታገደ መሆኑን በማስረዳታቸው፣ ጠበቆቹ እንዳይከራከሩ በማሳገድ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡ ተጠርጣሪው ፍርድ ቤትን ለማሳሳት በፈጸሙት መንግሥታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀት የሙስና ወንጀል ተከሰውና ዋስትና ተከልክለው ታስረዋል፡፡

አቶ ፍቃዱ አምባዬ በ1990 ዓ.ም. ከአገር ሲወጡ ሞዝቮልድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለውን ድርጅታቸውን እንዲያስተዳድሩላቸው ውክልና የሰጧቸው አቶ መላኩ ፈለቀ የተባሉት ተጠርጣሪ፣ የውክልና ሥልጣናቸውን በመጠቀም ጉዳት ማድረሳቸው በክሱ ተካቷል፡፡ አቶ መላኩ የተሰጣቸውን ውክልና ወደ ጎን በመተው፣ ለራሳቸውና የአቶ ፍቃዱ ወርቁ ልጅ ናቸው ለተባሉት አቶ ሳሙኤል ፈቃዱ ተገቢ ያልሆነ ብልፅግናና ጥቅም ለማስገኘት በማቀድ፣ አቶ ፍቃዱ አምባዬ በማኅበሩ ውስጥ ካላቸው 4,000 አክሲዮን ውስጥ፣ 100 አክሲዮን ለአቶ ሳሙኤል ፍቃዱ፣ 3900 አክሲዮኑን ለሌላ እንዲተላለፍ በማድረግ፣ ምንም ለማይመለከታቸው ግለሰቦች በነፃ በማስተላለፋቸው፣ በከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡ 

ሦስቱን ተጠርጣሪዎች ሊያገኛቸው እንዳልቻለ የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ አስረድቶ፣ በቀጣይ ቀጠሮ እንደሚያቀርብ አሳውቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም አቶ ፍቃዱ ወርቁ የጠየቁትን የዋስትና መብት በማለፍ፣ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ በማዘዝ ለጥቅምት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡