20 August 2014 Written by  EthiopianReporter

ከ100 ሚሊዮን ብር ሙስና ጋር በተገናኘ የተከሰሱ የቀይ መስቀል ማኅበር ኃላፊዎች በእስራት ተቀጡ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እ.ኤ.አ. በ2011 ተከስቶ ለነበረው ድርቅ፣ በሞያሌና አካባቢው የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት የ100 ሚሊዮን ብር የምግብ እህል ግዢ ለመፈጸም በወጣ ጨረታ ላይ በሙስና ተጠርጥረው ክስ ተመሥርቶባቸው በነበሩ የማኅበሩ ሰባት ኃላፊዎች ከአንድ ዓመት እስከ ስድስት ዓመታት በሚደርስ እስራትና ገንዘብ ተቀጡ፡፡

ክሱን ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ሐምሌ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ፣ አንድ ተከሳሽ በሌሉበት የተወሰነባቸው በመሆኑ፣ እጃቸው ከሚያዝበት አንስቶ በሦስት ዓመታት ጽኑ እስራትና በስምንት ሺሕ ብር እንዲቀጡ አዟል፡፡ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ ስድስት ዓመታት ተቀጥተዋል፡፡ ከአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት የተወሰነባቸው አራት ኃላፊዎች በሦስት ዓመታት ገደብ እንዲለቀቁ ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡

በወቅቱ ሊፈጸም ከነበረው የ100 ሚሊዮን ብር ግዢ ላይ ሊጭበረበር የነበረው የሙስና እንቅስቃሴ በዋና ጸሐፊዋና የቦርድ አባላት አማካይነት ከዘረፋ ሊድን መቻሉም ተጠቁሟል፡፡ በወቅቱ ሊገዛ የነበረው የዕርዳታ እህል ጨረታ ለሌሎች ተጫራቾች ተሰጥቶና ግዢው ተፈጽሞ በጉጂና ቦረና ዞኖች ለሚገኙ ከ84 ሺሕ በላይ ተረጅዎች መከፋፈሉም ተገልጿል፡፡ 

ተከሳሾቹን ተከታትሎ በመያዝና ለፍርድ ቤት በማቅረብ ሰባቱ የማኅበሩ ኃላፊዎች በእስራትና ገንዘብ እንዲቀጡ ያደረገው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ነው፡፡ በወቅቱ የዕርዳታ እህሉን ግዥ ተከትሎ ሊፈጸም የነበረውን ሙስና በሚመለከት መዘገባችን ይታወሳል፡፡